ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ ሐምሌ 13/2010 ዓ.ም የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ መግለጫ ሰጥቷል። ከተነሱት ነጥቦች መካከልም፦
1~ የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ድንበር ተሻግሮ እየገባ በአማራ ገበሬዎች ላይ እያደረገውን ያለ ወረራና ጥቃት በተመለከተ፤ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የአገርን ሉዐላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ፣ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ወራራ በዘላቂነት መፍትሔ እንዲበጅለት፤
.2~በኦሮሚያና በሶማሌ እንዲሁም በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ እና መፈናቀልን ከዕለት ወደ ዕለት ችግሩ እየከፋ መምጣቱ ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚያሳስበው፤ መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ወደ አካባቢው የመከላከያ ሃይልና የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ በመግባት ችግሩ እንዲፈታ ትዕዛዝ መስጠቱ የሚበረታታ ቢሆንም ሠራዊቱ ፍፁም ኃላፊነት በተሞላው መልኩ እንዲንቀሳቀሱና ግጭቶችን በቁጥጥር ስር እንዲያውል፤
3~ የራያ ሕዝብ ህገመንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲገባ፤ የትግራይ ክልላዊ መንግስት እየወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ በማውገዝ የፌደራል መንግሥት ሁኔታውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለው ሰማያዊ ፓርቲ ለመንግስት በማሳሰቡ፤
4~ የደህንነት መዋቅር ማስተካከያ ጋር በተያያዘ ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የተቋሙ ኃላፊ መልዕክት፤ በየደረጃው ያሉ የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ሙያተኞች ከየትኛውም የፓርቲ ፖለቲካ የፀዱና ሕዝብን በታማኝነትና በቅንነት የሚያገለግሉ መሆን እንዳለባቸው ያስተላለፉትን መልዕክት ሰማያዊ ፓርቲ የሚደግፈውና ለተግባራዊነቱም የድርሻውን እንደሚወጣ፤
5~ የአምባሳዶርነት ሹመት አስመልክቶ፤ በሕዝብ ዘንድ የተወገዙ፣ ብቃት ማነስ የታየባቸው፣ ተደጋጋሚ ጥፋቶችን የፈጸሙ በአለም አቀፍ መድረክ አገርን የመወከል ብቃትም ሆነ ሞራል ሣይኖራቸው ከሕዝብ ፊት ዞር ለማድረግ ብቻ የአምባሳዶርነት ሹመት መስጠት ጉዳቱ ስለሚያመዝን መንግስት ጉዳዮን እንዲመለከተው ሰማያዊ ፓርቲ አሳስቧል።