በዚህች ምድር ላይ የቆየው ለ40 ዓመታት ብቻ ነው፤ ከ1970 ዓ/ም እስከ ታህሳስ 2010 ዓ/ም። ተስፋዋና ፍሬዋ ለልጆቿ እንደ መንግሥተ ሠማያት መንፈስ ብቻ በሆነው ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ከተማ በመከረኛዋና ታሪካዊዋ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ – ጨርቆስ – ተወልዶ አደገ። ብሩህ አእምሮን የተቸረ በዕውቀት ቀሳሚነቱ የናረና ከሁሉም በላይ ግን ሀገራዊና ወገናዊ ሰብዕናን ከስነ ምግባር ጋር ያዋሃደ የኢትዮጵያ ልጅ ኢትዮጵያዊ ሆነ። ስለ ሀገሩና ስለህዝቧም ሲል በናዚስት የዘረኝነት አስተምህሮ ካበዱት ከግፍ ጠማቂዎቹ ናዚስት ወያኔ ገዢዎች የሀገሩን የፍዳ ገፈት ተግቶና ከሀገሩ ተገፍቶ በሰው ሀገር በስደት ተንከራትቶ አለፈ። እሱም ጋዜጠኛና የሰብዐዊ መብት ተሟጋቹ ኢብራሂም ሻፊ ይባላል። ግፈኞቹና በግፍ ዘመነ ሥራ ዕድሜ የጠገቡት ሀገሩን ኢትዮጵያን ሲቆጣጠሩ በ1983 ዓ/ም እሱ ገና አስራዎቹን የጀመረ ታዳጊ ነበረ።
እነሆም ቁምጣ ታጣቂዎቹ አህያ ነጂዎቹ በረባሳ አጥላቂዎቹ ጎፈሬያሞቹና ቤሳ ቤስቲን በኪሳቸው ያልነበራቸው ናዚስት ወያኔዎች ኢትዮጵያ መንበር ላይ ከተቀመጡ በሁዋላ የጣሊያን ሱፍ ቀያያሪዎች፤ የአዞ ቆዳ ጫማ አድራጊዎች ‘ውበታቸውን’ ጠባቂዎች፤ ምቾታማና ዘመናዊ መኪና ነጂዎች ሚሊየነሮችና ቢሊየነሮች ሲሆኑ፤ ነባር ሰፈሮችን እየደረመሱ የጎስቋሎችን መሬት ሲዘርፉ፤ የራሳቸውን የናጠጡ ቪላዎችና ፎቆችን ሲገነቡ፤ ወጣቱን ሲያግዙና ሲረሽኑ፤ ሀገር ሲሸነሽኑ ሀገር ሲቸረችሩ ዘር በዘር ላይ ሲያዘምቱና ለዝርዝር የሚያታክቱ እርኩሰቶችን ሲተገብሩ እሱ – ኢብራሂም ሻፊ – እዛው አዲስ አበባ ጨርቆስ እየኖረ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ተመልክቷቸዋል፤ አጢኗቸዋል፤ አውቋቸዋል።
ኢብራሂም ከተለምዶው የወጣት ህይወት ጎዳና ያፈነገጠ ሰብዕናና የህይወት ተልዕኮ ያለው መሆኑ በገሀድ የሚታየው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመመረቂያ መፅሄት ላይ ከፎቶው ሥር ያሰፈረውን “የህይወት ጥያቄ” (ፕሮፋይል) ሲመለከቱ ነው። እንዲህ ይላል።
1. በዩኒቨርሲቲ ህይወት፤
ሀ/አሳዛኝ ወቅት – ህይወቴን አደጋ የጣሉ ወቅቶች ሁሉ።
ለ/አስደሳች ወቅት – ከጓደኞቼ ጋር የማሳልፈው ማንኛውም ጊዜያት።
ሐ/ማድረግ ብችል – ዩኒቨርሲቲውን ሠላማዊ የመማሪያና የመወያያ ተቋም ማድረግ።
2. የምትወደው ጥቅስ፤ “እጅህ ከሚደርሰው በላይ ዘርጋው፤ አእምሮህ ከሚያስበው በላይ ተመኝ፤ አለበለዚያ ገነት ለምን የተፈጠረ ይመስልሃል”
3. ተጨማሪ መልዕክት፤ የቤተሰቤም ሆነ የሀገሬ አለብኝ።
4. ስም ከነአባት ኢብራሂም ሻፊ። ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሶስት አጥረው በሚፈነዱ ንደፈ ሀሳቦች የተሞሉት የኢብራሂም “የህይወት ጥያቄ” መልዕክቶች ትንታኔ መስጠት ለፈለገ አያሌ አንቀፆች የሚወጧቸው ዓላማና ራዕይን ያጣመሩ ምልከታዎች ሆነው ይገኛሉ። ከወጣት ትከሻ የአዛውንት ሀሳብ – ይሏል እንዲህ ያለውን ነው። አዎ! ወጣቱ ኢብራሂም ሻፊ ትልቅ ራዕይና ተስፋ ስለሀገሩና ስለ ወገኑ ነበረው።
ኢብራሂም ሻፊ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በማዕረግ በማጠናቀቅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ዲግሪውን አግኝቷል። ኢብራሂም በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ በሲቪክ መምህርነት ባገለገለበት ወቅት በተማሪዎቹ ተወዳጅና ተከባሪ የሆነ ምሥጉን መምህር የነበረ ሲሆን ከመምህርነቱ ሌላ በትምህርት አስተዳደር ቢሮ ውስጥም አገልግሏል። ለምሳሌ በመምህርነት ዘመኑ ስለነበረው ዕውነታ በማህበራዊ ገፅ ላይ ካሰፈረው የሚከተለውን ያጤኗል፤
“ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ፖለቲካን (ሲቪክስ) አስተምሬያለሁ፤ የፖለቲካ መምህራንን አሰልጥኛለሁ (ከፈለጋችሁ በትግርኛ ቋንቋ ዜና አንባቢ የነበረውን ሙዱ ዓሊን ጠይቁት፤ ኮከበ ጽባህ ፖለቲካ አስተማሪ ነበር። ሰልጣኝ መምህራን ከአበላቸው አዋጥተው የግድግዳ ሰዐት ስለሸለሙኝ እና በሰልጣኞቹ ተመርጦ ሸላሚው እርሱ ስለነበር የሚረሳ አይመስለኝም)። ዲሞክራሲ እንዴት እንደሚገነባ፤ ነፃ፤ ፍትሐዊ፤ እና በፉክክር የተሞላ ምርጫ እንዴት እንደሚከወን፤ ስለ ህግ የበላይነት፤ ርትዕ፤ የርትዕ ተቋማት ነፃነት ጥቅም፤ ሀገር መውደድ፤ ሀገር በሁሉም መስክ ራስን መቻሏ አስፈላጊነት እና ሀገርን በተመለከተ ላቅ ያለ እውቀት (ማሰላሰልን ጨምሮ) እንዴት እንደሚገኝ ለተማሪዎቼ እና ሰልጣኞቼ ሰብኬያለሁ። በተረዳሁት መጠን። በዘር “ተደራጀትህ” ሀገር ትረከባለህ አላልኩም። ይህንን ካደረግህ ስህተት ነው ብያለሁ። “የአሁኑስ?” ብለው ጠይቀውኝ “ይኸን ስህተት መልሳችሁ መድገም ትፈልጋላችሁ?” ብዬ መልሻለሁ። በተለይ ሰልጣኝ መምህራኖቼን እውነታ ብቻ እንዲያስተምሩ፣ ትክክለኛ መንገድ እንዲያሳዩ አደፋፍሬያለሁ። ሀገር ከምትበጣጠስ እኛ ለጊዜውም ቢሆን ብንጎዳ ምንም አይደለም ብያለሁ። አሁን ግን የምመለከተው ሁሉ ሌላ ነው። የእኔ ብቻ ይቆጣጠር…የእኔ ብቻ ይንገስ…የእኔ ብቻ ይግዘፍ ባዩን። ለእኔ “ስልቻ…ቀልቀሎ፤ ቀልቀሎ…ስልቻ” የሆነውን!!!”
