ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኦሮሚያ ክልል በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ የፀጥታና የአስተዳደር አባላት ላይ ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ለፍትሕ ሊቀርቡ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።
ለሟቾች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለደረሰባቸው ጉዳት ተገቢ የሆነ ካሳ ሊሰጣቸው ይገባል ሲልም ነው ኮሚሽኑ ያሳሰበው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጉዳዮን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በኅዳር 22 ቀን 2014 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት አርዳ ጅላ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሕይወትና የአካል ጉዳት ስለመድረሱ በደረሰው ጥቆማ መሰረት፣ ከታኅሣሥ 7 እስከ ታኅሣሥ 12 ቀን 2014 በቦታው በመገኘትና ተጎጂዎችን፣ የአይን እማኞችን፣ የሟች ቤተሰቦችንና የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በማነጋገር ምርመራ ማካሄዱን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ኅዳር 21 ቀን 2014 ለሥራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አከባቢ ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ የነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በወረዳው ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሳለቸው ታውቋል።
ይህንን ተከትሎ ኅዳር 22 ቀን 2014 በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በፈንታሌ ወረዳ ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ሥሙ ዴዲቲ ካራ ከሚባል የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር የደረሱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የአይን እማኞች አስረድተዋል ሲል ገልጿል።
ኮሚሽኑ ጥር 25 ቀን 2014 ይፋ ያደረገው ሪፖርት ከእነዚህ በፀጥታ አባላት ቁጥጥር ሥር የዋሉ የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16 ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14ቱ ሰዎች በጥይት ተመተው እንደተገደሉ ጠቅሶ በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ በዝርዝር እንደተመለከተው በዚሁ ሁኔታ የከረዩ አባገዳ ከዲር ሀዋስን ጨምሮ በአጠቃላይ 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተመተው መገደላቸውንና 2 ሰዎች ደግሞ ወደ ጫካ በመሮጥ ማምለጣቸውን ምስክሮች ለኮሚሽኑ ማስረዳታቸውን ገልጿል።
የሟቾችን አስከሬን ለማንሳት ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ የሄዱ ሰዎች በቦታው በነበሩ ፖሊሶች እንዳያነሱ በመከልከላቸው፣ አስከሬኖቹ ለበርካታ ሰዓታት ሳይነሱ መቆየታቸውንና የፈነዱና በከፊል በዱር እንስሳ የተበሉ ጭምር እንደነበሩ አስከሬኖቹን ያነሱና የቀበሩ ሰዎች ገልጸዋል ብሏል።
በአስክሬኑ ጭንቅላት ላይ የመፈንከት፣ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ቁስል እና የድብደባ ምልክቶች ይታዩ እንደነበረ አስክሬኑን የተቀበሉ የቤተሰብ አባላት ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። የተቀሩት በእሰር ላይ የነበሩ የጅላ አባላት ከሳምንታት በኋላ ከእስር መለቀቃቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
በተጨማሪም፣ በግዳጅ ከተወሰዱት 23 የጅላ አባላት መካከል አንድ ሰው ሞጆ ከተማ በሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እያለ ሕይወቱ አልፎ ያለምንም ምርመራ አስክሬኑን ቤተሰቦቹ እንዲወስዱና እንዲቀበር መደረጉ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ተጨማሪ ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ መኖሩን በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ ማግኘቱን ገልጿል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎችን እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ አስታውሰው፣ “ስለ ጠቅላላ የነገሩ ሁኔታ እውነቱን በመግለጽ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ ላይ የተመሰረተ አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን የማኅበረሰቡን ሰላም እና ደኅንነት እንዲመለስ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

























