በአማራ ክልል የሚተዳደረው “በኩር ጋዜጣ” እና አስቸኳይ አዋጁ

በአማራ ክልል የሚተዳደረው “በኩር ጋዜጣ” እና አስቸኳይ አዋጁ

በአማራ ክልል መንግስት ስር የሚተዳደረው “በኩር ጋዜጣ” አስቸኳይ አዋጁን አስመልክቶ የሚከተለውን ይዞ ወጥቷል።

___________

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ

ችግሩን ከምንጩ አይፈታውም”

ምሁራን

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል::

ይህ አዋጅ በ2009 ዓ.ም በሀገሪቱ የነበረውን አለመረጋጋት ለማስቆም ለ10 ወራት ያህል ተግባራዊ ተደርጐ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመልሶ ተግባራዊ የተደረገ ነው:: ይህንን ተከትሎ ከአዋጁ መውጣት በፊትና በኋላ ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያስተናገደ ይገኛል:: በተለይም አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የነበረው ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና የመብት ተሟጋቾችን እንዲሁም ተከሰው በእስር ላይ የነበሩ ግለሰቦችን ከእስር የመፍታት እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት እንደ አንድ ትልቅ ዕድል ተወስዶ ነበር::

ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሃገሪቱ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መግባቷ ብዙዎችን ግር አሰኝቷል:: ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ምን እየሆነ ነው?

ከአዋጁ ባሻገር

አቶ መልካሙ ብርሌ የተባሉ የባህር ዳር ነዋሪ ለበኩር ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈልጋል የሚል እምነት የላቸውም:: ምንም እንኳ በሀገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚታዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ቢኖሩም ይህንን ችግር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብቻ ለመፍታት መሞከር ተገቢ አይደለም ይላሉ፤ “ሌሎች አማራጮችን መፈለግ ተገቢ ነበር:: ውይይት ማድረግና በበሰለ አመራር ጉዳዮችን ወደ ነበሩበት የመመለስ አቅምን መፍጠር የአካባቢውን አመራሮች ይጠይቃል” ብለዋል::

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሃገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄዱና በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት መፍትሔ መስጠት ስላልተቻለ የአዋጁን አስፈላጊነት አስቀምጧል:: ይሁን እንጂ አዋጁን እንደ መጨረሻ መፍትሔ ከማየት ይልቅ ሌሎች አማራጮች አልነበሩም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ሲሰነዝሩ ይሰማል:: በእርግጥስ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጋብዝ ነው ወይ? የሚለውም የብዙዎቹ ጥያቄ ነው::

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ፣ “ከአዋጁ ውጭ ሌሎች የመፍትሔ መንገዶች አሉ ብየ አምናለሁ” ሲሉ፤ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር መምህር የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ በበኩላቸው፣ “ሲጀመር ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያበቃ በቂ ምክንያት የለም” ባይ ናቸው::

አቶ ስዩም፣ “አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የድንበር ወረራ፣ ህገ መንግስትን በኃይል ለመናድ አሊያም የበሽታ ወረርሽኝ ሳይሆን ህዝብ የሚያነሳው የመብት፣ የነፃነት፣ የዴሞክራሲና የፍትኃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነው” ይላሉ:: ከዚህ አንፃር ሲታይ ለአዋጁ መታወጅ ተጨባጭ ምክንያት የለም የሚል ሀሳብ አንስተዋል::

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ ዘላለም እሸቱ በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጋብዙ አካባቢዎች መኖራቸውን ቢያምኑም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ አዋጁን መጫን ተገቢ አይደለም ይላሉ:: መንግስት አካባቢዎችን ለይቶ ማውጣት ነበረበት፤ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጋብዝ ሁኔታ ተፈጥሯል ቢባል እንኳ አዋጁ ችግሩን ከምንጩ የሚፈታው እንዳልሆነ ሙያዊ ትንታኔ ሰጥተዋል::

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በባህሪው ለመንግስት ጉልበት ማግኛ መንገድ ነው:: አሁን የኢትዮጵያ መንግስት ያነሰው ጉልበት ሳይሆን በመደበኛው የህግ ማስከበር ሂደት ያሉ አማራጮችን በሚገባ አለመጠቀሙ ነው” ብለዋል::

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባሻገር ሌላ መንገድ እንደነበረ የሚጠቁሙት የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ዶ/ር ቃለ ወንጌል በበኩላቸው ሶስት የመፍትሔ ሃሳቦችን ይሰነዝራሉ:: አንደኛው በመንግስት ተጀምሮ የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር የማስፋት ለውጥ በግለቱ እንዲቀጥል ማድረግ የሚል ነው:: ይሁን እንጂ ከአዋጁ መውጣት በኋላ ለውጡ ስለመቀጣጠሉ ግልጽ ነገር የለም ባይ ናቸው:: ሁለተኛው አዲስ ምርጫን እንደ አማራጭ የሚያስቀምጥ ነው:: “በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይበልጥ ቅራኔውን ስለሚያባብሰው ይህንን የሚገነዘብ መንግስት ምርጫ ሊጠራ ይችላል::

