መንግስት የኮንዶሚኒዮም ቤት ተመዝጋቢዎች ላይ የፈጸመው የውል ጥሰት እና ያደረሰው ኪሳራ! |...

መንግስት የኮንዶሚኒዮም ቤት ተመዝጋቢዎች ላይ የፈጸመው የውል ጥሰት እና ያደረሰው ኪሳራ! | በሙሉጌታ በላይ

መንግስት/የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ40/60 የኮንዶሚኒዮም ቤት ተመዝጋቢዎች እና በመሬት ባለይዞታዎች ላይ የፈጸመው የውል ጥሰት እና ያደረሰው ኪሳራ!

መግቢያ

መንግስት የህዝቦችን ሉዓላዊ ስልጣን የመንግስት እና የህዝብ የቃል-ኪዳን ሰነድ(ውል) በመባል በሚታወቀው ህገመንግስት አማካኝነት ሲወስድ በዚህ ውል አማካኝንት የተቀበላቸውን የዜጎች መብት የማክበር እና የማስከበር በተለየም የንብረት መብታቸውን ሊያከብር እና ከሌሎች ሰዎች ጥቃት ወይም ጉዳት ለመከላከል ነው፡፡ መንግስት በህግ የተጣለበትን ለዜጎች መጠለያ የማቅረብ ግዴታ እንደ አንድ አዳጊ ሀገር በራሱ ብቻ ሊወጣው የሚችለው ባለመሆኑ በጉዳዩ ላይ ዜጎችን ተሳታፊ በድረግ የቁጠባ ባህልን በሚያበረታታ መልክ ገንዝብ ለቆጠቡ ዜጎች ቤት የመሰራት ግዴታ ውስጥ በ2005 ዓ/ም ገብቷል፡፡ በዚህም መነሻነት በርካታ ዶላር እና ብር ከበርካታ ዜጎች ሰብስቧል፡፡

ይህ ፅሁፍም መንግስት በዚህ ግዴታ ውስጥ ያልተወጣቸውን ግዴታዎቹን ብሎም ውሉን ግልፅ በሚባል ሁኔታ የጣሰባቸውን ሁኔታዎች ከህግ አንፃር ለመመርመር ይሞክራል በዚህም አንባቢን ላለማሰልቸት የህጉን መሰረተ ሃሳብ እንጅ ብዛት ያላቸውን የህግ ድንጋጌዎች ከመጥቀስ ተቆጥቧል፡፡

መንግስት (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ከቤት ተመዝጋቢዎቹ ጋር የገባው ውል ይዘት

በ2005 ዓ/ም መንግስት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ከቤት ተመዝጋቢዎቹ ጋር ባደረገው ውል ዜጎች ለአምስት ተከታታይ አመታት እንዲገነባላቸው የሚፈልጉትን ቤት ጠቅላላ ዋጋ 40 በመቶ እንዲቆጥቡ መንግስትም ለዜጎቹ በውሉ ላይ በተገለጸው መሰረት የአዲስ አበባ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ስርቶ የሚያስረክበውን ቤቶች እንደሚያስረክብ ነገርግን በውሉ አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 6 መሰረት የቤት ድልድሉን ቅደም ተከተል በተመለከተ በደንበኞች የቁጠባ መጠን ልክ፤ በአመዘጋገብ ቅደም ተከተል እና በእጣ መሆኑን በዚህ መሰረትም ለብድር ብቁ የሆኑ እና ከፍተኛ ገንዘብ የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች ቅድሚያ እድል ይኖራቸዋል በማለት በውል እና በሚዲያ መግለጫዎች ለህዝብ ማረጋገጫ ሰጥቶ በርካታ ገንዘብ ሰብስቧል፡፡

