ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደታቸው አካል ጉዳተኞችን ያገናዘበ ካልሆነ የእውቅና ፈቃደቸው እንደሚሰረዝ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ለሁሉም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፣ ተገቢውን ማስተካከያ ባላደረጉ ተቋማት ላይ የእውቅና ፈቃድ እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስባለሁብሏል።
ባለስልጣኑ ሁሉም ተቋማት የማስተማሪያ ህንፃ፣ ከባቢያዊ ሁኔታና የማስተማሪያ ግብዓት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆን ማሻሻያ እንዲያደርጉ የሶስት ወራት ጊዜ ሰጥቷል።
ከዚህ በኋላ የእውቅና ፈቃድ መስጠት እና እድሳት የሚደረገው በእዚህ አግባብ ነው ያለው የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የማሻሻያ የመጨረሻ የጊዜ ገደብ መሆኑን አስታውቋል።
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ በሚያገኙበት እና በሚያድሱበት ወቅት የተለያዩ ከባቢያዊም ሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታቸው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆን እንዳለባቸው በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 ላይ ተደንግጓል።

























