ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በዋና መዲናዋ ከሚገኙ ስመ ገናና ባለ አራት ኮከብ ሆቴሎች መሀል አንዱ የሆነው ሐርመኒ ሆቴል ከመንግሥት በኩል ተልከናል ያሉ የጸጥታ ኃይሎች ባለፈው እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረጉት ከፍተኛ ፍተሻ ፈንጂዎችንና የተለያዮ የጦር መሣሪያዎችን በብዛት በሆቴሉ ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያው በሆቴሉ ውስጥ ተከማችቶ መገኘቱ በዕለቱ የነበሩ የአይን እማኞችን ክፉኛ እንዳስደነገጠ ያስታወሱት የዜና ምንጮች የሆቴሉ ባለንብረቶች ሕጋዊ ድርጅታቸውን ለሕገወጥ ዓላማ ሲጠቀሙበት በመገኘቱ ሆቴሉ እንዲዘጋ ተደርጓል ብለዋል።
አፍቃሪ ሕወሓት በሆኑት የአደዋ ተወላጆች ባለሀብትነት እንደተቋቋመ በሚነገረው ሐርመኒ ሆቴል ውስጥ መቀሌ የመሸገው አምባገገነን ቡድን ቁልፍ ሰዎች እጅ እንዳለበት ቀደም ባሉት የሆቴሉ ምስረታ ወቅት በስፋት መናፈሱን የሚያስታውሱ እማኞች የተገኘው ፈንጂ እና የጦር መሣሪያ ሀገሪቱን በሽብርና እልቂት ለመናጥ የሚሻው ህወሓት በከተማዋ ሊያደርስ ያሰበውን ጥፋት አመላካች ነው ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በሐርመኒ ሆቴል በሰዎች በተደረገ ጥቆማ የተገኘውን ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ተከትሎ በተለይም የሆቴሉ ባለቤት በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ሊዉሉ እንደሚችሉ ያመላከቱት የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ግለሰቡ እስካሁን ሳይያዙ የቀረው በተጨማሪ ሀብትነት የሚያስተዳድሯቸው በ22 አካባቢ የሚገኘው ግዙፉ “ጎላጎል ” ህንፃን ጨምሮ በተለያዮ ስፍራዎችም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ከፍተኛ ክትትል በመደረጉ መሆኑን ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሳፋሪ ወንጀል ተጠርጥሮ የተዘጋው ሐርመኒ ሆቴል ሥራ ያቆመው ከኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ጋር በተያያዘ የሆቴሎች ገቢ መቀዛቀዙን ተከትሎ ነው ሲሉ የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ ገልፀዋል።
የአደባባይ ሀቁን ለመሸፋፈን የሞከሩት የሐርመኒ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዜናዊ መስፍን ዛሬ ለንባብ ለበቃው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ሆቴሉ ሥራ ባለመኖሩ ሠራተኞች ደምወዝ እየተከፈላቸው እረፍት እንዲወጡ መደረጉን ጠቁመው፤ ተገኘ ስለተባለው ፈንጂና የጦር መሣሪያ ግን በደፈናው መረጃው የለኝም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

























