ሚያዝያ 2010
ዶር. ዓቢይና አቶ ለማ መገርሳ በኢትዮጵያ መድረክ ላይ መታየት ሲጀምሩ ኢትዮጵያ የተአምር አገር መሆንዋን አስታወስሁና እግዚአብሔር ፊቱን ወደኢትዮጵያ መመለሱን ተረዳሁ፤ ከዚያም በላይ ያለፈው ጠቅላይ ሚኒስትር እናቱን በመውቀስና በመመጻደቅ ጀመረ፤ አዲሱ ደግሞ እናቱን በማወደስ መጀመሩ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት በአደባባይ ደጋግሞ በመግለጹ አከበርሁት፤ አከብረዋለሁ፡፡
ከዚህ በፊት ሦስት ጊዜ በፌስቡክ የጻፍሁትን ልድገመው፤››
አንድ፤ በ1965 በወሎ ችጋር ዘመን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች እርዳታ ለማድረግ በምንሯሯጥበት ጊዜ አንዳንድ የኢሕአፓ አባሎች ለተራቡት እርዳታ መሰብሰብ አብዮቱ እንዳይመጣ ማድረግ ነው እያሉ ይቃወሙን ነበር፤ ነፍሱን ይማረውና አብርሃም ደሞዝና እኔ ተቆጥተንና አስፈራርተን አደብ እንዲገዙ አድርገናቸው ነበር፤ ዛሬ ደግሞ በዓቢይ ሹመት መደሰቴን በመግለጼ የሚሳደቡ አሉ፤ ስለዓቢይ የጻፍሁት ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆኑ በፊት ነበር፤ አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን ያደረገውን ንግግር አዳምጫለሁ፤ ስለዚህም ቀድሜ በተናገርሁት እጸናለሁ፤ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ አረመኔ አይደለም፡፡
ሁለት፤ በአሁኑ ጊዜ በዶር. ዓቢይ ላይ ብዙ ቅሬታዎች ይሰማሉ፤ ለእኔ እንደሚታየኝ ሁለት መነሻዎች ያሉ ይመስለኛል፤ አንዱ መነሻ ዓቢይ የተመረጠበት ሁኔታ ከወያኔ (ኢሕአዴግ) መመሪያ የወጣና ወደአልተሸበበ ነጻነት የሚያመራ መስሎ መታየቱ በወያኔ መንደር ሽብር እንደሚያስነሣ ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ሁለተኛው የተለመደው የኢትዮጵያውያን የፖሊቲካ ባሕርይ ነው፤ የተፈለገው ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ከመጠለያ ስር አሾልከው እያዩ ከደመናው በላይ ወጥተው የጠራ ሰማይ ለማየት የሚሞክሩ ናቸው፤ የደመናው ግርግርና ሽብር አይመለከተንም የሚሉ ይመስላሉ፤ ዓቢይ አንድ ሰው ነው፤ ዓቢይ ከነቡድኑ ትንሽና ደካማ ነው፤ ይህንን እውነት መገንዘብ ከተመልካችነት ወደቆራጥ ተሳታፊነት መሸጋገርን ይጠይቃል፤ የሚያስፈራውና የዳር አጨብጫቢነትን የሚጋብዘው ይህ ነው፤ የዳር አጨብጫቢነት ውስጥ ያሉት ሁሉ ወደተግባር ተሳታፊነት ቢሸጋገሩ የዓቢይ ዓላማ የማይሳካበት ምክንያት የለም፤ ካልሆነም ለድጋፍ የተገኘው ኃይል የታወጀውን ለመጠበቅም ይረዳል፡፡
ሦስት፤ ዶር. ሰማኸኝ፣ ያለህ ስጋትና ጥርጣሬ ይገባኛል፤ ነገር ግን ያለነው 27 ዓመታት ሙሉ ውል በሌለው በዘፈቀደ የተገመደ የመሀይሞች የፖሊቲካ ውስብስብ ውስጥ ነው፤ አንድ በልልኝ፤ ዓቢይ የኦህዴድ ሙሉም ባይሆን ሰፊ ድጋፍ አለው፤ የኦህዴድን ቅርጽም ልብ ብለህ ግንዛቤህ ውስጥ አስገባው፤ ሁለት በልልኝ፤ ከዚህ በተረፈ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች (በስም የማላነሣቸው አውቄ ነው፤) ሊኖር የሚችለውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ዓቢይ 27 ዓመት ሙሉ በወያኔ የተፈተለውን የመንደር ፖሊቲካ መጋረጃዎች ሁሉ ቀዳዶ ሰው መሆንን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ማዛመዱን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈለልጋል፤ ይህ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ በኃይል ስቧል፤ ሦስት በልልኝ፤ የዓቢይን ልምዱንና ትምህርቱን ስናይ ለየዋህነት ቦታ ያለ አይመስለኝም፤ ከጎኑ ለማና ጓደኞቹም አሉ፤ አራት በልልኝ፤ አሜሪካም ደግፎታል፤ አምስት በልልኝ!
