‹‹እማማ ፋጡማ እና እማማ ደብሪቱ›› /መላኩ አላምረው/

‹‹እማማ ፋጡማ እና እማማ ደብሪቱ›› /መላኩ አላምረው/

‹‹ሰማሽ ወይ ፋጡማ የኛም ጦሙ ገባ
በይ እንሂድና… ከካቡ ጠብቂኝ በተስኪያን ስገባ
የእኛው ቅዳሴ ታለቀ በኋላ ወደ መስጅድ ሄደን
ስግደትሽን ሰግደሽ አዛኑ እንዳለቀ እንመለሳለን
ካፈጠርሽ በኋላ ምሽቱን ከእኔ ቤት ቡና እንጠጣለን…

እንደተለመደው የማርያምን ቡና
እንጠጣዋለን አንችው ታፈይና… ››
እያለች ደብሪቱ ስትነግር ለፋጡማ
ፋጡማም በፍቅር ካጠገቧ ቆማ…

‹‹ውይ ደብርየዋ ወላሂ ልክ ነሽ ዛሬ እኮ ማርያም ናት
ነይማ ቁጭ በይ ጧፍ እንድትገዛልሽ ሃሊማን ልንገራት
…ማነሽ ሃሊማየ ንሽማ ሮጥ ብለሽ ከሱቁ ጣፍ አምጭ
በኋላ ከእኛ ጋር ከነደብርዬ ቤት ቡና እንድትጠጭ
ለማርያም ቅዳሴ እንዳይረፍድባት ቶሎ በይ ሩጭ…››
ትላለች በፍቅር ሙድሊሟ ፋጡማ
ክርስቲያኗ ደብሬ ካጠገቧ ቆማ።

ቅዳሴው ከደብር አዛኑ ከመስጊድ ካለቀ በኋላ
እንዲህ ማርያም ስትሆን ከነደብሪቱ ቤት ቡናው እየፈላ
ጣፋጭ ወጋቸውን እየተጫወቱ
አንዳንዴ እየሳቁ…
አንዳንዴ በሀዘን ደረት እየመቱ
ሲያወጉ ሲያወጉ… ጨለማው ሲጠና
‹‹በይ ልሂድ ደብርዬ… ውይ ጨልሟልና
በጊዜ ልተኛ ጉልበቴ ለስግደት አርፎ እንዲጸና››
ትላለች ፋጡማ…
ለመራመድ ቆማ…
‹‹ውይ ውይ ፋጡማዬ ትንሽ አትቆይም?
ከማርያሙ ጣዲቅ ጨምረሽ አትበይም?››
ትላለች ደብሪቱ…
ሰዓቷን ስታየው ተጋምሷል ሌሊቱ።

‹‹አይ ደብሪቱ ደሞ…
ቆይ ትይኛለሽ እንደዚህ ጨልሞ?
ይልቅ ደና እደሪ…
ነገ ከእኔ ቤት ነው ለቡና እንዳትቀሪ፤››
‹‹እንግዲህ እምቢ ካልሽ አንችም ደና እደሪ
ባይሆን ቆይ ልሸኝሽ ደሞ እንዳትፈሪ….››

እማማ ደብሪቱ ከእማማ ፋጡማ
ሚጫወቱት ሁሉ ሩቅ እየተሰማ….
ላለመለያየት እንደተገናኙ
በድቅድቅ ጨለማ እየተሸኛኙ…
ደብሪቱ እንዲህ አለች በፋጡማ ጆሮ
‹‹እንዲያው ፋጡማዬ የዚች የሃሊማ ጡቷ ተወድሮ
ለመዳር ደርሳ ሳል ዝም ብለን ምናያት ምን ነካን ዘንድሮ?
ለምን ለእህቴ ልጅ ለእስጢፋኖስዬ…
ሚስቱ አትሆንም ልጅሽ ሃሊማዬ?››
ፋጡማ እየሳቀች…

