ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ በተጀመረው የፍስለታ ጾም፤ በኢትዮጵ የተጋረጠውን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ለማለፍ ሕዝቡ ከክፋት መመለስና ንሥሐ መግባት እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገለጸች።
ሕዝበ ክርስቲያኑ የዘንድሮውን የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ ሱባዔ ፤ እግዚአብሔርን በመፍራትና የተቸገሩትን በመርዳት ማሳለፍ ይገባዋልም ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ እኩሌታ የሚጾመውን ጾመ በፍልሰታን በማስመልከት በሰጠችው መግለጫ ላይ፤ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፤ የዘንድሮው ጾመ ማርያም የሚጾመው ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ተከበው ባሉበት ወቅት መሆኑንም አስረድተዋል።
“እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በምንሠራው ሥራ፤ በምንናገረው ቃል፤ በምናስበው ሀሳብና ምኞት ሁሉ እግዚአብሔር ያውቅብናል፣ ይፈርድብናል፣ ያየናል የሚል አስተሳሰብ በውስጣችን አድሮ ከክፉ ድርጊት መቆጠብ ነው” ያሉት ፐፓትርያርኩ፤ኢትዮጵያ የዚህ ትውልድ ብቻ ሳትሆን ያለፈውም፣ የወደፊቱም ጭምር እንደመሆኗ መጠን ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታትና ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ የሁሉም እንደሆነ ገልጸዋል።
ሕዝበ ክርስቲያኑ የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታን ኮቪድ-19ን በመከላከል፣ የተቸገሩትን በመርዳት እንዲያሳልፍ የተማጸኑት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ፤
ሕዝቡ ከይቅርታና እርቅ፤ ከሰላምና አንድነት የተሻለ የችግሮች ማሸነፊያም ሆነ ማስወገጃ የለውም ብለዋል።