የአሜሪካው ጉብኝት እና የመጋረጃው ጀርባ ትዕይንት!

የአሜሪካው ጉብኝት እና የመጋረጃው ጀርባ ትዕይንት!

ባለፈው ጽሁፋችን… ዝግጅቱ መጠነኛ የክፍያ ዋጋ እንዲኖረው፤ ይህንንም በTicket Master አማካኝነት መስራት እንደሚቻል ጠቁመን ነበር። ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረና ከዶ/ር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉዞ መልስ፤ ወሬያችን ስለመደመራችን ሳይሆን፤ በጉብኝቱ ወቅት ስለነበረው ምስቅልቅል እና ትርምስ ሆነ። ነገሩን ከውጭ ሆኖ በቲቪ በተመለከትንበት አይን መመዘን የለብንም፤ ወደውስጥ ስንገባ ትርምሱ ያናድዳል፤ እራስ ያማል። በዚያን እለት በስፍራው ሲጉላላ ለነበረው ህዝብ የሚናገርለትና የሚተነፍስለት ወገን ያስፈልገዋልና እነሆ ከዋሺንግተኑ ትርምስ ጀርባ የነበረውን ምስቅልቅል በጨረፍታ እናስታውሳችኋለን። ከዚያም ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ጀርባ እነማን እንደነበሩና ምን አይነት ስህተት እንደተሰራ አብረን እንመለከታለን። የምልከታችንም ዋና አላማ ከስህተታችን ተምረን ተመሳሳይ ስህተት እንዳንሰራ ለማድረግ እንጂ፤ የግለሰቦችን ሚና ለማንገስ ወይም ለማኮሰስ እንዳልሆነ ከወዲሁ ይሰመርበትና ወጋችንን እንቀጥላለን። እስከመጨረሻው ድረስ አብራችሁን ቆዩ… መልካም ንባብ።

የአሜሪካው ጉብኝት እና የመጋረጃው ጀርባ ትዕይንት!

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

በስልክ ስናደርግ የነበረው የመጨረሻ ንግግር የሚከተለው ነበር።

“እንዲያውም እያንዳንዱ ህዝብ የሚከፍለው ገንዘብ ከአዳራሹ ወጪ አልፎ ኢትዮጵያ ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን፤ ለመርዳት ቢውል” አልኩና፤ በቀላል የሂሳብ ስሌት ወጪና ገቢውን አብራራሁለት።

ክርክር እና ንግግር የታከተው በሚመስል መልክ፤ “ነገሩ አልገባህም!” ሲል ጀመረልኝ።

“ነገሩ አልገባህም! አየህ ይሄ ወጪ በስፖንሰሮች የሚሸፈን ነው!” አለና “እገሌ የተባለው ካምፓኒ ሰባ ሺህ… እገሌ ይሄን ያህል፣ እንትና ይህን ያህል ሺህ…” አለና አጠቃላዩ መቶ ምናምን ሺህ ዶላር ወጪ ከሞላ ጎደል በስፖንሰሮች እንደሚሸፈን ገለጸልኝ። እኔና እሱ በዚያው ተለያየን።

ብዙም ሳንቆይ ግን የኮንቬንሽን ሴንተሩን ሰነድ ስንከታተል፤ መቶ ሺ የተባለው ቁጥር፤ በቁጥ ቁጥ እየጨመረ… ከ3 መቶ ሺህ ዶላር በላይ ሆኖ አረፈው። ለዚህ ብለን ነው እንግዲህ… “ህዝቡ ከፍሎ ቢገባ…!” ብለን የተሟገትነው። አሁን የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሞራል ኪሳራም ሊመጣ ይችላል። በአጠቃላይ አለመደማመጣችን ይህን ዋጋ አስከፍሎናል።