‹‹አሂሂ ደብርዬ… የዘመኑ ልጆች እንደኛ መስለውሽ?
የውልሽ ባለፈው እሁድ በጠዋቱ መምሬ መጡልሽ
‹እንግዲህ ደብርዬ ሃሊማን ስናያት ለጋብቻ ደርሳ
ለወልደ ሥላሴ ልንጠይቅ መጣን ያንችን እጅ ልንነሳ›
ብለው ቃላቸውን ሳይጨርሱ አውርተው ለካስ ሰምታ ኖሮ
ሮጣ በመግባት ካጮለቀችበት ከሳር ቤቱ ጓሮ…
‹ምነዋ መምሬ ደግሞ ብለው ብለው
ክርስቲያን ሊያጋቡኝ ሃይማኖቴን ጥለው?›
ብላ አትጮህ መሰለሽ ህጣኗ አፍ አውጥታ
እርሷ እንኳን በሃቅሟ እናንተን እና እኛን በእምነት ለያይታ
ብቻ ምን አለፋሽ የዘንድሮ ልጆች ምናቸውም አይጥም
ፍቅር አንድነት ትተው ሚናገሩት ሁሉ በጆሮ አይዋጥም።
እንኳን ሊኖርና እስላም ከክርስቲያን ተጋብቶ ተፋቅሮ
በዘር አንድ ካልሆነ እርስ በርሱም መጋባት ቀረ እኮ ዘንድሮ
ብቻ እርሱ አላህ በጎውን ቀን ያምጣ እንጅ ምን ይባላል
ለእኔማ እስጢፋኖስ ከማንም ከማንም ለሃሊም ይሻላል››
በማለት ፋጡማ ነገሩን ሲያብራሩ
የደብሪቱ ዓይኖች ነጭ እምባ አቀረሩ
‹‹ይሁና እንግዲህ ጭንቅ አማላጅቱ በጎውን ቀን ታምጣ
እንዲህማ ካለች ሃሊማን ጥየቃ ቃልም አላወጣ
እርሷ እኮ ልጄ ናት… ከብልትና ጡትሽ ወተቱን ብታጣ
ከእቅፌ ማደጓ ጧትና ማታ ጡቶቼን መጥምጣ…
እናም ሃሊማየ ጡቴን ጠብታ አድጋ እንዳትቀየመኝ
ዝም ብል ይሻላል ሌላ ሰው ሲያገባት በብርቱ እያመመኝ
ብቻ እርሱ ይሁነን…. ዘመኑማ ከፍቷል
ትውልዱ ዘር ቆጥሮ ፍቅርን ዘንግቷል
ሼሁና ካህኑ ማስታረቁን ትቷል…
ብቻ እርሷ ትሁነን የጭንቅ አማላጇ
ዞትር ምማፀናት ወድቄ ከደጇ….››
ደብሪቱ አለቀሰች…
ፋጡማ በፍቅር እንባዋን አበሰች።

ኢትዮጵያ ሀገሬ ልዩ ነበርሽ ምድሬ
እንዲህ ነው የኖሩት ፋጡማና ደብሬ።
—-


(ዛሬ ምሳ በልተን ከሥራ ባልደረባዬ ከአህመድ ጋር ቡና እየጠጣን እያለ ይህንን ፎቶ ከቤተልሄም ሀብቴ ገጽ ላይ አየሁትና ትንሽ ተከዝሁ፡፡ አንደኛዋ ሙስሊም አንደኛዋ ክርስቲያን እንደሆኑ በማመን ‹ፋጡማ እና ደብሪቱ› ብዬ ሰየምኋቸው፡፡ በፎቶው በኩል ውስጤን ንጦ የተሰማኝን ስሜት የምገልጽበት የቅርብ ሀብቴ ግጥም ነውና ይህችን ጽፌ <እንደወረደ> አጋራኋችሁ፡፡
ሰላምና ፍቅር ይብዛልን !!!)

LEAVE A REPLY