ጌታ ሆይ ! /መላኩ አላምረው/

ጌታ ሆይ ! /መላኩ አላምረው/

ዳግመኛ መምጣትህ እንደማይቀር ባውቅም
የመምጣትህን ቀን አሁን አልናፍቅም

ከዕርገትህ በኋላ ዳግም ስትመጣ
ጻድቅ መንግሥት ሊወርስ ኃጥዕ ግን ሊቀጣ
እንደሆነ አውቃለሁ ዘላለም ለመፍረድ
እና አሁን መጥተህ እኔ ሲኦል ልውረድ ?
እባክህ አምላኬ ትንሽ ዘግይ አትውረድ

“ቶሎ ና” ሚሉህን ፈጽሞ እንዳትሰማ
እነርሱ ስለ’ኔ ምንም አያውቁማ
የአንተን ቶሎ መምጣት ሚናፍቁ ሁሉ
ባክህ ልብ ስጣቸው እስኪ ያስተውሉ
ስለ’ነርሱን እንጅ ስለሰው ያውቃሉ ?
በፍጹም አያውቁም ! ሚያቁማ ቢሆኑ
ለእኔ ቢጤ ነፍሳት ራርተው ባዘኑ
“ጊዜ ለንሰሐ” ብለው በለመኑ…

የአንተ ዳግም መምጣት…
ልክ እንደልደትህ ኃጢአትን ለማጥፋት
አይደለም ለመስቀል አይደለም ለመሞት
ለመፍረድ ነው እንጅ ይግባኝ በሌለው ቃል
የእኔን ሥራ ደግሞ ልቦናዬ ያውቃል
እናም ካላስቸገርሁ…
ለሠራሁት ኃጢአት ዘንድሮና አምና
ንሰሐ ለመግባት…. አስቤአለሁና
የሆኑ ዓመታት… ትንሽ ዘግይተህ ና

ግን አደራ አምላኬ !
ዕድሜን በቸርነት ከመስጠት ባሻገር
ይህን ክፉ ልቤን ለንሰሐ ስበር

ልቡ ተጸጽቶ ያልተሰበረ ሰው
ምንም ለንሰሐ ሺህ ዓመት ቢሰጠው
ያው ያባክነዋል ፊት እንዳመለጠው ።
።።።።።።።።።።

LEAVE A REPLY