ከዚህ መሰረታዊ የውሉ ይዘት አኳያ የተጣሱ የውል ጉዳዮች

1. በውሉ ግዴታ መሰረት አስቀድሞ የበለጠ ለቆጠበው ቤቶቹን አለማስተላለፍ

ውል በተዋዋይ ወገኖች ዘንድ ህግ ነው፡፡ ላቲኖቹ (pacta sunt servanda) ይላሉ ሰው በቃሉ ይታሰራል እንደ ማለት፡፡ መንግስት ከዜጎቹ ጋር በጅምላ ባደረገው በዚህ ውል ይበልጥ የቆጠበ ይበልጥ እንደሚጠቀም እንዲያውም ሙሉ ከፍያውን አስቀድሞ ለከፈለ ሰው ቅድሚያ እንደሚሰጥ በውል ግዴታ ከመግባት አልፎ በየሚዲያዎቹ ቅስቀሳ እና መግልጫ ሲሰጥ እንደነበረ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡ለዚሁ ቃሉ ታማኝ መሆኑን በሚያሳይ መልኩም በመጀመሪያው ዙር የ40/60 የእጣ ድልድል ወቅት ቀድመው 100 በ 100 ለቆጠቡት ከ 1200 ቤቶች በላይ ወደ ተመዝጋቢዎች አስተላልፏል፡፡ ነገርን በዚህ ኛው ዙር አስቀድሞ ካደረገው በተቃራኒው ሁሉም የቤቱን ጥቅላላ ዋጋ 40 በመቶ የቆጠቡ በሙሉ እጣ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጓል ይህ በአራት መሰረታዊ ጉዳዮች ቃልን ማበል ህግን መጣስ ብሎም በዜጎች መካከል አድሎ መፈፀም ነው፡፡

አታላይነት ወይም እምነት ማጉደል

አንደኛ መንግስት በውል የገባውን ግዴታ በግልፅ እና በግድፈት በመጣሱ በውል እና በሚዲያ መግለጫ ይበልጥ ከቆጠብክ ይበልጥ ትጠቀማለህ በሚል የገባውን ግዴታ በመጣስ ህዝብ እንዳታለለ የሚያስቆጥር ተግባር ፈፅሟዋል፡፡ የዚህ ድርጊት ጉዳትም በተመዝጋቢዎች ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን ዜጎች በሙሉ መንግስት ቃሉን የሚበላ ፤ የማይታመን ፤ ዋሾ እንደሆነ እንዲገምቱ በማድረግ ወደፊት ለህዝብ የሚገባቸውን ቃሎች እንዳያምኑ በማድረግ በመንግስ በኩል የሚጀመሩ የህዝብን ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ዜጎች ተጠራጣሪ እንዲሆኑ የማድረግ ውጤት አለው፡፡ እንዲያውም ይህው ፕሮጀክት በሚዲያ በተነገረበት ሰአት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ዜጎች መንግስት ገንዘብ ቸግሮት እንጅ በርግጥ ለዜጋው አስቦ አይደልም በማለት ፕሮጀክቱን የተጠራጠሩ እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡ መንግስት ቤቶቹ እጅግ ዘግይተው ከተመዝጋቢው ቁጥር አኳያ እጅግ አነስተኛ በሆነ መጠን መስራቱ ሳያንስ ይህኑም ከውል ወጭ እና ቃል ከገባው በተቃራኒ መፈጸሙ ጥርጣሬውን የሚያጎላ እና የወደፊት ፕሮጀክቶች እጣፋንታ ላይም አንድ ተግዳሮት መሆኑ የሚቀር አይደልም፡፡