ኢብራሂም ከህይወት ዘመኑ ከአስር ዓመት በላይ የሚሆነውን ያሳለፈው የነፍስያውን ጥሪ በማዳመጥ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ነበር። በዚህም አንቱ የተባለ የስፖርትና የፖለቲካ ተንታኝና ፀሀፊ ለመሆን በቅቷል። በምክትል ዋና አዘጋጅነት ያገለገለበት ኢትዮ-ስፖርት ጋዜጣ ብቃትና ጥራቱን የጠበቀና ዝነኛ የሆነ የስፖርት ጋዜጣ ስለመሆኑ አያሌ አፍቃሪዎቹ ዋቢ ናቸው። ስፖርት ዓለም ዐቀፍና መዝናኛ የተባሉት ጋዜጠችም የጋዜጠኝነት ሙያውን ከሞረደባቸው አምዶች መኻል ይጠቀሳሉ። ኢብራሂም በተለያዩ የሬዲዮ አቅርቦቶች ላይ ሀገራዊና በተለይም ዓለም ዐቀፍ ስፖርታዊ ትንታኔዎችን በማቅረብ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ረመጥ ላይ “በባዶ እግሩ” እየተራመደ ዕውነትንና ፍትህን ሲዘግብ የቆየው የሳምንታዊው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ምክትል አዘጋጅ ነበር – ኢብራሂማ ሻፊ። በዚህ እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ ‘የነፃ ፕሬስ’ ተጋድሎ የመጨረሻው ምልክት በሆነው ሳምንታዊው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ላይ በሀገር ጉዳይ ከሚወጡት ጥልቅ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች መረጃ አዘል ፅሁፎችና ምልከታዎች መካከል የኢብራሂም ሻፊ ፅሁፎች ዐይነተኛ ድርሻ ነበራቸው። በ1997 ዓ/ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ማግሥት በናዚስቶች እየታደኑ እስር ቤት ከገቡት መኻል አንዱ ሲሆን እዚያም በደረሰበት የከፋ ድብደባ/ቶርች እግሩን ታማሚ ሆኖ በመውጣቱ የእግር ታማሚ ሆኖ ቀርቷል።
እንደ ቀደምቶቹ በናዚስቶች በሽብርተኝነት እንደተከሰሱትና እንደተዘጉት ጋዜጦችና መፅሄቶች ለስደትና ለእስር እንደተዳረጉትም ጋዜጠኞች በመጨረሻው ሰዐት “አዲስ ጉዳይ” መፅሄትም “የሽብርተኝነት” ክስ ተመስርቶበት ሲዘጋና ጋዜጠኞቹም በተመሰረተባቸው ክስ ሲዋከቡና ሲሳደዱ በነሀሴ 2006 ዓ/ም ኢብራሂም ሻፊ ከሚወዳት ሀገሩ ተገፍቶና ሀገሩን የሚያገለግልበትን የሙያውንም ‘መሳሪያ’ ተነጥቆ ለስደት ተዳረገ። ከርሱም ጋር አብረውት አብዛኞቹ የ“አዲስ ጉዳይ” ጋዜጠኞች ተሰደዱ። ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ የስደትን ህይወት ሲገፋ የቆየው በናይሮቢ ኬንያ ላንጋታ ሰፈር ነበር። እነሆም ከሀገሩ የተገፋውና ጋዜጣውን በማሸግ ድምፁን የተነጠቀው ኢብራሂም ናዚስቶች እንዳሰቡት ድምፅ አልባ ግን ሊያደርጉት አልቻሉም። እሱም እንደ ሌሎቹ ‘እልፍ’ ስደተኞች ጋዜጠኞችና ፀሀፍት ሁሉ በተሰደደበት ስለሀገሩና ስለ ህዝቡ ከመፃፍና ድምፁን ከማሰማት የሚያግደው አንዳችም ሀይል አልነበረም-ትንፋሹን ለሁልጊዜም እስከ ዋጠባት ቅፅበት።
በኢትዮጵያ መንበር ላይ ለ21 ዓመት ተፈናጦ የገዛውን የናዚስት ዘረኝነት ቀመር አርኪቴክትና የኢትዮጵያ ሰቆቃ ጠንሳሽ ከነበሩት አጋፋሪውን መለስ ዜናዊን ‘ባለ ራዕዩ መሪ’ እያሉ ለሚያወድሱት ህወሃታውያንና ለህወሃቱ ልሳን ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጭምር የሚሆን መልዕክት በማህበራዊ ሚዲያ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል፤ “ወንበዴ ያው ወንበዴ ነው!!! ዘርፎ በላ…ቀምቶ በላ…ረግጦ በላ… በዘር በሀይማኖት ከፋፍሎ በላ!! አጠገቤ ያለን ሰው ሳጣ ማን ሰማኝ? አብሬያቸው የተቸገርኩትን ማን ረዳኝ? ስንታሰር ማን ይሰማናል…ስንገደል ማን ይሰማናል…ስንቆስል ማን ይሰማናል…ስንሰደድ ማን ይሰማናል…ስለ ዘር/ሀይማኖት ተመርኩዞ በደል ስንሰማ ማን ይሰማናል?…ራዕይ የነበረው መሪ/ገዢ አልነበርንም…ወንበዴ…እንጂ…” ሲል ዕውነታውን እንደ ፈንጂ በቃላት አስተጋብቷል።
የሙያ ጓደኞቹና በቅርብ የሚያውቁት ኢብሮ ይሉታል – አብራሂምን። ኢብሮ የሚፅፍባቸው ፖለቲካዊ ማህበራዊና ስፖርታዊ ዘርፎች አድማሳቸው እጅግ የሰፋና የጠለቀ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚያስደምመው እኒህን የሚገልፅባቸው ቁጥብና ፈንጂ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮቹ ይዘትና ውበትም ጭምር እንጂ!! ለምሳሌ የህወሃቱን ልሳን ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፤ “ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ማህበራዊ ቋንቋን በየትኛውም አስፈላጊ መግባቢያ የማያውቅ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከየት ነው ያመጣነው? የእርሱን ቃለ ምልልስ እያቋረጥኩም፤ እየቀጠልኩም ለመጨረስ ቢያንስ አንድ ወር ይፈጅብኛል…ዘጊ…!!!”
