በመስቀል አደባባዩ ቦንብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው ተባለ

በመስቀል አደባባዩ ቦንብ ፍንዳታ የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው ተባለ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድን  ለመደገፍ በወጡ ሰልፈኞች ላይ በደረሰው የቦምብ ጥቃት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ  አምስት ግለሰቦች ላይ ክስ ሊመሰረት መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድን ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ እንዳስታወቀው  በተጠርጣሪዎች ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ አጠናቅቆ መዝገቡን ለጠቅላይ ዓቃቤ ህግ መስጠቱን ገልጿል።ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም መዝገቡን መቀበሉን ለፍርድ ቤት አረጋግጦ በጣም ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ በህጉ መሠረት የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠን ሲል ጠይቆ ተፈቅዶለታል።

 ተጠርጣሪዎቹም አብዲሳ ቀነዒ፣ ደሳለኝ ተስፋዬ፣ ጌቱ ግርማ፣ ህይወት ገዳና ባህሩ ቶላ መሆናቸው ተጠቅሷል።እንደ ፖሊስ የምርመራ መዝገብ ከሆነ አንደኛ ተጠርጣሪ አብዲሳ ቀነዒ በዕለቱ በወንጀሉ ተጠርጥረው የህክምና ዕርዳታ እየተሰጣቸው የነበሩትን ሰዎች ለማስመለጥ ሙከራ ያረገ እንዲሁም ሶስተኛው ተጠርጣሪ ጌቱ ግርማ ደግሞ የቦንብ ጥቃቱን በማስተባበር ወንጀል ተጠርጥሯል ሲል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

 ተጠርጣሪዎች ጨለማ ቤት ውሰጥ ተቆልፎብናል፣ ህገመንግስታዊ መብታችንም ተጥሷል በሚል ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸው ተገልጿል።

 መርማሪ ቡድኑ  በበኩሉ የአያያዝ ችግር እንደሌለና ይህንንም በቪዲዮ አስደግፎ ለፍርድቤቱ ማቅረብ እንደሚችል ገልጿል።ፍርድ ቤቱ ከፈለገም ገለልተኛ አጣሪ ቡድን በመመደብ ሊያጣራ እንደሚችልም አስታውቋል።

ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ከአያያዝ ጋር በደል እንዳይደርስባቸው፣ ክትትል እንዲደረግላቸውና በቀጣዩ የቀጠሮ ቀን ነሐሴ 12/2010ዓ.ም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተጠርጣሪዎች ማረፊያ የስራ ኃላፊ ቀርበው ስለ አያያዛቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ ማዘዙም ታውቋል።

LEAVE A REPLY