ወንጪ ሀይቅን በማልማት ሂደት ታጣቂው የሸኔ ኃይል እንቅፋት መሆኑ ተነገረ

ወንጪ ሀይቅን በማልማት ሂደት ታጣቂው የሸኔ ኃይል እንቅፋት መሆኑ ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የወንጪ ሀይቅ ልማት በሸኔ ታጣቂ ኃይል እና በካሳ ጥያቄዎች እየተፈተነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው “ወንጪ ላይ የጀመርነው ስራ ትንሽ ፈተና ገጥሞናል፤ ለመጨረስ ጥረት እየተደረገ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሮጀክቱ ላይ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ሲያስረዱም “ከፈተናዎቹ አንዱ ሸኔ ነው፤ እዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱትን ኩባንያዎች መዝረፍና ማቃጠል አንድ ሁለቴ ስላጋጠመን ስራው ትንሽ ተስተጓጉሏል” ብለዋል። ሌላኛው ፈተና የካሳ ጉዳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ካሳን በሚመለከት በየቦታው በህዝብ መዋጮ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ካሳ መጠየቅ እየተለመደ ስለመጣ በተወሰነ ደረጃ ጉዳት አለው” ብለዋል።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በደቡብ ክልል ኮይሻ፣ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮምያ ክልል ወንጪን ለማልማት የታቀደ ሲሆን እስከ ትላንት የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ 4.2 ቢልየን ብር ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ እንደተሰበሰበ ተዘግቧል።

አብያታና ሻላ ሀይቅ ማልማትን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አካባቢው ከመልማት ባለፈ ከተማ መገንባት የሚያስችል ቦታ አለው፤ የተጀመሩት ሲያልቁ በቀጣይ ይታሰበታል” ብለዋል። ከወንጪ በስተቀር የኮይሻ እና የጎርጎራ ፕሮጀክቶች በያዝነው ዓመት ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

LEAVE A REPLY