ቃሉ የሕዝብ ነው። ቃሉንም በተግባር የሚተረጉመው ሕዝብ ነው። የወንዝ ውሃ ሽቅብ እንደማይፈስ ሁሉ፥ ይህም ቃል ወደ ተግባር ሳይቀየር ይቀለበሳል ብሎ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። ይልቁንስ ይህን ቃል ለመተግበር የዶ/ር አብይ ድርሻ ምንድነው ብሎ አውቆ በዚያው ሚዛን ብቻ እርሳቸውን መመዘን ያስፈልገናል። ለሕዝብ ታማኝ ባይሆኑ፥ እሳቸው ከታሪካዊነት ይጎድላሉ እንጂ የሕዝብ ቃል ዕውን መሆኑ አይቀሬ ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ የሚናገሩት ቃል እርሳቸው የፈለሰፉት ስለሆነ አይደለም የተወደደው። ቃሉ የሕዝብ ቃል ስለሆነ ነው እንጂ።
ይህ ሰሚ ያጣ ሕዝብ በትግሉ የራሱን ቃል የሚያስተጋባ ጠ/ሚ ሊያመጣ ቻለ። ታዲያ ይህን ቃል የዶ/ር አብይ የግል ንብረት ተደርጎ፥ ቃል ዋጋ የለውም ብሎ ቃሉን ማጣጣል ለኢትዮጵያ አይጠቅምም። የውልጃ አብሳሪ የሆነ ቃል በውልደት ቀን ዋዜማ ሲሰማ፥ በተስፋና በትጋት ይህን የሕዝብ ቃል በክብር መያዝ ይገባል። ይህ ታላቅና አስገራሚ ሕዝብ ቃሉን በአደባባይ ካሳወጀ በሁዋላ፥ ይህ ቃል አይተገበርም ማለት የቃልን ምንነትና የቃሉ ነፀብራቅ የሆነውን ሕዝብ ማንነት ያለማወቅ ነው።
ከአሁን በሁዋላ በምድራችን የሚሆነውን ነገር ለማወቅ ከተፈለገ ወደ ፊት በማየት ማገናዘብ እንጂ ወዳለፈው ታሪካችን እየተመለከትን ሽንፈትን ማስተናገድ አይበጅም። በመጀመሪያ ቃል ተወለደ። ይህ ቃል ቀጥሎ ዲሞክራሲን ይወልዳል። ዲሞክራሲ ሁሉን የኢትዮጵያ ልጆችን አሳትፎ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ያስወልዳል። ስለዚህ ይህ የታወጀው ቃል የምጥ መጀመሪያ ነው። ያለፈውን የእርግዝና ወቅት ሳይሆን አሁን ያለውን አዲስ የምጥ ሂደት ማስተናገድ ይገባናል። መወለድን ማስተጓጎል ቀርቶ ማዘግየት የሚቻልበት ወቅት ላይ አይደለንም።
እናስተውል። አሁን ቸኩለን ስለ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ማውራትና መጠየቅ አንችልም። አሁን ዶ/ር አብይን በቅድሚያ የዲሞክራሲ አዋላጅነታቸውን ግዴታ እንዲወጡ ብቻ በተጠያቂነት መያዝ ይኖርብናል። ከዚያ ዲሞክራሲ ተቃዋሚ የሆኑትን ሃይላት ወደ አማራጭ ሃይልነት ቀይሮ ተባባሪ አዋላጅ ያደርጋቸዋል። ያኔ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ያሳተፈ ሂደት አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንድትወለድ መቻልን ያመጣል። ሁሉንም የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚዳኝ ሕዝብ ነው። ለዚያ ዲሞክራሲ የመጀመሪያው መሰረት ነው። ስለዚህ ይህን የሕዝብ ቃል ይዘን ዲሞክራሲ በቅድሚያ ይወለድ ዘንድ ግድ እንበል።
ኢትዮጵያን በጎሰኝነት ከፋፍሎ ሊበትን ጠላት ያቀደው በቃል ነበር። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ወደሚጠብቃት ታላቅ ክብርና ሞዴልነት የሚወስዳትን ጉዞ የሚያስጀምረውም በቃል ነው። የአዋላጅነት ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ዘብ መቆም እኛም ከአዋላጆቹ ጎራ እንድንመደብ ያደርገናል። ዶ/ር አብይን በብዙ ጉዳይ እያዋከብናቸው እና አፍራሽ ቃል በመጠቀም ጥሪያቸውን እንዳይወጡ ለጠላት መጠቀሚያ እንዳንሆን እንወቅበት። በዶ/ር አብይ አዋላጅነት ሊሆን ያለውን ድል እንቅፋት እንዳንሆን መጠንቀቅ እጅግ ያስፈልገናል። ይህን የኢትዮጵያ ልጅ ለመውቀስም ሆነ ለማሞገስ አንዱንና ብቸኛውን ዲሞክራሲ ላይ ትኩረት በማድረግ መሞገትና ተጠያቂ ማድረግ መልካም ነው።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢሜል ethioStudy@gmail.com