በሌላ ሰው ገንዘብ ያለአግባብ መበልፀግ

አንድ ዜጋ ፈቅዶ ፤ ወዶ ወይም በህግ በግልፅ በተደነገገ ልዩ ሁኔታ ካልሆነ በቀር የሱ በሆነ ገንዘብ ወይም ንብረት መንግስትም ሆነ ሌላ ዜጋ ያለአግባብ መጠቀም አይችሉም፡፡ በዚህ የ40/60 ፕሮጀክትም መንግስት 100 ፕርሰንት የቆጠበ ሰው እንደሚበረታታ እና ቅድሚያ እድል እንደሚያገኝ ከገለጸ በኋላ ቁጥራቸው ከ 17 ሽህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቆጠቡት 100 ፐርሰንት እና ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ሰዎች በቆጠቡት ከ40 በመቶ በላይ ገንዘብ መንግስት በዶላር እና በብር ገንዘቡን ከሰበሰበ በኋላ የሰራቸውን ቤቶች ያነሰ ቁጠባ ያደረጉ ሰዎች በእጣ ስም ያለአግባብ እንዲጠቀሙባቸው አድርጓል፡፡ ይህን ቃሉን ማጠፉ ሁሉንም ገንዘብ ባንክ ገቢ ያደረጉ ብሎም በርካታ ገንዘብ የቆጠቡ ሰዎች ባዋጡት ወይም በቆጠቡት ገንዝብ ሌሎች ያነሰ ገንዘብ ያወጡ ሰዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ አንድን ሰው በግዳጅ ራሱን ሳይጠቅም ሌላ ሰው እንዲጠቅም ማስገደድ ተብሎ የሚቆጠር ህገ-ወጥ ተግባር ነው፡፡

ይህ በመሆኑ አንድ ዜጋ የራሱ ባልሆነ ሌሎች ሰዎች ባዋጡት በደከሙበት ገንዘብ እንዲጠቀም በማድረግ የዜጎቹ የንብረት መብት ከህግ ወጭ ያለአግባብ እንዲነካ ሆኗል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከ 40 በመቶ በላይ ያለውን ገንዘባቸውን ለፈለጉት ለሌላ ጉዳይ ማዋል እየቻሉ መንግስት በገባው ቃል እና ግዴታ በመተማመን ገንዘባቸውን ላለፉት አምስት አመታት በባንክ ሳይወጣ እና ሳይንቀሳቀስ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ገንዘብ ውሉ በሚያዘው እና በሚፈቅደው ልክ ሳያስቀምጡ ገና ወደፊት መንግስት ከታክስ ከፋዮ ህዝብ ከሰበሰበው ገንዘብ ላይ በሚያበድራቸው ገንዘብ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል(ይህ ተግባር በዚህ ፅሁፍ አገባቡ በራሱ ስህተት ነው ማለት ሳይሆን ስህተት የሚሆነው በውሉ መሰረት በተመዘገቡ ሰዎች መካከል ብቻ ነው) በዚህ ገንዘብ ሌሎች ሰዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ለዜጎች በህግ የተከበረላቸውን የንብረት መብት መጣስ ነው በዚህ ረገድን መንግስት ለዜጎች ያላበትም የንብረት መብት የማስጠበቅ ግዴታ አልተወጣም መብታቸውን በመጣስ ተግባርም ተሳትፏል፡፡

አድሎ እና የእኩልነት መርህ መጣስ

ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸው የሃገሪቱ የበላይ በሆነው ህግ የተደነገገ የትም መቼም ሊጣስ የማይገባው የማይገደብ መብት ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት አስቀድሞ በገባው ውል እና በሰጠው መግልጫ የጨዋታ ህጉን ካሳወቀ በኋላ የጫዋታ ህጉን ተከትለው ወደ ጨዋታው በገቡ ዜጎች መካከል ህጉን በመቀየር አድሎ በመፈጸም ህገመንግስታዊ ጥሰት ፈፅሟል፡፡ እዚህ ጋር እኩልነት የተጣሰው እንዴት ነው የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ይህውም ዜጎች አስቀድሞ በወጣ ህግ መሰረት ወደ ጨዋታው ከገቡ በኋላ የጨዋታው ህግ ሲቀየር የጨዋታውን ህግ አምነው የገቡ እና በጨዋታው ህግ መሰረት የተሸላ አፈጻጸም ያሳዩ ዜጎች እንዲጎዱ በጫዋታው ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩት ደግሞ ያለአግባብ እንዲበለፅጉ ያደርጋል፡፡