ኢብራሂም ዘርፈ ብዙ የሆነ ዕውቀትና ጣዕም (ቴስት) የነበረው ወጣት ምሁርና ጋዜጠኛ ነበር። ለአብነት ቀጣዩን በሶሻል ሚዲያ የቀረበ መልዕክት ይመለከቷል። “ሙዚቃ ለምን ትሰማለህ? ልትል ትችላለህ…ቴዎድሮስ ካሳሁንን ነው የሰማሁት። የጠነዙ የዘር እና ሀይማኖት ክርክርን ልታመጣ ትችላለህ…አሁንም ቴዎድሮስ ካሳሁንን ነው እየሰማሁ ያለሁት። ስሜት፤ ሰብዐና እና ነብስ ያለው ሙዚቃን ማን ይጠላል? ቴዲ ሀገር ነው፤ ጥበበኛ ነው። ሁሌም ተከታታዮቹን፣ ወዳጆቹን እና አድናቂዎቹን የማያሳፍር። አትቋቋመውም። በቃ እንድትሰማው ያደርግሃል። ቃላት ስንጠቃ ቀላል ነው። መፈረጅ ደግሞ ከቂልነት ጋር ተጨምሮ የበለጠ ቀላል ነው።…ኢትዮጵያን ቴዎድሮስ በስድስት ደቂቃዎች አሳምሮ የሚገልፃትን ያህል ግን ማን ይሞክረዋል? – ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ።” ይህ እንግዲህ ኢብሮ የፃፈው ነው። ኢብሮ ራሱ የጥበብ ሰው ነው። ቃላቱ የጥበብ ፈርጦች ናቸውና! ኢብሮ ስለ ቴዲ ብዙ ፅፏል፤ ተሟግቷል፤ ጥብቅና ቆሟል። አብነት እናክላለን፤
“የተሰጣቸውን ፀጋ በቅንነት አስከመጨረሻው ጥግ መጠቀም የሚችሉ ሰዎች ያስቀኑኛል እወዳቸዋለሁም። ጥንካሬያቸውንም ምነው የእኔ ባደረገው ብዬ ከልቤ ተመኝቼ አውቃለሁ። የቴዎድሮስ ካሳሁን እምነት ጥንካሬ ግን የማይታመን ነው። ሀገር ለሁለት አስርተ ዓመታት በመንግስት ደረጃ ተቀምሮ እና ተሰርቶ ‘ካልተበታተንኩ’ እያለች እሱ ግን ግመሌን ላጠጣት እስከ አፋር ተጉዤ፣ ግመሌን ላጠጣት ቀይ ባህር ተጉዤ፣ አንድ ገመድ አጣሁ ልመልሳት ሄጄ። እያለ ‘ልሰርሽ’ ይላታል። ትውልድ ታሪክ እንዲያነብ ይገፋል፤ ያስተምራል። ገንዘብ ግዱ አይደለም። በሀሰት መወንጀል ብርቁ አይደለም። እንደ ሮቦት የተሰጣቸውን በሚተፉ አጉራ ዘለል ወጠጤዎች መዘለፉ ምኑም አይደለም። የእሱ ፍላጎት ሀገር ማሰር ነው። ሀገር ማቆም። ብቻውን ምንም ኃላፊነት ከማይሰማው መንግስት ጋር መታገል ብቻ። አሁንስ አሳዘነኝ – ነፍሱን የሰጣት ለካ ዓለም ንቆ / አገር ሊያቆም ነው ቴዎድሮስ ወድቆ።
ሲል አንጀቴ የተላወሰው አፄ ቴዎድሮስን ብቻ አስታውሼ አይደለም። ራሱ ቴዎድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቆም እያደረገ ያለውን ልፋት ልብ ብዬ እንጂ…” በማለት ስለ ወጣቱና የዕድሜው አቻ ቴዲ አፍሮ ጥብቅና ቆሟል፤ ስደተኛው ጋዜጠኛ ኢብሮ።
ኢብራሂም ሻፊ በዘመነ ህወሃት ያደገና ነፍስ ያወቀ፤ በዘመነ ህወሃት የተማረና የጎለበተ ምሁርና ወጣት አይመስልም – ስለ ታሪክ፤ ስለ ሰው መሆን፤ ስለ ሀገር፤ ስለ መንግሥትና ህዝብ፤ ስለ ሰብዐዊነትና ስለ መቻቻል፤ ስለሙያዊ ክብርና ልዕልና የሚፅፈውና የሚሰብከው ሁሉ ሀገራዊና ወገናዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የራዕዩና የመልዕክቱ ጥልቀት የትየለሌ ነው። እንዲህ የምንፅፈው በስሜታዊነትና አልያም በትውውቅ አይደለም። እንደውም ኢብሮን ከአነሁላይ ፅሁፎቹ በስተቀር በአካል አናውቀውም አያውቀንም። ስለ እርሱም ያወቅነውን ያህል ለማሳወቅ የተነሳነው ከህልፈቱ በሁዋላ ባደረግነው ጥቂት ‘ቁፋሮ’ ነው። ኢብሮ ታሪክን ስለምን ማንበብና ማወቅ እንዳለብን እንዲህ ፅፏል፤
“ሀገር የእዝን ድንኳን አይደለችም። ያዝ፣ ወጥር፣ ፌሮውን ምታው እና ምሶሶው መሐል ይሁን ብለህ የምታቋቁማት። ሀገር የዘመናት ሂደት ነች። በዚህ ውስጥ ደግሞ ብረት አለ፤ ጦርነት አለ። ማስገበር መገበር አለ። በዘር፣ ሀይማኖት፣ ቆዳ ቀለም እና አመለካከት ተቧድኖ ያልተጋደለ የለም። የትኛውም ሀገር ይኸን ሂደት አልፏል። በጦርነት ተተራምሷል፣ እርስበርስ ተጋድለዋል። ኢትዮጵያም ስትመጣ ይሄው ነበር። ብረት ነበር፣ ጦርነት ነበር፣ ገባሪ እና አስገባሪም ነበር። ይህን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን የምናጠናው፣ የምንመረምረው፣ ማስረጃ የምንሰበስበው፣ የምናደራጀው እና ከግኝታችን ተነስተን የምንተረጉመው ቂም ወርሰን እንደገና ለመጋደል አይደለም። ታሪክ ያለቀ ነው፤ የተፈፀመ። ስለዚህም ስህተት ከነበር ለይተን ልናርመው፤ በጎውን አውጥተን የበለጠ ልናጎለብተው እንጂ። ‘ቴዎድሮስ ካሳሁን አፄዎቹን ያወድሳል። አፄዎቹ ደግሞ ሙስሊሙን ጨቁነዋል…ሙስሊም እንደ መሆንህ መጠን ልትቃወመው ይገባል’ የሚል ‘ምሁር መካሪን’ ራሴው ዓቃቤ ህግ ሆኜ፣ ክስ መስርቼ፣ ጥፋተኛ አስብዬ፤ ራሴው ደግሞ ዳኛ ሆኜ እስር ቤት ብወረውረው ደስ ይለኛል…ምኞቴ ነው። ይሄንን ‘ምክር’ እንኳን ለዕድሜ አቻዎቼ ለመጠቆም አደባባይ ልወጣ አይደለም አብረውኝ ላደጉት በጣም ለምወዳቸው በዕድሜ እጅግ ታናናሾቼ ለእህቶቼ ልጆች ዘኪዬ እና ኢብሮዬ አይመጥንም። ሳት ብሎኝ ይኽን ስል ቢሰሙ እንኳን (ፍፁም አልልም እንጂ) በእነርሱ የግንዛቤ አቅም እንኳን እየነሆለልኩኝ መሆኔን ልብ ብለው የሚስቁብኝ ይመስለኛል…አጎቴ ምን ነካው? ብለው ክትከትከት…አምላክ ይዘንላቸው እና ጋሼ አሰፋ ጫቦ በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ‘ስለ ኢትዮጵያ አንድ መጽሐፍ አንብበህ ከሆነ…ሁለት አድርገው…ሁለት ከሆነ ሦስት…ሦስት ከሆነ አራት አድርገው። ኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዓመታት ውጤት ነች። በጣም በርካታ መጽሐፍትም ስለ ኢትዮጵያ ተጽፏል። ከተለያዩ አቅጣጫዎች እና ፍላጎት ጋር’ ሲሉን ነበር። አዎን ኢትዮጵያ ብዙ ነች። ያለፍንበት ዘመንም ረጅም ነው። ያለፍንበት ዘመንን የሚገልፁልን ብዙ መጽሐፍትም አሉን። እነዚያን መጽሐፍት የምናነበው፣ የምንመረምረው እና የምናጠናው አሁን እኔ ቂም ወርሼ፣ ጥላቻን በልቤ አርግዤ፣ በቀልን በመሻት ከወንድሜ ጋር ልጋደልባቸው አይደለም…ዘኪዬ እና ኢብሮዬም ጊዜያቸው ሲደርስ ከወንድሞቻቸው ጋር እንዲፋጁ አይደልም…
አንድ የሚያደርጉንን ነጥቦች ነቅሼ፣ የሚያስማማንን አበጥሬ እና በጋራ የሚያኮሩንን ለይቼ ብላቴናው የሚመኛትን በፍቅር የተሞላች ምርጥ ሀገር ለማየት እንጂ…!!! ለማንኛውም ወደ ፍቅር ጉዞ እያላችሁ ደግሞ ዛሬ………..!!!” በማለት ፅፏል፤ ኢብራሂም። ‘ብላቴናው የሚመኛትን ሀገር’ ማለቱም ቴዲ አፍሮን ሲጠቅስ ነው።
ኢብራሂም በምድረ ኢትዮጵያ በየትኛውም አቅጣጫ ከየትኛውም ማህበረሰብ ለተነሳና ወይም በየትኛውም የህብረተሰብ አካል ላይ ለደረሰ በደልና ጥፋት ቅርብ ነው። ቅርብ ብቻ ሳይሆን በደል ሲደርስ ያመዋል። ጥፋት ሲደርስ ነፍሱ አብራ ትጠፋለች – በውስጠ ሲቃ። ለምሳሌ ስለ ቆሼ እልቂት እንዲህ ብሏል፤ “ሁሉም ነገር ህመም ሲሆን…….በደንብ ያማል። ይጠዘጥዛል። የሰው አስክሬን ‘በግሬደር’ እየተቦደሰ ሲወጣ ያሳቅቃል። ቆሻሻ ከሰው በላይ ሆኖ ሲገድል፤ ህይወት ሲቀጥፍ ያሳርራል። 15 የተባለው……..65 ደረሰ ሲባል፣ ገና ከዚህም ይልቃል ተብሎ ሲታወጅ እምባን ያመጣል። የቆሻሻው ክምር ሰውን ሊገድል እንደሚችል እየታወቀ…….ፊልም ጭምር ተሰርቶበት….፤ ‘ጆሮ ዳባ ልበስ’ ያሉ ባለስልጣናት አሉን። ዛሬ የሀዘን መግለጫ እና ማቋቋሚያ አሰናድተናል የሚሉን። በዚህ ጉዳይ ቀጥተኛ ተጠያቂዎች ሊሆኑ የሚችሉ ባለስልጣናት ቢያንስ…ከህግ ካመለጡ የበለጠ አዝናለሁ። አሰቃቂ ሀጥያቱን ባይመልሱ እንኳን ድህነት እና እስርን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ። አምላክ ያስባችሁ ያለፋችሁ ወገኖቼ።” ሲል የውስጡን ሰቆቃ አስፍሯል ኢብሮ በኬንያ ምድር ከሚኖርበት የስደት ካምፕ። በሌላ ፅሁፉ ደግሞ “ኢሊ አባ ቦራ እልቂት የገዢው ጥፋት ነው። የዘር እልቂት በገዢው የተዘራ ነው። ከየትም ርቀት ጥፋቱ የገዢው እንደሆነ መረዳት አያቅትም።” ሲል በናዚስት ህወሃት አቀናባሪነትና መሪነት በኢሉባቦር የተካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አውግዟል።
ኢብራሂም ሻፊ ክብር ለሚገባው ክብር የማይነፍግ በምግባሩና በሰብዕናው ተልዕኮ የዘቀጠውንም በተገቢው ቋንቋ የሚነቅፍ ሥነ ሙያዊ ልዕልናውም ከፍ ያለ ጋዜጠኛ ኢትዮጵያዊ ነው። ምሳሌ እናቀርባለን። “በርካቶች ባይሞቱ፣ ባይገደሉ፣ አካላቸው ባይጎድል እና ባይታሰሩ ዛሬ ስለ ጄኔራል ለገሰ ተፈራ ማለፍ የምናዝንበት ቀን ነበር። ጄኔራሉ ከኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ አየር ኃይሉ ባልደረባ የማትረባዋን F-5E ይዘው የወቅቱ ጠላት ሶማሊያ ስድስት ሚጎችን አየር ላይ ያስቀሩ ነበሩ። በርካታ ፊልም የሚመስሉ ግዳጆችን በጀግንነት የተወጡ ብሩቱ ሰውም ነበሩ። በአንድ ወቅት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት በነበሩት አብዱላሂ ዩሱፍ ተይዘውም ነበር……..