ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ነገ በአማራ ክልል ሠራዊቱ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክቶ የድጋፍ ሰልፍ እንደሚካሄድ ገለፁ።
“መላው የክልላችን ህዝብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ህገ ወጡ የትህነግ ቡድን ያደረሰውን ግፍ እና የሀገር ክህደት ወንጀል ለመላው ዓለም በምንችለው ሁሉ ለማሳወቅ የሰልፉ ተሳታፊ አንድንሆን ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉም በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ሰልፉ የሚካሄደው በክልላችን ባህር ዳር፣ ፍኖተ ሰላም፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ደብረ ታቦር ከተሞች ብቻ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤
ከእነዚህ ከተሞች ውጭ ባሉ የክልሉ ከተሞች ሰልፉ የማይካሄደው ህገ ወጡን የትህነግ ቡድን በህግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚደረገው ውጊያ ልዩ የጸጥታ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ እንደሆነም ይፋ አድርገዋል።
ነገ ኀዳር 03/2013 ጠዋት 2፡30 ተጀምሮ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቀው ሰልፍ፤ በተዋቀረው የሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ እና በጸጥታ ኃይል ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑም ተገልጿል።

























