ሰሞኑን አየሩን የሞላው “የበላይነት” የሚለውን ጽንሰሃሳብ በመለጠጥና በማጥበብ ዙርያ ሆኗል። የህወሃት የበላይነት፣ የትግራይ የበላይነት፣ የትግራይ ህዝብ የበላይነት በሚሉ ብዙም በማይራራቁ ጽንሰ ሃሳቦች ዙርያ ከዝንብ መላላጫ የማውጣት ያህል ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ነው።
እነዚህ እሰጥ አገባዎች አብዛኛውን ጊዜ ስሜታዊነትና ጥላቻም ተቀላቀሎባቸው ሶሻል ሚድያውን፣ የርስ በርስ ውይይቱንና መገናኛ አውታሮችን ያጣበቡ ሲሆን በጣም ጥቂቶች በአጋጣሚው የጠለቀ ትንተና በመስጠት በነገሮች ላይ ያለንን እይታ እንዳሰፉት እሙን ነው።
ወያኔም ህብረተሰቡ በዚህ ስሜታዊ እንካስላንትያ ሲጠመድ ሊያገኝ የሚችለውን እፎይታና የተቃውሞው ጎራ መከፋፈል ሊያተርፍበት ሲንደፋደፍ ይታያል።
ለእኔ ደግሞ “የበላይነት” አለ፣ የለም የሚለው ጉንጭ አልፋ ውይይት ላይ ጊዜና ጉልበታችን ሲጠፋ አግባብ ሆኖ አይታየኝም። የነኢህአፓና መኢሶን “እናቸንፋለን” ና “እናሸንፋለን” ተራና መናኛ ቃላት ብዙ ሺህ የአገሪቷን ዜጎች እንዳጋደለና የትግሉን አቅጣጫ እንዳሳተ አይተናል። ዛሬም የቃላት አዙሪት ውስጥ ሳንገባ በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍክፍል አለመኖሩን፣ ህዝቡ የስልጣኑ ባለቤት እንዳልሆነ፣ የህግ የበላይነት እንደሌለና አገሪቱ ህልውናዋ አዳጋ ላይ መውደቁን ከተስማማንበት፤ ለዚህ ሁሉ ዳፋ ተጠያቂ የሆነው ዘረኛና ዘራፊ የህወሃት ቡድን መሆኑን አምነን ስርዓቱን ለመጣል ጊዜ፣ ጉልበትና ሃብታችንን በዚያ ላይ ማዋል እንጂ “የበላይነት” ቲዎሪ ስንሰነጥቅ የምንውልበት ፋይዳ የለውም።
አባቶች “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ያሉት ይህንን ዓይነቱን ዓላማውን የሳተ ድርጊት ነው። ወያኔ ጉልህ በሆነ ሁኔታ ፊታችን ላይ ቆሟል። ቅዝምዝሙን ከወያኔ አሻግረን አርቀን አንወርውረው። ወያኔ ሲጠፋ የበላይነቱ ይጠፋል። ጉልበታችንንና ጊዜያችንን ወያኔን ትተን ጥላውን ስናባርር መዋል አዋቂ አያደርገንም።
አንተነህ መርዕድ