አብረዋቸውም አፈወርቅ ኪዳኑ የተባሉ ሌላ ጀግና ነበሩ። ጋሽ አፈወርቅ ህይወታቸው ሶማሊያ አስር ቤት ሲያልፍ………ጄኔራል ለገሰ ግን ክብዙ ዓመታት እንግልት እና የእስር ቆይታ በኋላ ተመለሱ። የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የጀግና አቀባበል ማድረጉን ትዝ ይለኛል። ትላንት ግን ህይወታቸው ማለፉን ሰማሁ………አምላክ ይዘንሎት ጄኔራል ለገሰ ተፈራ!!!” እንግዲህ ኢብራሂም ማለት ይሄ ነው ወይም ነበር። ስለ አትዮጵያ ክብርና ልዕልና ስለ ህዛቧም ነፃነትና ስለ ባንዲራዋ መታፈር መሥዋዕትነትን የከፈሉትን የማይረሳ፤ የሚያስታውስ፤ ክብር የሚሰጥ ወጣት!! ኢብሮ የቀደሙትን ብቻም ሳይሆን የእርሱ ትውልድ አካል የሆኑትንም የህዝብ ሰቆቃ ለማሰማት የራሳቸውን ህልውና ወደጎን ለሚያደርጉትም አክብሮቱንና ወገናዊነቱን ሲገልፅ አይሰስትም። ቀጣዩ አብነት ምሥክርነት ይቆማል።
“በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለው ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ አፈና፣ አስር እና ስደት ያንገበገበው ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሊምፒክ ማራቶን ሁለተኛ ወጥቶ ድልን ካስመዘገበ በኋላ ደስታውን በጭፍራ አልገለፀም። በቁጭት ጥርሱን ነክሶ እና መለያውን አውልቆ ተቀምጦ ነገሮችን በአርምሞ ሲከታተል ነበር። የሀገሩ አምባገነናዊ አገዛዝ እየሰራ የሚገኘው ወንጀል አንዳስቆጨው፣ እንዳበሳጨው እና እንዳስጨነቀው ፊቱን ብቻ ተመልክቶ ማስተዋልም…መናገርም ይቻል ነበር። ከአሸናፊዎች የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫም በኋላ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ግፍ መኖሩን ለማሳየት የምንጠቀምበትን ምልክት አሳይቷል…በቃላት ሳይሆን ጀግንነት በታከለበት ተምሳሌታዊ መንገድ የህዝብ ህመም ህመሜ ነው ብሏል።” ሲል የጀግናውን የኦሎምፒክ ታሪክ ሰሪ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳን ሀገራዊ መሥዋዕታዊ ተግባር አድንቋል።
ኢብራሂም ሻፊ በኖረበት አጭር የህይወት ዘመኑ የተቸገሩትን በመርዳት፤ ያለውን በማካፈል፤ ለዕውነትና ለታሪክ፤ ለህዝብና ሰው ስለመሆን ጥብቅና የቆመና የተሟገት፤ ከናዚስት ህወሃትና ህወሃታውያን ጋር እንዳች ጥቅመኝነትን ሳይጋራ የኖረና የተሰደደ በስደት ህይወቱም ስለ ኢትዮጵያ እንደዘመረ፤ እንዳለቀሰ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሠላምና ስለ ህዝቧም ደህንነት ተስፋ እንደሰነቀ ያለፈ የኢትዮጵያ ልጅ ኢትዮጵያዊ ነው። ለምሳሌ ከሀገሩ ተገፍቶ ከመሰደዱ በፊት ያደርጋቸው ከነበሩት ምግባረ ሰናይ ተልዕኮዎቹ መኻል እንዲህ ፅፏል፤
“ኢህአዴግ ሲመጣ ልደቴን ማሳልፍበት ምልክትም አጣሁ። አዲስ ዓመት መጥቶ ከከበቡኝ ልጆቼ፣ ጥቂት ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ጋር ሆኜ ሀሳብ መጣልኝ። ህፃናቱን እየመረጥኩ ‘ስንተኛ ክፍል ነህ?’ ማለት አመጣሁ። ገረመኝ…! ብዙዎቹ ትምህርት እንኳን አልጀመሩም ነበር። ትምህርት ነፃ ቢሆንም መማሪያውን ማግኘት ነበር ፈተናው…ለእነርሱ። ትንሽ እሰራ ስለነበር፣ ገንዘብ ኪሴ ውስጥም ስለነበር ደብተር እና ሌሎች የመማሪያ ቁሶች መግዛት ጀመርኩ። አካባቢዬ ያሉ ሰዎች ማዋጣት ጀመሩ። የቻልነውን ገዛን፣ ሰጠን። ደስታው ልዩ ነበር። ከዚህ በኋላ መስከረም 2 በመጣ ቁጥር ይህን እቀጥላለሁ ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ። ፍፁም መርሻ፣ ቃሲም ደሉ እና በያን ድንቁ የሚባሉ ከአጠገቤ ማይጠፉ ጀግና ልጆች ነበሩኝ። ጳጉሜ ሲጀምር የመዋጮ ገንዘብ መሰብሰብ የሚጀምሩ።” ይህ እንግዲህ ኢብሮ ተወልዶ ባደገባት ጨርቆስና አካባቢው የነበሩ ወጣቶችን ከኪሱ ገንዘብ እያወጣ መርዳትና ማስተማር የጀመረበትን ሂደት የሚያመላክት ሲሆን ‘ልጆቼ’ የሚላቸው እርሱ የሚረዳቸውን እንጂ እሱ ትዳርም ሆነ ከአብራኩ የተከፈለ ልጅ ሳይኖረው ነው ይህቺን ምድር የተሰናበተው።
