ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ትህነግ የፌደራል መንግሥቱን ጥቃት ለመመከት የተከለው የሚሳይል መቃወሚያ አድርጎ ያቀረበው ምስል ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነው ተባለ።
ሩሲያ ሠራሽ ኤስ-400 (S-400) የሚሳይል መቃወሚያ (ሚሳይል ዲፌንስ ሲስተም) ምሥልን የጁንታው ቡድን ያለው መሆኑን የሚያሳይ ምስል የህወሓት አባላትና ተከታዮቹ እያሠረጩ ይገኛሉ።
እነዚህ አካላት በፌስ ቡክ ገጾቻቸው የሩሲያ ሠራሽ እሳት ወይም አረር የሚተፋ መሣሪያ አገልግሎት ላይ አንደዋለ አድርገው ሲያሰራጩ መቆየታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ከእነዚህ የተሳሳቱ ምሥሎች ሥር “ይህ የምትመለከቱት ፎቶ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንኳ እኛ በክልል ደረጃ ያለን የጦር መሣሪያ እንደሌላት ነው” የሚል ጽሑፍ መስፈሩን ዘግቧል።
ጁንታው ራሱን ከአየር ጥቃት ለመከላከል እየተጠቀመበት መሆኑን ይፋዊ መግለጫ ከሰጠበት መሣሪያና ከመሣሪያው ፎቶ አጠገብ ደግሞ የትግራይ ልዩ ኃይል አባል የደንብ ልብስ የለበሰ የሚመስል ሰው ቆሞ እንዲታይ በማድረግ ሀሰተኛውን ነገር እውነት ለማስመሰል ጥረዋል።
ምስሉ ተቀናብሮ የተሠራ ሲሆን፣ ከመሣሪያው ፎቶ ጋር የትግራይ ልዩ ኃይል አባል ፎቶ ሆን ተብሎ ተጨምሮበት የታተመ ለመሆኑ አረጋግጫለሁ ያለው ቢቢሲ፤ ከአካባቢው ካሉ የምሥል ጥላዎች በተቃራኒ የቅንብር ፎቶዎቹ ጥላ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ማሳየቱ አንዱ ለፎቶ ሐሳዊነቱ ማሳያ ነው ብሏል።
“አንዳንዶቹ የአካባቢው ምሥሎችም ከሌላው ጨለም ያሉ ናቸው፤ የብርሃን ምጣኔያቸው ልዩነትም ይህን ያሳብቃል፤
በተጨማሪም በአንደኛው ፎቶ ላይ ወታደሩ ከከባቢያዊ ምሥሎች በተለየ የእርሱ ፎቶ ምጣኔ የተለጠጠ ሆኖ ይታያል” የሚለው የቢቢሲ የጥናት ውጤት፤ የፎቶው ምንጭ በተደረገ የኦንላይን ፍተሻ ከየት እንደሆነ ተደርሶበታል ሲልም ሀቁን ይፋ አድርጓል።
የሚሳይል መቃወሚያው በሩሲያ አስትራካን ክልል ወታደሮች ልምምድ ከሚያደርጉበት ሥፍራ የተወሰደ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በሩሲያ ቋንቋ የተደገፈው ቪዲዮም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ከመሆኑ ባሻገር፣ በመስከረም ወር የተወሰደው ይህ ተመሳሳይ ምሥል ተመሳሳይ የአየር መቃወሚያ አገልግሎት ላይ ሲውል በግልጽ ያሳያል።
ጁንታው አለኝ ያለው የአየር መቃወሚያ ኤ-400 (S-400) የአየር መቃወሚያ ሲስተም እጅግ ዘመናዊ የሚባል፣ ከምድር ወደ አየር ተምዘግዛጊ የሚሳይል ሲስተም ሲሆን፤ ከሩሲያ ሌላ ጥቂት የውጭ ሀገራት እጅ ውስጥ ካልሆነ በቀር በብዙ ሀገሮች እንደሌለና ኢትዮጵያም ይህንን መሣሪያ ውስጥ ከገዙት ሀገራት ዝርዝር ውስጥ እንደሌለች ቢቢሲ ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።

























