ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) 38ኛ ልዩ ጉባኤ በወቅቱ ሊቀመንበር የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ሰብሳቢነት ተካሂዶ የተለያዮ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።
የሱዳን ሕዝብ እና መንግሥት ከሚመለከታቸው ወገኖች የጁባ የሰላም ስምምነት መፈረማቸውን ያደነቀው የኢጋድ ጉባዔ፤ የሱዳን መንግሥት አሜሪካ ከያዘቻቸው አሸባሪነት የሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ በመውጣቱም ደስታውን ገልጿል።
ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘ አገሪቱ በአዲስ መልክ የተዋቀረ ብሔራዊ የሽግግር አንድነት መንግሥት፣ የአስተዳደር መዋቅር መቋቋሙ የሚያስደስት ነው ያለው ጉባዔ፤ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ቴኒ ላይ የጉዞ እቀባ አለማድረጉንም አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስለተካሄደው ዘመቻ አስመልክቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቀረበ ማብራሪያ ያዳመጠው ኢጋድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ፣ የአገሪቱ መረጋጋት እና አንድነት ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ እርምጃው ተገቢ እንደነበርም አረጋግጧል።