ጋዜጠኛ፤ የሰብዐዊ መብት ተሟጋችና አቀንቃኝ /አክቲቪስት/ ኢብራሂም ሻፊ ‘አክቲቪስት’ ማለትና ‘አክቲቪስትነት’ን ሲገልፅ፤ “አክቲቪዝም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ነገሮች ቁልቁል ሲሄዱ የሚቃወም ወደፊት ሲመጡ የሚያዳንቅ ነው። የአክቲቪስቱ ዋነኛ መሳሪያ መፃፍ እና ጥሪ ነው።” በማለት ፍንትው አድርጎ አስቀምጧል።
እነሆ የጎልማሳነት ዘመኑን ሀሌታ ሲጀምር የተቀጨው ኢብሮ የህይወት ዘመኑ ፍፃሜ ላይ መድረሱን የተነበየው ከህልፈቱ ሁለት ሳምንት በፊት በፃፈውና ለዚህ ጥንቅር ርዕስ ባደረግነው አንጀት በሚበላና ከህሊና በማይጠፋው ‘መንግሥት ሲኖረኝ ቀስቅሱኝ’ በሚል በደመደመው መልዕክቱ ነው። ኢብሮ እስከ ወዲያኛው ከማሸለከቡ በፊት የፃፈው እንዲህ ይላል።
20 December 2017 at 13:08
ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የተሰጠ “መንግስትነት እና ገዢነት ማይፍርስበት” መግለጫ ነው። “ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እስከአሁን ባደረገው ግምገማ በ4ቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የርስ በርስ መጠራጠር ያመዘነበት፣ አለመተማመን ቀስ በቀስ የነገሰበት መሆኑ በግልጽ ታይቷል። በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅታችን አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን በሚገባ ይገነዘባል። ሃገራችን በአሁኑ ሰዓት ለምትገኝበት አስጊ ሁኔታ ድክመቱ ያደረገው አስተዋፆ ከፍተኛ ነው። የድርጅታችን በየደረጃው ያለው አመራር ከሞላ ጎደል የዚሁ ድክመት ተጋሪ ቢሆንም ስራ አስፈፃሚው የዚህ ችግር ዋነኛ ባለቤት መሆኑንና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ችግሮችን በቁጭት መንፈስ ከመፍታት ይልቅ የእርስ በርስ ንትርክ ላይ እንደሚያተኩር መግባባት ላይ ተደርሷል።” ኢትዮጵያን የሚመራው ይሄን የጻፈ የከረፋ ተቋም ነው። “አቅም የሌላቸውን በጭካኔ እና ጅምላ ገድያለሁ” ብሎ ኃላፊነት የሚወስድ መረን ገዢ። #መንግስት ሲኖረኝ ቀስቅሱኝ
እነሆ ረቡዕ ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ/ም (ጃንዋሪ 3/2018) ከሀገሩ ተገፍቶ በስደት ይኖር የነበረው ጋዜጠኛ ኢብራሂማ ሻፊ ኬንያ ናይሮቢ ከተማ ላንጋታ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ግብዐተ መሬቱም ሲታመምና ሲያለቅስላት በኖረችው ሀገሩ ኢትዮጵያ ታህሳስ 27 ቀን 2010 ዓ/ም (ጃንዋሪ 5/2018) በአዲስ አበባ ኮልፌ እስላም መቃብር ‘እልፍ’ ህዝብ በተገኘበት በታላቅ ሥነሥርዐት ተከናወነ። የሥራ ባልደረቦቹና የቅርብ ወዳጆቹ ከሆኑት መካከል የ“አዲስ ጉዳይ” ጋዜጠኞች የኢብራሂምን ዜና ህልፈት ሲገልፁ እንዲህ ብለዋል፤
Addis Guday
4 January at 23:26
ባልደረባችን፤ ጓደኛችን፣ ወንድማችን ብዙ ለሃገሩ ያበረክታል ብለን የምንጠብቀው ኢብራሂም ሻፊ Ibrahim Shafi Ahmed ድንገት ተለይቶናል። የአዲስ ጉዳይ መፅሔት ባልደረቦች ሀዘናችን መራር እና በቁጭት የታጀለ ነው። ቁጭታችን ግን ኢብሮን ድንገት ማጣታችን ብቻ ሳይሆን ለኢብሮ እና ለሌሎች ወገኖቻችን ስደት፣ እንግልት፣ ስቃይ ብሎም ሞት ዋና ተጠያቂ የሆነው አምባገነናዊ ሥርዓት ተወግዶ ዜጎች በሃገራቸው የመናገር ነፃነት ሆነ ሌሎች የሰብኣዊ መብቶቻቸው ተጠብቆላቸው፣ ግፍ የተዋለባቸው ወገኖች ሁሉ በተገቢው መንገድ የሚታሰቡበትን ፍትሃዊ ሥርኣት መናፈቅን የተመረኮዘ ነው።
የባልደረባችን ኢብራሂም ሻፊ ዜና እረፍትን ተከትሎ ከሁሉም በፊት የኢብራሂም ቤተሰቦች ይህንን አሳዛኝ መርዶ ተገቢውን ሥርኣት በጠበቀ መልኩ ተረድተው አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ይወስዱ ዘንድ በማሰብ ትኩረታችን በተቻለ አቅም የቤተሰቡን ከባድ ሃዘን መጋራት እና የወንድማችን ሥርዓተ ቀብር በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ዝምታን መርጠን ቆይተናል።
