እናቱ እናቴ – ልደትሽ ልደቴ ! /በመላኩ አላምረው/

እናቱ እናቴ – ልደትሽ ልደቴ ! /በመላኩ አላምረው/

ለእናትነት ክብር – እርሱ ከመረጠሽ
በዮሐንስ በኩል – ለእኔ ከተሰጠሽ
እኔም እርሱን ጌታ – ብዬ ከተቀበልሁ
ማዳኑን አምኜ – በሕጉ ስር ከዋልሁ
እናቱን እናቴ – ብየ ለመቀበል…
ጥያቄ ልደርድር? ለምን? እንዴት? ልበል?
+ + +
ልጅሽ በምድር ላይ – ሥጋሽን በመልበስ
አዳምን ሊያድነው – ለእኛም ጽድቅን ሊያወርስ
የረገጠው መሬት – የቆመበት ቦታ
ከቤተልሄም ዋሻ – እስከ ጎለጎታ
ቅዱስ ከተባለ – ውሎ ያደረበት
ልዩ ክብር ካለው – የተሰቀለበት…
አንችማ እናቱ – ማህፀን ዓለሙ
የሰውነት ልኩ – ሥጋውና ደሙ
እንዴት አትከብሪ!? እንዴት አትቀደሽ!?
እንዴት አትወደጅ!? እንዴት አትወደሽ!?
+ + +
እንኳንስ ለእኔና…
ለእርሱም ለጌታችን – ፈጣሪ ለሆነ
እናቱ መባልሽ – ይህ እውነት ከሆነ
እናቴ መሆንሽ – እንዴት አልታመነ???
+ + +
በሥጋ ያይደለ – በረቀቀ መንፈስ
እናቴ ሆነሽኝ – ያንችን ክብር ብወርስ
ይሄንን መታደል – እንዴት እገፋለሁ?
እናቱ እናቴ ነሽ! – ተቀብየሻለሁ!!!
+ + +
ፈጣሪን ልትወልጅው – አምላክን ልታ’ዥው
ሰማይና ምድር የማይወስኑትን – በእቅፍሽ ልትይዥው
ከድንግልና ጡት – ወተት ልታጠቢው
የዓለሙን መጋቢ…
ከደኃ ማጀትሽ – ሲራብ ልትመግቢው
እናት አባትሽን – ከእስር ልታስፈቺ
የክፋትን አባት – በፍቅር ልትረቺ
ከሀና ከኢያቄም – የተወለድሽ አንቺ
እናትና ድንግል – ንግሥትና አገልጋይ
ሰማየ ሰማያት – ጽርሐ አርያም ሆይ!
የአንቺ ግሩም ልደት – ለእኔም ነው ልደቴ
የጥምቀት መሥራቹ – ልጅሽ ነው አባቴ
ዳግም የተወለድሁ – ከውኃና መንፈስ
ባንቺ መወለድ ነው – የአዳም ተስፋው ሲደርስ
ሕይወት የሆነልን – የልጅሽ ሥጋና ደም
ከአንቺው ነው የነሳው – ከላይ አልወረደም
ዝም ማለት ያልቻልኩት – ለዚህ ነው ድፍረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እና ነሽ – ልደትሽ ልደቴ
+ + +
+
ቅድስተ ቅዱሳን – ንጽሒተ ንጹሐን
ማሕጸኑ ለጽድቅ – እናቱ ለብርሃን
ሰማየ ሰማያት – ታናሽ ብላቴና
ከእያቄም ወሀና – ተወለደሻልና
ዓለም ብርሃን አየ – ውስጥሽ ባለው ፀሐይ
አዳም ቀና አለ – ተስፋ ብርሃኑን ሊያይ
ፍጥረታት በሙሉ – ከሰማይ ከምድር
በደስታ ተመሉ – ልደትሽ ሲነገር
ተወለደሻልና – የፀሐይ እናቱ
ጽርሃሐ-አርያም ሆንሽ – ብላቴናይቱ !
+ + +
+
(፡›አበው ስለክብርሽ – ቃላት አጠራቸው
ስለ ደም ግባትሽ – ምሳሌ ጠፋቸው
እኔ ግን ደፋሩ – እዘባርቃለሁ
ባልበሰለ ብዕር – ቃላት እመርጣለሁ
በተንሸዋረረ ዓይን – ክብርሽን አያለሁ
ምልጃሽን እያሰብሁ – በተስፋ እኖራለሁ‹፡)
+ + +
የብርሃን እናቱ – የፀሐይ ምሥራቁ
የአዳም ሙሉ ተስፋ – የሰይጣን መብረቁ
ስለ አንቺ መወለድ – ዓለም ተፈጠረ
ስለ አንቺ መወለድ – የሰው ልጅ ከበረ
አዳምና ዘሩ – በኃጢአት ቢረክሱ
በአንቺ መወለድ – ግን በክብር ነገሡ
በአንቺ ልዩ ልደት – አዳም አምላክ ሆነ
በአንቺ ልዩ ልደት – ክብራችን ገነነ
በአንቺ ልዩ ልደት – ዲያብሎስ ታሰረ
በአንቺ ልዩ ልደት – ባሪያ መሆን ቀረ
እኔም ደፋር ሆንኩኝ – ፍርሃት ተሰወረ
ባዶው አዕምሮዬ – ክብርሽን ነገረ፡፡
+ + +
ሰማይና ምድር – ልደትሽን ሲያከብሩ
ሊቃውንት ሲቀኙ – መላእክት ሲዘምሩ
ክብርሽን ተማምነው – በምልጃሽ ያደሩ
በምህረት ቃል ኪዳን – ለክብር ሲጠሩ
እንደልጅነቴ ለእኔም – እንዲደርሰኝ
እንባሽን አስታውሶ – ልጅሽ እንዲምረኝ
ዝም ማለት ያልቻልኩት – ለዚህ ነው ድፍረቴ
የአንቺ መወለድ ነው – የጽድቅ መሠረቴ
ልጅሽ ሕይወቴ ነው !
እናቱ እናቴ ነሽ – ልደትሽ ልደቴ፡፡
+ + +

.
(((‹‹ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ።›› (መኃልዬ 4፥7)
ይህ በፎቶ የምታዩት ቦታ የሚገኘው በቤይሩት ሊባኖስ ሲሆን በግዙፌ የሊባኖስ ተራራ ላይ የተሠራ የእመቤታችን ሐውልት ነው፡፡ የቦታው ልዩ ስም ደግሞ ‹ሐሪሳ› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ሐውልቷ የቆመበት ተራራ እመቤታችን የተወለደችበት ነው፡፡ ሁሉም ይስማማበታል፡፡ በሊባኖስ ከግንቦት አንድ ጀምሮ እስከ ሰላሳ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑም ሆነ ሌላው አማኝ በዚህ ቦታ በመገኘት ይጎበኘዋል:: በተለይም በግንቦት 1 ቀን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ወደ አደባባዩ በመውጣት በዓሉን አድምቆት ይውላል፡፡)))
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
በዓለ ልድት በሰላም አደረሰን – አደረሳችሁ !!!

LEAVE A REPLY