“““““““““““““““““““““““““““
ዶር. ዓቢይ በተለያዩ ስፍራዎች ያደረጋቸውን ንግግሮች በጥሞና አዳምጫለሁ፤ በተለይም ከሀብታሞች ጋር፤ አንድም ቦታ ሀሳቡ ሲደናገር ወይም ሲዛነፍ አልሰማሁም፤ በዚህም የእውቀቱን ስፋት፣ የአእምሮውን ምጥቀት፣ የኅሊናውን ጽዳት፣ የወኔውን ብርታት፣ የዓላማውን ጥራት፣ የዘዴውን ሥልጡንነት በጣም እጅጉን አደንቃለሁ፡፡
ለእኔ ኢትዮጵያ የሰውም ሆነ የአእምሮ ችግር ኖሯት አያውቅም የሚለውን እምነቴን አረጋግጦልኛል፤ የአገዛዝ ጫማ የኢትዮጵያውያንን ራስ ጨፍልቆ ረግጦ አመከነው እንጂ አለን፤ ደርግ ከአገዛዝ አወጣችኋለን ብሎ አሥራ ሰባት ዓመት ረግጦ ገዛን፤ ወያኔ ከደርግ አገዛዝ አወጣችኋለን ብሎ ይኸው እየረገጠ ሲገዛን ሠላሳ ዓመታት ሊሞላው ነው፤ አሁን ዶር. ዓቢይ አህመድና አቶ ለማ መገርሳ ወደአዲስ አቅጣጫ ሊመሩን የተዘጋጁ ይመስላሉ፡፡
ዶ
ር. ዓቢይና አቶ ለማ በየትኛው መንገድ እንደሚመሩን ገና በትክክል ባናውቅም መድረሻቸው አሁን ካለንበት የተለየ እንደሚሆን ግልጽ አድርገዋል፤ ይህ አስተያየታቸው ተቃራኒ የሰላም ጥያቄዎችን አስነሥቷል፤ ሰላም ምን ማለት ነው በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት፡… የዓየር አለመኖርና አደገኛነቱ የሚታወቀው ዓየር ሲታጣ ነው፤ ዓየር ሳይኖር ሞት፣ ሰላም ሳይኖር ሞት ነው፤ ጸረ ሰላም የሚሆነው ሬሳን ማንቃት ነው። ወይስ ሞትን ማወጅ። ሬሳን ማንቃቱን አብዮተኛነት የሚሉት አሉ፤ ሞትን ማወጅን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሉት አሉ፤ በሁለቱም በኩል ለሰላም የሚደረገው ጩኸት ሰላምን የሚነሳ ነው፤ የሰላም ጠንቅ ሆነው ሰላምን መሻት የአገዛዝ ማዘናጊያ ዘዴ ነው፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳለ ነው፤ ሆኖም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹም-ሽር አድርጓል፤ በዚህ ሹም፣ሽር የወያኔ ቀኝ እጅ የሚታይ አይመስልም፤ ሆኖም ሹም-ሽሩ የዓቢይ የመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ መሆኑ ነው፤ ለእኔ ቅር ያለኝ የሴቶች ቁጥር ማነስ ነው፤ በመጀመሪያው የወያኔ ስብሰባ ላይ ወያኔ አንድም ሴት አልነበረውም፤ ይህንን ጉዳይ ለመለስ ዜናዊ አንሥቼበት ነበር፤ በግዮን ሆቴል አንዲት (እንደነገረችኝ) የአሥራ አራት ዓመት ልጅ ቁመትዋን የሚያህል ጠመንጃ ተሸክማ አየሁ፤ አነጋገርኋት፤ ብዙ እንደእስዋ ያሉ ሴቶች ልጆች ነበሩ፤ በሐምሌው ጉባኤ ላይ አልተወከሉም ነበር፤ መለስ ዜናዊ ስሕተት መሆኑን አምኖ እንደሚታረም ነግሮኝ ነበር፤ በዚህ በኩል የዓቢይም ሹመት ከመለስ ዜናዊ እምብዛም አልተሻለም፡፡
