ህወሃት፤ ዶ/ር አብይና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት መከልከል፤ ህዝቡና ሌሎችም/ሚኪ አማራ/

ህወሃት፤ ዶ/ር አብይና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት መከልከል፤ ህዝቡና ሌሎችም/ሚኪ አማራ/

ህወሃት ሰሞኑን ደብረጢወን ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት ይወዳደራል ብሎ ወሬ እያስወራ ነበር፡፡ ሲጀምር ደብረጢወን የፓርላማ አባል አይደለም፡፡ የፓርላማ አባልነቱን ያጣዉ የክልል መሪ ሲሆን ነዉ፡፡ ስለዚህ የሱ ወንበር አባዱላ ሙተዋል ወይም ጠፍተዋል ካላቸዉ ከ8ቱ ጋር ይደመራል፡፡የእስቸኳይ ጊዜዉን ፓርላማ ተገኝቶ መምረጡ እራሱ ህገወጥነት ነዉ፡፡ ሲቀጥል ህወሃት በህይወት ከቆየ አላማዉ ዶ/ር ቴወድሮስን እስኪመለስ ጠብቆ ኢህአዴግን ወደ ግንባር በማሳደግ ለረዥም ጊዜ መቆጣጠር ነዉ፡፡ ደብረጢወን ይወዳደራል ማለቱ ታክቲካል ነዉ፡፡ አንደኛ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዳይሆን የሚፈልጉት ዶ/ር አብይ ሳይሆን ቢቀር ሃላፊነቱን ከህወሃት ለማዉረድ ነዉ፡፡ እኛም ተወዳድረን አልተሳካልንም የለንበትም ለማለት ነዉ፡፡ ሁለተኛ በዚህ ሰሞን መካከለኛዉ የህወሃት ካድሬ ዉስጥ ለዉስጥ ጥያቄ እያነሱ ነበር፡፡ ህወሃት ስልጣኑን እያጣ ነዉ የሚል ፍርሃት እንዳደረባቸዉ ለድርጅት ሃላፊዎች ሲናገሩ ነበር፡፡ ስለዚህም እነሱን ለማረጋጋት የታሰበ ነዉ፡፡ ሶስተኛ ህወሃት አርጅቷል ተተኪ እንኳን የለዉም ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት የሚያቀርበዉ የለዉም የሚል ከተቃዋሚዉ በኩል ይሰነዘራል፡፡ ባጠቃላይ ደብረጺወን እንዲወዳደር የተፈለገዉ ስልጣኑን የምር ፈልገዉት ሳይሆን ይሄን ዉጫዊና ዉስጣዊ ግፊት ለመቋቋም የተደረገ አካሄ ነዉ፡፡ስልጣኑን እነሱን የማይጋፈጥ ታዛዥ የሆነ የሌላ ብሄር ወይም ድርጅት ቢይዘዉ ይመርጣሉ፡፡