በዚህም የሚበረታታው ቁጠባ ሳይሆን እድል ድካም ሳይሆን እጣ ፋንታ ይሆናል፡፡ በዚህም የእኩልነት መርህ ይጣሳል፡፡ በተለይም አስቀድሞ በነበረው ዙር ተመዝጋቢዎች በጨዋታው ህግ መሰረት ቤቶቹን ከተረከቡ በኃላ ይህ የጨዋታ ህግ መቀየሩ አስቀድመው በቀድሞው የጨዋታ ህግ መሰረት ቤት በወሰዱ እና ከነሱ በኃላ ባሉ ዜጎች መካከል ልዩነት እንዲፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ የእኩልነትን መርህን ጥሷል፡፡

ግልፅነት እና ተጠያቂነት

መንግስት ማኛውንም የመንግስት ስራ በሚከውንበት ግዜ ስራውን በግልፅነት እና በተጠያቂነት መሰራት ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ከተያዘው ጉዳይ አኳያ መንግስት ግልፅ ነው የሚባለው ወደ ስራ ከመግባቱ አስቀድሞ የጨዋታውን ህግ በማሳወቅ ለህዝብ ይፋ በማድረግ ረገድ ያለውን ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን በዚህ ረገድ መንግስት የጨዋታውን ህግ ግልፅ መድረጉ የሚካድ ባለመሆኑ ትችቱ በዚህ በኩል የሚነካው አይሆንም፡፡ ችግሩ ይህን ግልፅ ያደረገውን ህግ እና አሰራር መልሶ በድንገተኛ ውሳኔ ሲቀይረው ነው፡፡ አንዳንዶችም በዚህ ረገድ በግልፅ ተናግሮ ቃሉን ከሚያጠፍ መንግስት ይልቅ አስቀድሞ ግልፅ ያልሆነ መንግስት ይሻላል በማለት ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ መንግስት የገባውን ቃል በማጠፍ ግልፅነቱን ህዝብን ማባበያ በማድረግ ከህዝብ ገንዘብ ከሰበሰበ ብኃላ ቃሉን ማጠፉ ቃሉን አምነው ገንዘባቸውን በሰጡ ዜጎች ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው፡፡ በዚህም ይህን ቃል በማመን ገንዘባቸውን ለሰጡ ዜጎች ድርጊት ሃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ተግባርም በሌሎች የመንግስት ስራዎች ላይ የሚደገም ከሆነ የህዝብን አመኔታ የሚሸርሽር ግልፅ የመልካም አስተዳደር ጥፋት ነው፡፡

ስለቤቶቹ መግልጫ መስጠት ሆነ ም ቤቶቹን የማስረከብ ስራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንጅ የቤቶች ልማት ስራ ስላለመሆኑ

መንግስት ከዜጎቹ ጋር ግዴታ የገባውም ሆነ በአደባባይ መግለጫ የሰጠው ውሉ የተደረገውም ሆነ በቀደመው ዙር ስራዎች የተከናወኑት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መሆኑ አከራካሪ አይደልም በዚህኛው ዙር ከዜጎች ጋር ግዴታ የገባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያለ መግለጫ የሰጠው ወሉን የቀየረውም ሆነ በቤቶቹ ላይ ውሳኔ ያስተላለፈው የቤቶች ልማት መሆኑ ከውል ወጭ ሲሆን ግዴታ የገባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የደንበኞቹን መብት እና ጥቅም አሳልፎ የሰጠ መሆኑን የሚያሳይ አጋጣሚ ነው፡፡

