መታሰቢያነቷ ለድምጻዊ ኮይሻ ሴት የማይታይ ክብር /በግሩም ተ/ሀይማኖት/

መታሰቢያነቷ ለድምጻዊ ኮይሻ ሴት የማይታይ ክብር /በግሩም ተ/ሀይማኖት/

ኡኡኡ አትበሉ..ከቶም አታልቅሱ

ወከባ አታንግሱ..ያልሆነ አታልብሱ
ከሞተ በኋላ ተዉ አታወድሱ
አትዘክሩት ይቅር ስራው ይዘክረው
መታሰቢያ ምሽት
ሻማውስ ምኑ ነው?
ቢበራ ባይበራ ከሞት ላያስቀረው..
ለሰማይ ቤት መንገድ
ብርሃን አይሆነው?
ለዛውም ለዛውም…
በቲፎዦ ሆኖ ዝክር ማጨብጨቡ
የግጥም ምሽቱ በግጥም መጠበቡ
ስንቱ ወዳጅ ያጣ ስራው የነጠረ
ጥበብን ጠብቦ ለታሪክ ያኖረ
ሆይ ሆይ የሚልለት ወገን በማጣቱ
ስሙ ይቀበራል ስራው ግን ሀውልቱ
ለነገሩ …
ሲዘክሩ ውለው ሲዘክሩ ቢያድሩ
እሱ ያላወቀው ያልቀመሰው ክብሩ
ያልሆነውን አርገው ቆልለው ቢያወሩ
ታሪክ አበላሽተው ታሪክ ያጠቁራሉ
የሞተ አወድሰው ስም ይፈልጋሉ…
ይልቅ
በቁም ዋጋ ሰጥተን በቁም እናክብረው
በስራው አድንቀን በስራው እንመዝነው
በቁም
እንቅፋት የሆነው የስራው ደመኛ
የማያውቀው ሁሉ ሲያደርገው ጓደኛ
ሩህሩህ፣ ለጋስ፣ አዋቂ፣ የተመራመረ
ሰው አክባሪ ሀገሩን ወዳድ…..ነበረ
….ነበረ
….ነበረ
…ነበረ ልትሉት በነበር አታስቀሩት
በማያየው ክብር ከቶ አትጀቡኑት
በቁሙ እያለ በእነተወ መስክሩለት
ተቸግሮ ሳለ በህይወት ዘመኑ
አንድም አጥቶ ይሆናል
የሚቆም ከጎኑ
ብቸኝነት ይዞ አዙሮ አንጎላጆ
ችግርና ማጣት ሆኖ መቀናጆ
በላዩ ላይ ሲዘምት ያ-ሁሉ መከራ
አይዞህ ባይ ጠያቂ ጠፍቶ ባልንጀራ
ልክ ሞቱን ሲሰማ ሁሉ ወዳጅ ሆኖ
በጥሩ ሲስለው መጥፎነቱን ከድኖ
ሴጣን ከነበረም በመላዕክት መስሎ
ባልዋለበት ቦታ ባልሆነው ተስሎ
ያልሆነውን አድርጎ ያልሆነውን ኩሎ
ያን ሁሉ ጋጋታ ከምትጭኑበት
በቁሙ እያለ በቂ ፍቅር ስጡት
በስራው መዝኑት
በስራው አክብሩት

ኩይሻ ሴታ የዜና ሽፋን ሆነ..ግን አንድ ሰው ሳይጠይቀው ሞተ

የወላይትኛ ዜማን በዘመናዊ መንገር እንዲሰማ ፈር ቀዳጅ የሆነው ኩይሻ ሴታ ታሞ ሞተ። ከሞቱ አሟሟቱ የከፋ ነበር። ራስ ደስታ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ለአምስት ቀናት የመጣል ያህል ተኝቶ ነው የሞተው።

ኩይሻ ሴታ ከመጀመሪያው ጀምሮ የተታለለ ስለሆነ እንዲሁ እንደተበሳጨ እንደጠጣ መውደቂያው ሳያምር አለፈ። ዛሬ እና ትላንት ግን ኢቲቪ ሳይቀር እየተቀባበሉ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል አሉ።
እንዴት ያሳፍራል???? አምስት ቀን ሙሉ ማን ጠየቀውና??

LEAVE A REPLY