ዶ/ር አብይን ለምን አልፈለጉትም

——–

ህወሃቶች ዶ/ር አብይን በፕሮፖጋንዳ ጠምደዉ ይዘዉታል፡፡ ሌሎችን ግን ሲደግፉ እንጅ ስለእነሱ መጥፎ ነገር ሲያወሩ አልታየም፡፡ከዉድድሩ እራሱን እንዲያገል ያላደረጉት ጫና የለም፡፡ ባብዛኛዉ ተቃዉሞዉ ከህወሃት የደህንነት ክፍል ይመነጫል፡፡ ጌታቸዉ አሰፋ (የደህንነት ሃላፊዉ) ዶ/ር አብይን ቢሮዉ ድረስ በመጥራት አነጋግሮታል፡፡ ዶ/ር አብይን ከአንዴም ሁለቴ ህወሃቶች ተጫዉተዉበታል/በድለዉታል፡፡ የመጀመሪያዉ እሱና ሶስት ሌሎች ጓደኞቹ (የትግራይ ሰወች ናቸዉ) ከወታደር ቤት እንደተመለሱ ሶስቱን ጓደኞቹ አሜሪካ ልከዉ ሲያስተምሯቸዉ እሱን አሜሪካ አንልክህም በማለት ከፈለክ ደቡብ አፍሪካ መሄድ ትችላለህ ብለዉት እዛ ሂዶ ከ ኮምፐዉተር ሳይንስ ጋር የተያያዝ ስልጠናወችን ወስዷል፡፡ ሲቀጥል ከኢንሳ ያለፍላጎቱ ወታደሮቹ አባረዉታል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ለማ ዶ/ር አብይን ለዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴርነት እጩ አድርጎ ቢያቀርበዉም ህወሃት አንፈልገዉም በማለቱ እሱም በዚህ አለመግባባት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርነት ተነስቶ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደ፡፡ ስለዚህም የበደለ ሰዉ ሁሌም ቢሆን ተበዳይን አያምንም፡፡ አንዱ ምክንያት ሁለትና ሶስቴ የበደልከዉን ሰዉ አለቃ አድርገህ አምነህ ልታስቀምጠዉ ባለመፈለግ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ምናልባትም ሪፎረም በማድረግ ከጨዋታ ሊያስወጣን ይችላል የሚል ፍርሃት ይመስላል፡፡

ህወሃትና ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ

——–

ብዙ ሱዉ ህወሃት ወታደሩ ስላለዉ ጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ቢሰጥ ምን ይሆናል የሚል ነገር ያነሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንደ ክልል ፕሬዝደንት አይደለም፡፡ የክልል ፕሬዝደንት ካልተመቸኸ ታስረዋለህ ወይም ታባረዋለህ አለያም አፈ ጉባኤ ወይም አምባሳደር አድርገህ ትልከዋለህ፡፡ ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስቴሩን እንደፈለክ አታደርገዉም፤ አስራለዉ ቢል ከአገር አልፎ አለምቀፋዊ ዉግዘት ይደርስበታል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚሆን ሰዉ በተለይም አድር ባይ ካልሆነ ስልጣኑን ቀስ እያለ ሲያደላድል ወታደሩንም ይቆጣጠራል አሱ በሚፈልገዉ መንገድም እንደገና ሊያደራጀዉ ይችላል፡፡ስለዚህም ህወሃት የእምነት ማጣት ነዉ፡፡ እንኳን አይደለም ዶ/ር አብይን ህወሃት የብአዴኑን ደመቀን እንኳን ማመን አልቻለም፡፡ እሱን ስላላመነ ደህዴንን ሶስቴ የመረጡትን ሰዉ በማስቀየር ሽጉጤን ወደፊት እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ህወሃት በፊት አሁንም ቢሆን አምርሮ ከሚጠላቸዉና ከማያምናቸዉ አንዱ የአማራ ህዝብ ነዉ፡፡ አሁን ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ጨምሯል፡፡

ኦህዴድና የኦሮሞ ተቃዋሚወች

——–

ባለፈዉ ኦህዴድ የእነ ጃዋርን አጀንዳ ሁሉንም ወስዶ (hijack አድርጎ) ከዛም በተጨማሪ የፖለቲካ ፍኖተካርታዉን በኢትዮጵያዊነት መስመር በመቅረጽ ለህዝቡ ስለቀረብ ያልታሰበና ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ኦሮሚያ ዉስጥም መለወጥ አለባቸዉ ያላቸዉን ነገር በግልጽ በማቅረብ የህዝቡን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃም የከረመዉን የጥላቻ ፖለቲካ ታምኖበትም ይሁን ለታክቲክ ወደ ጎን በመተዉ ጥሩ የህዝብ ድጋፍ አግኝተዉበታል፡፡ አሁን ደግሞ ተራዉ የጃዋር ይመስላል፡፡ ጃዋር ወደ ሴንተር ፖለቲካ (ለታክቲክም ይሁን ዉስጣዊ ፍላጎት) በመምጣት የኦህዴድን የፖለቲካ ፍኖተካርታ በተራዉ hijack (የመንጠቅ) ስራ እየሰራ ያለ ይመስላል፡፡ ኦህዴድ በኢትዮጵያ ደረጃ ይሄን ያህል ድጋፍ ካገኘ እኔስ የማላገኝበት ምን ምክንያት አለ አይነት አካሄድ ነዉ፡፡ በዚህም ከኦህዴድ ጋር መፈራቀቅ ታይቷል ከዛም አልፎ የኦህዴድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሁን ከማለት ወደ ትራንዚሽናል መንግስት ይቋቋም ተቀይሯል፡፡