ቤቶቹ በውሉ መሰረት በስፋት እና በይዘት ደረጃ ያልተረሟሉ መሆናቸው ሌላ የውል ጥሰት ስለመሆኑ

በቀደመው ዙርም ሆነ በዚህኛው ዙር ለዜጎች ተስርተው ይሰጣሉ የተባሉ ቤቶች የካሬ ሜትር ስፋት ዲዛይንም ሆነ የክፍሎች ብዛት ከውል ውጭ እንደነበረ አስቀድመው ከተላለፉት ቤቶችም ሆነ አሁን ለመተላለፍ በሂደት ላይ ባሉት ቤቶች በግልፅ ታይቷል፡፡ (በውሉ ላይ የሌላ 4 መኝታ ቤት መሰራቱን ልብ ይሏል) በዚህ መንገድም እንደ ውሉ ሳይፈፅም በውሉ መሰረት ሳይሆን በባለሰልጣናት ውሳኔ እና ትእዛዝ ስራውን እንዳሽው መከወኑ ግልፅ የውል ጥሰት ሲሆን በዚህም ዜጎች አስቀድመው ከተዋዋሉት ከፈለጉት እና ከሚፈልጉት ውጭ መንግስት በራሱ መንገድ መስራቱን ያሳያል፡፡

ቤቶቹ ስለተገነቡበት ይዞታ እና ስለባለይዞታዎቹ መብት

መንግስት የአንድ ዜጋን የመጠለያ መብት ሲያከብር የሌላውን ሰው የኢኮኖሚ መብት እንዳይነካ መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡ በዚህ መጠንቀቅ ውስጥ ጉዳት የሚደረስ ከሆነ ደግሞ ተገቢውን ካሳ መክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ምንም እንኳ በህገ መንግስቱ መሬት የብሄር ብሄረሰቦች የጋራ ንብረት ቢሆንም በመሬቱ ላይ መብት ያላቸው ግለሰቦች ግን ተገቢውን ካሳ የማግኘት መብታቸው የተከበረ ነው፡፡ ይሁን እንጅ መንግስት የወሰዳቸውን ይዞታዎች በማይመጥን ሁኔታ ካሳ ይሰጥ የነበረ በመሆኑ በቦታው ላይ ሰፍረው የነበሩ የከተማው ኗሪዎችና ገበሬዎች ለበርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ እንደውም መንግስት በዚህ ይዞታን የማስለቀቅ ተግባር ንግድ በሚመስል ደረጃ ለባለይዞታዎቹ የሚከፍለው ካሳ እና ይዞታውን በሊዝ የሚተምንበት የዋጋ ልዩነት መንግስት በመሬት ንግድ የተሰማራ መሆኑን የሚያሳይ ነበር፡፡ በዚህ ድርጊትም ምክንያት የቤት ተመዝጋቢዎቹንም ሆነ ለቤቶቹ ሲባል የተፈናቀሉ ዜጎችን መብት ማስከበር አልቻልም፡፡ መንግስት አንድ ህዝባዊ ፕሮጀክት በሚጀምርበት ግዜ ፕሮጀክቱ ለህዝብ የሚሰጠውን ጥቅም ፕሮጀክቱ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ማመዛዘን የሚገባው ሲሆን በዚህም ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ወይም ለማካካስ ተገቢውን ካሳ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡

የመፍትሄ ሃሳቦች

1. መንንግስት በድጋሜ ውሉን ባከበረ እና ቃሉን በሚመጥን ሁኔታ እጣውን ሊያወጣ ይገባዋል፡፡

2. ይህ ማድረግ የማይችል ከሆነ በደል የፈጸመባቸውን ዜጎች ይቅርታ መጠየቅ እና በዚህ ድርጊት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ካሳ የመክፈል ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡

3. አነስተኛ ካሳ ተክፍሏቸው ይዞታቸው ለተወሰደባቸው ሰዎች የደረሰባቸውን ጉዳት የሚመጥን ካሳ ወይም አማራጭ እርምጃዎችን ለምሳሌ ቤት ሰርቶ መስጠትን የመሳሰሉ ተግባሮችን ሊፈፅም ይገባዋል፡፡

ይህን የማያደርግ ከሆነ ግን እንደማንኛውም በውል ግዴታ እንደገባ ግለሰብ ሁሉ በህግ ተጠያቂ ይሆናል፡፡

LEAVE A REPLY