ዞረሽ ዞረሽ ! ተሽከርክረሽ – ተሽኮርምመሽ፤
ተሽቀርቅረሽ ! ተሞናሙነሽ – ተኳኩለሽ፤
ቀናት ቆጥረሽ_ ወራት አዝለሽ – ዓመት ሞልተሽ፤
እኛን እረስተሽ_ ካለው ውለሽ – ካለው ቀብጠሽ፤
እንዳልነበርን – እንደሌለን ፤
አፈር ትቢያ – ጭቃ ለብሰን፤
ምናምንቴ – ከንቱ ሆነን፤
ውልብ ላንል – በትውስታሽ፤
ከምናብሽ_ ከመዝገብሽ – እኛን ፍቀሽ፤
እነ አባባ – እነ እማማን፤
ወንድም ጋሼ – እ’ት ዓለምን፤
ዘመድ አዝማድ – ጎረቤቱን፤
ሁሉን ትተሽ – ሁሉን ረስተሽ፤
ቀን አስልተሽ – ወራት ቆጥረሽ ፤
ዓመት ሞልተሽ – ዘመን አዝለሽ፤
እንቁጣጣሽ ምን አመጣሽ ? – ለምን መጣሽ ?!
ምን ትሠሪ ? – ምን ትፈጥሪ ?
ምን ታወሪ ? – ምን ትነግሪ ?
እኮ ለምን ?! ተናገሪ !!
ለወገኔ ለተራበው – በደል ጥቃት ላባዘነው፤
ኑሮ ጨሶ ለሚያጨሰው – በ’ንባዎቹ ለሚያጠቅሰው፤
ጠኔ ጥሎት ለወደቀው – በጎዳና ለሚተኛው
ለእኔ ብጤ_ ለሷ ብጤ _ ለኛ ብጤው፤
እንቁጣጣሽ – ምን አመጣሽ ?!
ተጠየቂ እስቲ እንስማሽ !!