ስምህን ሳላነሳ የተወጋ አይረሳ! ​/ከይሜ ወረደሮ/

ስምህን ሳላነሳ የተወጋ አይረሳ! ​/ከይሜ ወረደሮ/

ስምህን ሳላነሳ፣ ምኑን ሆንከው ፀጋ
ለአብሮነት መኖር፣ እየሆንክ አደጋ፣
አድርገህ ከያዝከው፣ የሙሉቀን ሥራ
ለማቃባት ደም፣ ኦሮሞን ካማራ።

‘ጀሃዳዊ ሃረካት’፣ እና ‘አኬል ዳማ’
በለምለሟ አርሲ፣ በአኖሊ ከተማ
ወያኔ ያቆመው፣ የጥላቻ ሃውልት
የተሸከመው እጅ፣ የተቆረጠ ጡት
ሆነ ውጤት አልባ፣ አነሰ አሉህ እንዴ
አሽከርካሪዎችህ፣ ፍጠር ሌላ ዘዴ?
ጦርና ጎራዴ
ሕዝቡን ለማማዘዝ
ድንገት ቱግ ብለህ፣ የምትረጨው መርዝ።
ዕውቀት ነበርኮ፣ ወገንን ለመጥቀም
ተከባብሮ እንዲኖር፣ ተዋዶ በሰላም
አየ ያንተስ መማር፣ “በረከተ መርገም”!!

ተስፋ ለቆረጠ፣ ቀን ለጨለመበት
ለጭቁን ወገኑ፣ መላ ለጠፋበት
ታጭዶ ለሚወቃው፣ በአግዓዚ ጥይት
በአላሚ እሩምታ፣ በቅሊንጦ ታጥሮ
ዶጋመድ ለሆነው፣ በሳት ተንጨርጭሮ
ፍዳውን ለሚያየው፣ እሥር ቤት ታጉሮ
እርቃኑን ለቀረው፣ በግብር በግቦ
በኑሮ ውድነት፣ ለሚያድረው ተርቦ
ለተሸማቀቀው፣ ፍትህ ሰጥታው ጀርባ
ለተከናነበው፣ የስቆቃ ካባ
ባይታወር ለሆነው፣ በቀየው በደጁ
መከራውን አይቶ፣ ያስተማረው ልጁ
አንገቱን ቀና አርጎ
እንባውን ጠራርጎ
አለሁህ ካላለው፣ ካልተጋፈጠለት
ክፍል ቆጠረ እንጂ፣ አልገበየም ዕውቀት።

ስምህን ሳላነሳ
ሁሉም ስለሚያውቅህ፣ የተወጋ አይረሳ፤
ኧረ ለመሆኑ፣ ምን አለ ያንተ አባት
ሚስቱን እናትህን፣ ዋጋ ስታሳጣት?!
ስታብጠለጥላት፣ አይንቁ ስትንቃት
ፍፁም ስትነፍጋት፣ የናትነት ክብር
ቆልለህ ስትቀብራት፣ በወንጀል ክምር
ስለተወለደች፣ ከአማራ ዘር?
ግን – እንደወንጀለኛ መቆጠር ካለባት
ይገባታል ቢባል፣ ዋጋ ግምት ማጣት
ትወቅ ጉዷን ቢባል፣ ተገምድሎ ፍርዷ
አበቃ አጥፍታለች፣ አንተን በመውለዷ!!
እንደሚባለው፣ ፍየል ወልዳ እሣት
ትልሰው ትተወው፣ እንደቸገራት
ዕድሏ ሆነና፣ ያንተም እናት ጉዳይ
በምንም ቢለካ፣ ከዚህ ምሳሌ አይለይ።

ዘጠኝ ወር አርግዛ፣ በስቃይ አምጣ፣
በሞትና ሽረት፣ መካከል ተንጣ
ወልዳ አሳድጋ፣ ትምህርት አስተምራ
ጠላት ስታደርጋት፣ በመሆኗ አማራ!
ያሰኛል – ምነው አጥንት ሆነህ፣ በቀረህላት
ከሆዷ ሳትወጣ፣ ሳትወልድህ በፊት።
አለች አይባልም፣ ካለች በሕይወት
ሳትሞት በቁሟ፣ ስለቀበርካት።
አወይ መታደሏ፣ እንደሆነም ሙታ
ማህፀኗን ከምትረግም፣ የምትላትን ሰምታ።

እስኪ ልጠይቅህ ስምህን ሳላነሳ
አንተም ታውቀዋለህ፣ የተወጋ አይረሳ፣
ያባትህ ስም ትርጉም፣ ከሆነ “አስታራቂ”
አልከበደህም ወይ፣ ስትሆን “አራራቂ”?

ከእንግዲህ ወዲህ፣ በአንተ ምክንያት
ግሥ ይሁን ያንተ ስም፣ መግለጫ “ክህደት”
የሱ ስም ያላችሁ፣ ባዲስ ስም ተጠሩ
ወገን ከሚያራርቅ፣ ስም ከምትጋሩ።

ትርጉሙ ምንድን ነው፣ ከቶ ያንተ ሥደት
ዘረኛ እስከሆንክ፣ ልክ እንደሕወሃት?
ምንድን ይሆን ጠብህ፣ ከወያኔ ጋር
እኩል ከጠላኸው፣ የአማራን ዘር?

ቢሸፍንህ እንጂ፣ ቢገልጽልህማ
አማራና ኦሮሞን፣ ማን ነበር ያስማማ፣
በሁለንተናው ውስጥ፣ እንዳንተ አዋህዶ
ካማራ ከኦሮሞ፣ ማንነት ተገምዶ
ካማራ ከኦሮሞ፣ ፍቅረኞች ተወልዶ።

የፈጀውን ቢፈጅ፣ ቢውልም ቢያድር
በሁለቱ ሕዝቦች፣ ጥብቅ ትሥስር
ሕዝባዊ አመፁ፣ ሲደርስ ከዳር
ማፈርህ አይቀርም፣ ጌታህ ሲገረሰስ
ተቆርቋሪ መሳይ፣ አንት “የትሮይ ፈረስ”።
ስምህን ሳላነሳ
የተወጋ አይረሳ!

LEAVE A REPLY