አሁን በዓቢይ ላይ ከየአቅጣጫው የሚወርደው የነቀፌታ ናዳ ‹‹የአብዮታዊነት ውጥረት›› ከስድሳዎቹ እየተወራረሰ የመጣ የኩርፊያ ውጤት ይመስላል፤ የአጼ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ሲወድቅ ስንት ወራት እንደፈጀ የማያስታውሱ ወይም የማያውቁ ሰዎች ዛሬ በሃያ አራት ሰዓት ለውጥ ማየት ይፈልጋሉ፤ ያውም እንደወያኔ ያለውን መዥገር ለማላቀቅ! በየካቲት 1966 ጸሐፌ ትእዛዝ አከሊሉ ስንብት አቀረቡ፤ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ጀኔራል ዓቢይ ታጩ፤ ልጅ እንዳልካቸው ተሾመ፤ አልቆየም፤ በልጅ እንዳልካቸው ተተካ፤ ከዚያ በኋላ ጀኔራል ተፈሪ በንቴ፣ ጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ወንበሩ ላይ ለአጫጭር ጊዜዎች ወጥተው ወረዱና ኮሎኔል መንግሥቱ እስቲኮበልል ድረስ ተቀመጠበት፡፡
ዓቢይ ገና መጀመሩ ነው፤ ራሱ እንደተናገረው ‹‹የመጀመሪያ›› ሥራውን እየሠራ ነው፤ ገና አንድ እግሩን ብድግ በማድረግ ላይ ነው፤ መሮጥ ቀርቶ መራመድ አልጀመረም፤ ሊጠልፉት ያደፈጡ ብዙዎች ሳይሆኑ አይቀሩም፤ በያለበት እየዞረ ንግግር የሚያደርገውም ከአደገኛ ጥልፊያ ለመዳን ወገኖችን በመፈለግ ይመስለኛል፤ እኔ እንደምገምተው በዶር. ዓቢይ ላይ የከረረ ነቀፌታ የሚሰነዝሩት የቅርብ ደጋፊዎች ሊሆኑ የሚችሉት ይመስሉኛል፤ እንደተገነዘብሁት እስካሁን ዶር. ዓቢይ የነካው ቁስል በአጠቃላይ የወያኔን ሥልጣን፣ በተለይ ደግሞ የአማራን የወልቃይት አካል ነው፤ (በነገራችን ላይ የወልቃይት-ጠገዴ ጉዳይ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በቱርክና በግሪኮች መሀከል በቱርክ የተሠራው ሸርና እስከዛሬ ሙሉ በሙሉ ያልተፈታው ችግር ግልባጭ ነው፤) ከጎሠኛ አመለካከት ከተወጣ ሁለቱም ሕመሞች የሚከስሙ ናቸው፡፡
የዜግነት ጉዳይ ያልገባቸው ፖሊቲከኞች ዛሬም ያሉ ይመስላል፤ የአንድ አገር ሕዝብን በዘር፣ በጎሣ፣ በሃይማኖት፣ በሥራ፣ ወይም በሌላ ማናቸውም ነገር ሳይሆን በሕግ ብቻ እንደዜጋ አንድ ሆነው የሚቆሙ ናቸው፤ዜግነት አንድን ሰው የአንድ አገር ሕጋዊ ባለቤት ያደርገዋል፤ አንድን ሰው ከሌሎች የዚያው አገር ዜጎች ጋር የአገር ሉዓላዊነትን እንዲጋራ ያደርገዋል፤ የአንድ አገርን ሕዝብ በሙሉ በአንድ የተደለደለ መድረክ ላይ ሊቆሙ ይገባል ብንል በዜግነት ነው፤ በሕግ ተሳስረዋልና በአንድ ዜግነት በቆሙ ሰዎች መሀከል የሕግ ልዩነት የለም፡፡
ገና ከአሁኑ በዓቢይ የቀናት አገዛዝ ጥሩ የለውጥ አዝማሚያዎች ይታያሉ፤ ዋናው በዜና ማሰራጫዎች ላይ የሚታየው ነው፤ በዚያው መጠን ሕዝቡም በነጻነት ሀሳቡን የመግለጽ ልምምድ የሚያደርግ ይመስላል፤ በዜና ማሰራጫዎቹ በኩልም የማታለሉ ዘዴ እየቀጠለ ይመስላል፤ በአንድ በኩል የነጻነት በር ሲከፍቱ በሌላ በኩል በር ይዘጋሉ፤ ለምሳሌ የሕዝብን ድምጽ ለማሰማት በሚል ሰበብ ከመንገድ የሚመርጧቸው ሰዎች እነሱ የሚፈልጉትን መልስ የሚሰጡትን ብቻ ይመሰላል፡፡
መጨረሻውን ለማየት ቢያንስ ስድስት ወራት እንጠብቅ፡፡