ብአዴን

——

ብአዴን ባህርዳር ተወሽቆ ኖሮ ሰሞኑን ተደናብሮ አብዛኛዉን ጊዜዉንና አትኩሮቱን አዲስ አበባ ላይ አድርጓል፡፡ ያም ሆኖ ብአዴን የሚጠቅም ነገር ያመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ብአዴን የአማራን ህዝብ ምናልባትም ለ100ኛ ጊዜ እንደገደለን የምንቆጥረዉ ሽፈራዉ ሽጉጤን ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሁን ብሎ ድምጹን ሰቶ የዉሎ አበሉን ተቀብሎ የመጣ ቀን ነዉ፡፡ ሽጉጤ ማለት በራሱ የዱካ ፊርማ በተፈረመ ደብዳቤ 15 ሺህ አማራ ከጉራ ፈርዳ አፈናቅሎ ዛሬ በየከተማዉ የቀን ሰራተኛ ሁነዉ የሚኖሩ፤ ከ 600 በላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ እንዲሁም ከ250 በላይ ለሞት እንዲዳረጉ ያቀነባበረ ሰዉ ነዉ፡፡

ህዝቡ

——-

ህዝቡ ያለ መሪ መንግስትን በእርግጥ ከሚገባዉ በላይ ተጋፍጦታል ምናልባትም ህዝቡ ማድረስ ያለበት ቦታ ላይ እየሞተም እየደማም አድርሶታል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ጫፍ በደረሰ ጊዜ ወደ አንድ በማሰባበስብና አመጹን ቅርጽ በማስያዝ ወደ ዉጤት ሊለዉጥ የሚችል መሪ ያስፈልገዋል፡፡ ህዝቡ አሁን ባብዛኛዉ እየተመራ ያለዉ በራሱና በአክቲቪሰቶች ነዉ በፖለቲካ መሪ አይደለም፡፡ የፖለቲካ መሪ ከሶስት ቦታወች ሊመጣ ይችላል፡፡ ከህዝቡ፤ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከመንግስት የሚያፈነግጡ፡፡ ከህዝቡ እስካሁን አልወጣም (የወጡትም በእስርና በጫና ህዝቡን መምራት ይከብዳቸዋል)፤ ከተቃዋሚ ድርጅቶችም አልመጣም፡፡ በተቃራኒዉ ከራሱ ከመንግስት ለማፈንገጥ የሞከሩ ሰወች የተሻሉ ሲንቀሳቃሱ ታይተዋል፡፡ በ2007/8 የእነ ገዱ ቡድን በ2009/10 የእነ ለማ ቡድን ከወትሮዉ ለይት ባለ መልኩ ከመንግስት ይልቅ ወደ ህዝብ የመወገን ሁኔታወች ነበሩ/አሉ፡፡ አሁንም ሁነኛ መሪ ያስፈለጋል፡፡ አክቲቪስት ህዝብን ያነቃንቃል፤ ያስተምራል፤ ህዝቡ ለመብቱ እንዲቆም ያደርጋል፡፡ መሪ ደግሞ የተነቃነቀዉን የህዝብ ሃይል በማስተባበር፣ ፖለቲካዊ አጀንዳ በመቅረጽና የጋራ ግብ በማስቀመጥ ወደ ፍሬነት ይቀይራል ማለት ነዉ፡፡

LEAVE A REPLY