/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ለዶ/ር አብይ አህመድ የድጋፍ ደብዳቤ ፃፈ።ቴዲ አፍሮ ዛሬ ጠዋት በፌስ ቡክ ገፁ በለቀቀው መልዕክት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድንና ባልደረቦቻቸውን አጋርነት የምናሳይበት ጊዜ ላይ ነን ብሏል።
ቴዲ አፍሮ ባለፉት በርካታ ዓመታት ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ፍቅርና አንድነት አብዝቶ በማቀንቀኑ በስርዓቱ ባለስልጣናት እንደ ጠላት ሲቆጠር ቆይቷል። በዚህም ታስሯል፣ በሀገሩ እንዳይሰራ ተደርጓል፣ በተደጋጋሚ የጉዞ ማዕቀብ ሲደረግበትና ሌሎች በርካታ በደሎች ሲደርሱበት መቆየቱ ይታወቃል።
የቴዲ አፍሮ ሙሉ መልዕክት የሚከተለውን ይመስላል፦
__
ለተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች በቅድሚያ የከበረ ሠላምታዬን እያቀረብኩኝ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን በማፈንና ብሄራዊ ስሜትን በማደብዘዝ አገራችንን ለአደጋ ከዳረገው ስርአት ለመላቀቅና በምትኩ አንድነትን ፥ መተባበርን እና ፍትህን ለማስፈን ከምንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ለማዳን በተለያየ አቅጣጫ ብዙ እንቅስቃሴዎች በሚካሄድበት በአሁኑ ወቅት፦
በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊነትን እና ይቅር መባባልን ይዘው ብቅ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድና ባልደረቦቻቸው አጭር በሚባል የስልጣን ቆይታቸው ለወሰዶቸው በጎ እርምጃዎች እና ላሳዩን ኢትዮጵያዊ አለኝታነት አጋርነትን ማሳየት እና ከጎናቸው መቆም ጊዜው የሚጠይቀው አስፈላጊ ተግባር መሆኑን ስገልፅ በሚደረጉት የድጋፍ እንቅስቃሴዎች ላይ በሥራ አጋጣሚ በቦታው ባልገኝም በመንፈስ አብሬያችሁ መሆኔን ሳረጋግጥ በታላቅ ኢትዮጵያዊ ስሜት ነው።
ድል ለኢትዮጵያዊነት
ፍቅር ያሸንፋል
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)