ባልደረባችን፤ ጓደኛችን፣ ወንድማችን ኢብራሂም ሻፊ (ኢብሮ) በርካቶች በስፋት ከሚያውቁለት በሳል የስፖርት ጋዜጠኝነቱ እና የስፖርት ክንውኖች ትንታኔ ልዩ ክህሎቱ ባሻገር የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቁ ኢብሮ በበርካታ አገራዊ ሆነ ዓለምአቀፋዊ የፖለቲካ፣ ማሕበራዊ ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋዜጠኝነት ሙያው የድርሻውን የተወጣ፣ ለለውጥ የሚሆኑ በሳል ሐሳቦችን በየጊዜው ያመነጨ፣ ያመነበትን ነገር በአደባባይ በመናገር ለዚሁም ዋጋ የከፈለ፣ ብዙ ለአገሩ ሆነ ለወገኑ የሚቸረው የነበረው ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነበር።
ኢብሮ ለዚህ ድንገተኛ ሕልፈት የበቃው በግፍ ታስሮ የደረሰበት ድብደባ ማባሪያ ለሌለው ህመም ዳርጎት ከዚሁ የጨቋኙ ሥርዓት የግፍ እስር ስደት ላይ በሆነበት ወቅት በመሆኑ ሃዘናችንን ከባድ ያድርገዋል። በተለይ ሕመሙ በፀናበት ወቅት በቅርበት ካጠገቡ በመሆን አቅም የፈቀደውን ነገር በማድረጉ በኩል የድርሻውን ሲወጣ ለከረመው ባልደረባችን ሃብታሙ ስዩም እና ሌሎችም ጋዜጠኞች በዚሁ አጋጣሚ ምስጋናችንን በመግለፅ ከምንም በላይ በዚህ በጣም አስቸጋሪ የሀዘን ወቅት በዋንኛነት ለባልደረባችን፤ ለጓደኛችን፣ ወንድማችን ኢብራሂም ሻፊ (ኢብሮ) ቤተሰቦች፣ ወዳጆች አድናቂዎች ጥልቅ መፅናናትን እንዲሰጥልን /እንመኛለን/።”
የኢብራሂም የሙያው አጋርና ወዳጁ የሆነው ስደተኛው ጋዜጠኛ ሀብታሙ ስዩም በበኩሉ የፃፈው የስንብት መልዕክት እንዲህ ይላል፤
Habtamu Seyoum
4 January at 21:48
እዚያ የማገኝህ ይመስለኛል!
በዚህ ጠዋት ይዤው የመጣሁት መርዶ የብዙ ወዳጆቹን እና አድናቂዎቹን ልብ የሚሰብር እንደሆነ ይገባኛል። ቢሆንም በዚህ ሰዓት መራሩን ሀዘን የማጋራት አመራጭ የለሽ ዕጣ ፈንታ ገጥሞኛልና ቀሪ አቅሜን አሰባስቤ መንፈስ ሰባሪውን ዜና እንዳጋራችሁ ይሁን። ወንድማችን ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ ረቡዕ ታህሳስ 25.2010 ዓ.ም በናይሮቢ ከተማ ላንጋታ በተሰኘው ክፍለ ከተማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ኢብሮ ከወራት ወዲህ በጠና ታምሞ ነበር። ሁሌም በሚታወቅበት የመንፈስ ጥንካሬው እየታገዘ እስከ ዕረፍቱ ዋዜማ ድረስ በማህበራዊ ገጾች ላይ ሳይቀር ሀሳቡን ያጋራ ያካፍል ስለነበር የህልፈቱ ዜና ድንገተኝነት በዓመታት ትጋትና አይተኬ ተሰጥኦው ያገለገላቸው ወዳጆቹን ለድንጋጤ እንደሚጥል እንረዳለን። ሆኖም በአይበገሬነት ለዓመታት የቆየው ወንድማችን በስተመጨረሻ በሞት ተሸንፏል።…
ከጥቂት ሰዓታት በፊት የወዳጃችን፣ መምህራችን፣ ወንድማችን ኢብራሂም ሻፊ አስክሬን ከኬኒያ ጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ጣቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተልኳል። ከጥቂት ሰዓታት በኃላ ወንድማችን በተሟገተላት፣ ስቃይና እንግልት በተቀበለላት ናፍቆቱና ህመሙ ሆና በከረመችው ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዕረፍቱን ያደርጋል። በስራዎቹ ፣ በመልካም ግብሮቹና በግዙፍ አበርክቶቱ የሚያውቁት አድናቂዎቹና ወዳጆቹ የሚገባውን ክብር እና አሸኛኘት እንደሚያደርጉለት ሙሉ ዕምነት አለን። የደግነት እና የጥንካሬ ተምሳሌት ለሆናችሁ የቤተሰቡ አባላት፣ ለመላው አድናቂዎቹና ወዳጆቹ፣ የስደት ዓለም ወንድሞቹና እህቶቹ በምን ቃል ሀዘናችሁን ማቅለል፣ በምን ታምር ስብራታችሁን መጠገን፣ በምን ቃል ጉድለታችሁን መተካት እንደሚቻል ፈተና እንደሚሆን አውቃለሁ። የብዙ ታምራት ባለቤት የሆነው ፈጣሪ መጽናናትን በመላክ እንዲረዳችሁ ይሁን። ኢብራሂም ወንድሜ ዓይኖችህ በተከደኑ አፍታ የገነት በሮች ሲከፈቱልህ ታውቆኛል። ወንድማለም እዚያ የማገኘህ ይመስለኛል። እስከዚያው ደህና ሁን ጓደኛዬ።” ሲል ኢብሮን ተሰናብቶታል ጋዜጠኛ ሀብታሙ።
አዲስ አበባ ላይ የሚገኘው ሶደሬ ዜና (ሶደሬ ኒውስ) የተባለ የዜና አውታር ስለ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ልዩ የመታሰቢያ ዝግጅት አስተላልፏል። የዝግጅት ክፍሉ በልቅሶው ወቅት ከሀዘንተኞች መካል በመገኘት በተለይም እንደ ጉድ ከተገኙት ወጣቶች መካከል የጥቂቶቹን የሀዘን መልዕክት የያዘና የስሜታቸውን መጎዳት ጥልቀት ጭምር ያሳየ ነበር።