የሌላው ሀገር ልምድም ይህንኑ ያሳያል” የሚሉት ዶ/ር ቃለወንጌል፣ “መንግስት፣ ሃገር ለመምራትና ለማስተዳደር የህዝብ ተቀባይነት የለኝም ብሎ ካሰበ አዲስ ምርጫ የሚጠራበት መንገድ አለው:: ይሁን እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ምርጫን በጥርጣሬ በሚመለከት ህዝብ ውስጥ አማራጩ ይሰራል – አይሰራም የሚለው ያከራክራል” ነው ብለዋል::

በሶስተኛ ደረጃ ያስቀመጡትን ግን ከሁሉም የተሻለው አማራጭ ሲሉ ይገልፁታል:: “ይህ ሶስተኛው መንገድ ኢህአዴግን ጨምሮ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተሰባስበው የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ማድረግ ነው:: ይህ ሁሉን አካታች በመሆኑ ጥሩ አማራጭ አድርጌ እወስደዋለሁ” በማለት አስረድተዋል:: ይሁን እንጂ እነዚህን አማራጮች ተግባራዊ ለማድረግ በመንግስትና በአመራሩ በኩል ድፍረት የተሞላበትን ውሳኔ የሚጠይቅ እንደሆነም ገልፀዋል::

የሄድ – መለስ ፖለቲካ

የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ዶ/ር ቃለ ወንጌል ኢትዮጵያ ወደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መግባቷ ተስፋ የተጣለበትን የፖለቲካ ምህዳር ያጠበዋል የሚል ስጋት አሳድሮባቸዋል:: “መንግስት የፖለቲካና ሌሎች እስረኞችን በመፍታት እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ያሳዩት ውሳኔ ትልቅ የለውጥ ጅምር ነው፤ ነገር ግን እርሱን ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከለውጡ ጋር ፈጽሞ ይጋጫል:: ይህ ደግሞ ህዝብን ለአላስፈላጊ ጥርጣሬና ጭንቀት እንዲሁም በፌዴራል እና በክልል መንግስታት መካከል ያለውን የፖለቲካ ሽኩቻ ያካርረዋል” ሲሉ አብራርተዋል::

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ:: መንግስት በአንድ በኩል እስረኛ እየፈታ በሌላ በኩል ለእስር የሚዳርግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ፍፁም ተቃርኖ ነው ብለዋል:: “እስረኞችን መፍታት በሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ የሁሉም ዜጐች መብትና ነፃነት የሚከበርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ዓላማ እንዳለው መንግስት ራሱ ገልፆ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መልሶ ማወጅ እየታሰበ ያለውን ለውጥ ውድቅ የሚያደርግ ተቃራኒ አካሄድ ነው” ብለውታል:: ከዚህ አንፃር ለውጥ ሳይሆን ወደ ሌላ ሁከትና ብጥብጥ የመግባት ዕድሉ ሰፊ ነው ባይ ናቸው::

የምጣኔ ሀብቱ እጣ ፈንታ

በአሁኑ ወቅት የሚገኘው የኢትዮጵያ ምጣኔሀብት በአለመረጋጋትና በምንዛሬ ቀውስ ውስጥ ይገኛል:: ይህ ባለበት ሁኔታ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የራሱን አዲስ ተጽዕኖ የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ነዋሪዎችና ምሁራኖቹ ይገልፃሉ:: ይሁን እንጂ በአዋጁ መታወጅ አንፃራዊ የንግድ እንቅስቃሴ መነቃቃት ይፈጥራል ብለው ተስፋ የሚያደርጉም አሉ::

በኩር ጋዜጣ ያነጋገራቸውና የባህርዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ብርቱካን ሉሌ የዚህ ተጋሪ ናቸው:: እርሳቸው፣ “ምንም እንኳ በአማራ ክልል ውስጥ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያሰገድዱ ሁኔታዎች የሉም” ብለው ቢያምኑም፣ በሌሎች አካባቢዎች የተነሱ አንዳንድ አለመረጋጋቶች ግን በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ላይ እክል መፍጠራቸው እንደማይቀር ሰግተዋል::

“በየቦታው የሚታዩ ግጭቶች፣ የመንገዶች መዘጋት፣ የነዳጅ እጥረትና ሸቀጣሸቀጥ እቃዎች ላይ የዋጋ ንረት አስከትሏል” የሚሉት ወ/ሮ ብርቱካን በሌላ አካባቢ የሚከሰተው አለመረጋጋት እኛንም የሚጐዳ ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊያረጋጋው ይችላል ብለው እንደሚያስቡ ገልፀዋል::

አቶ ስዩም ተሾመ ግን ጉዳዩን በተለየ አቅጣጫ ይመለከቱታል:: “የምጣኔሀብት ዕድገት እንዲኖር አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፍሰትና ተጨማሪ ምርት ተመርቶ እሴት ወደ ምጣኔሀብቱ ውስጥ መግባት አለበት:: ይሁን እንጅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውሰጥ በምትገኝ ሀገር ላይ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሀብት ገንዘቡን ለልማት ለማፍሰስ የደህንነትና የመተማመን ስሜት አይኖረውም” ይላሉ::

LEAVE A REPLY