ዝግጅቱን ያቀረበው የኢብሮ አድናቂ ጋዜጠኛ “እውቀቱና የራሱ አመለካከት ለራሱ ሳይሆን ለሌሎች በማድረግ ላይ ይመረኮዛልና እንደውም ቤተሰቦቹን ይህን ያህል ያስተውላል ወይ ብለን ለመጠየቅ እንችላለን” – ይላል የኢብራሂምን ከራስ በፊት ሌሎችን የማስቀደም የህይወት መርህ ለታዳሚ ሲየስተዋውቅ። “ኢብራሂም ለኛ ትልቅ ሰው ነው። ትልቅ ሰው ነው ያጣነው። ሀገራችንም አንድ ትልቅ ሰው እንዳጣች ይገባናል። ህይወቱ እንደዚህ በአጭር በመቀጨቱ ጥልቅ ሀዘን ነው የተሰማን” ይላሉ ለጋዜጠኛው የተናገሩት የጨርቆስ ወጣቶች። “ስለ ሰው ይጨነቃል እንጂ ስለራሱ አያስብም። የሰውን ሀሳብ እንደራሱ አድርጎ ስለሚያይ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከቤተሰቡ ቢጣላ እንኳን አስታራቂው እሱ ነው። ለራሱ ሳይሆን ለሰው የሚሞት ነው።” “በእሱ ሞት ብዙ ነገር ነው ያጣነው። ለምሳሌ ብዙ ጉዳዮችን ከእርሱ ጋር ነበር የምንወያየው። ማንኛውንም ያልተመለሰልህን ጥያቄ እሱ ይመልስልሃል። ውስጤ የነበሩ ጎዶሎዎችን የሚሞላልኝ እሱ ነበር። እኛ ከእሱ ተጠቀምን እንጂ እሱ ከኛ የተጠቀመው ነገር የለም።”
“እሱ ሰዎችን አሰባስቦ እርሳስ ደብተር ቦርሳ ይገዛ የት/ቤትም ይከፍል ነበር። እንደ ዜጋ ከምንም በላይ ሀገሩን ይወድ ነበር። ብዙ ልጆች (እስላም ክርስቲያን) ሳይል አስተምሯል። ብዙ ልጆች ከጎዳና ላይ አንስቶ አሳድጓል። አስተምሯል። እንደውም እሱ ከደረሰበት በላይ አድርሷል።” ብለዋል የጨርቆስ ወጣቶች ለ’ሶደሬ ኒውስ’ ጋዜጠኛ ሳግ እየተናነቃቸው በሰጡት ቃለ ምልልስ። ወጣቶቹ በቀብር ሥርዐቱ ላይ የሚለበስ ምስሉን የያዘ ቲ ሸርት አዘጋጅተውና በላዩም “እንወድሃለን ፤ ነፍስህን በገነት ያኑራት” የሚል መልዕክት ፅፈው እንደነበር ሶደሬ ዜና ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶቹ ኢብሮን ለማስታወስ የ”ሻማ መብራት” ዝግጅትም አድርገዋል።
ለጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ የተዘጋጀውን የ“ሶደሪ ዜና” የመታሰቢያ ፕሮግራም ሲቀነብብ ጋዜጠኛ ‘አቢይ’ እንዲህ ብሏል። “ሁሉም ሰው ሀሳብ ነው ብሎ የሚያስባቸውን ነገሮች መናገሩ ጥቅም አለው። ሀገርን ያሳድጋል። ግለሰብን ያሳድጋል። ለህብረተሰብ ለውጥ ሊያመጣበት ይችላል። ኢብራሂም በእግር ኳስ ላይ የሚፅፋቸው ፅሁፎች በጣም የሚገርሙ ናቸው። ፖለቲካ ላይ በሚፅፋቸው ፅሁፎች ደግሞ በተለይ መንግሥት ላይ ሥራዎቹን እየነቀፈ የሚተች ጋዜጠኛ እንደሆን እናውቃለን። ከዚህ በፊት በአዲስ ጉዳይ መፅሄት ላይ ብዙ ፅሁፎችን እናነብ ነበር። እንደዚህ ዐይነት ሰዎች አይጥፉ ማለት ያስፈልጋል። በጣም ነው ሀገርንም ሊያሳድጉ የሚችሉት። ሁሌ ተመሳሳይ ዐይነት ሀሳብ ሲኖር ሊወደቅም ይችላል። በአስተሳሰብ ደረጃ ልዩነቶች ሲኖሩ አንዱ ከአንዱ የተሻለ ሀሳቦች እንዲመጡ ያደርጋልና። /ኢብራሂምን/ በግላችን በጣም የምናበረታታው ጋዜጠኛ ነበር – በፅሁፎቹ። ጥሩ ነገሮችን ብቻ መፃፍ ጥሩ አይደለም። መጥፎዎቹን ድርጊቶች ነቅሶ መፃፍ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርግ ነውና በፅኑ መንግሥትን በደንብ እየተቸ የሚፅፍ ጋዜጠኛም ነውና /ኢብራሂምን/ በጣም እናመሰግነዋለን ለፃፈልንና ላደረገው አስተዋፅዖ።”
እነሆ እኛም ለዚህ ታላቅና ሩቅ ዓላሚ ቅርብ አዳሪ ጋዜጠኛ ያዘጋጀነውን ማስታወሻ እንደሚከተለው እናሳርጋለን።
ኢብራሂም ሻፊ ሆይ፤ ነፍስህን ከሀገርህ ሰማዕታትና ፃድቃን ጋር አላህ/እግዚአብሄር ያኑርልን! አዎ ብላቴናውና አንተ የደከማችሁለት መንግሥት በቅድስቲቱ ሀገርህ ላይ ሲቆም ትውልዱ ያኔ ይቀሰቅስሃል!! ያኔም ከመቃብር በላይ ትኖራለህ! የሞተለት መንግሥት ቆሟልና እነሆ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ ተነስቷል ይሉህማል። እስከዛው ለቤተሰቦችህ፤ ለወዳጅ ጓደኞችህም ሁሉ መፅናናት ይሁን!!
ኢትዮጵያ ሆይ፤ እንባሽና ሰቆቃሽ መቼና እንዴት ይሆን የሚያበቃው?
ጥር 2010 ዓ/ም (ጃንዋሪ 2018)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com
/ዋቢ፤ ከቪኦኤ፤ ከሶደሬ ኒውስ፤ ከጉግል ፈልግ፤ ከሶሻል ሚዲያ እና ከ‘ግሎባል ቮይስስ’ ዜና ተውጣጣ።/
1