ይሄ በዚህ እንተወውና… ፈረንጆች ጥፋተኛውን መያዝ ሲፈልጉ Follow the money የሚል ብሂል አላቸው። እኛም ገንዘቡን ስንከተል… ስንከተል… ስንከተል… ከዋናው አዘጋጅ ኮሚቴ በስተጀርባ ሌላ አዘጋጅ ኮሚቴ መኖሩን አወቅን። ከኮንቬንሽን ሴንተሩ እና  ከከተማው ባለስልጣናት ጋር ቀጥታ ግንኙነት የሚያደርገው፤ ሌላኛው እና የማይታየው አዘጋጅ ኮሚቴ በነሄኖክ የሚመራው ቡድን ሆነና አረፈው። ለነገሩ ሄኖክ በዋሺንግተን ዲሲ የፓርኪንግ ንጉሥ የሚል ተቀጽላ ያገኘው ነው። በዚያው መጠን ደግሞ፤ ድሮ ድሮ የነመለስ ዜናዊ ሰዎች ሲመጡ ጠብ እርግፍ ብሎ ያስተናግዳቸው ነበር። በህወሃት ዘመነ መንግስት… ከአዲስ አበባ አበልጁ ከሰንሻይን ባለቤት፤ አቶ ሳሙኤል ጋር መቀሌ ድረስ ሄዶ የተደብረጸየ ሰው ነው።

አሁን ያ ዘመን ካለፈ በኋላ… የዚያ ስርአት አገልጋዮች መልሰው ሲሰለጥኑብን ትንሽ ከበድ ይላል። ምንም ይሁን ምን ግን… ሰው መመዘን ያለበት፤ በባለፈው ማንነቱ ሳይሆን፤ አሁን እየሰራ ባለው ስራ በመሆኑ፤ የድሮውን ማንነት ወደጎን በመተው እንደEvent Organizerነቱ ለዋሺንግተን ዲሲ ያስገኘውን ትርፍና ኪሳራ በመመርመር ነጻ ልናወጣው ወይም ልንፈርድበት ግድ ይለናል። እናም ምርመራውን አሃዱ ብለን ስምጀምር… ‘በመቶ ሺህ ዶላር ያልቃል’ የተባለለት ፕሮጀክት 300 ሺህ ዶላር መድረሱን ስንመለከት… ጥያቄና የጥያቄ ምልክቶች ይበዙብናል።

አሁንም ድረስ የሚያናድደው ግን… ህዝቡ 5 እና 10 ዶላር እየከፈለ በመግባት፤ የባከነውን ገንዘብ መተካት እየተቻለ፤ በኢትዮጵያ ገንዘብ ወደ 10 ሚሊዮን ብር ተበትኖ ቀርቷል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት ሊጠየቅ የሚገባው የአዲስ አበባው ኮሚቴ ጭምር ነው። እናም በዚህ እለት ለአዳራሹ ገንዘብ መክፈል እየቻለ… “እኔ ልክፈልልህ” ተብሎ የአዳራሽ ወጪ የተከፈለለት ህዝብ… ክብሩን በሚፈታተን መልኩ ለሰባት ሰአታት ከአዳራሹ ውጪ መቆሙ በምንም መመዘኛ ትክክል አልነበረም።

ጁላይ 28፣ 2018፤ ቅዳሜ እለት – ጠዋት ላይ ነው። ዋሺንግተን ዲሲ ከተማ፣ L street – ኮንቬንሽን ሴንተር አካባቢ!

ከዋሺንግተን ዲሲ ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያው ከሚገኙ ከተሞችና ሌሎች የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች፤ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ኢትዮጵያውያን ከተማዋን አጨናንቀዋታል። የምሽት “አስረሽ ምቺው” አብቅቶ የማለዳ ጸሃይ ወጥታለች። የዋሺንግተን ዲሲ ‘ዳውን ታውን’ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያዊ ቀለማት አሸብርቀዋል። የሁሉም ልብ ዶ/ር አብይ ላይ ነው… ሁሉም ቅዳሜ ማለዳ ላይ ተነስቶ፤ በመኪና ወይም በባቡር ተሳፍሮ፤ ሃሳብ ቆርጦና መንገድ አቆራርጦ ወደ ኮንቬንሽን ማዕከል ተሟል። ሰልፍ እና ከሱ ጋር ተያይዝ ያለው ጭቅጭቅ… የህዝቡ ብዛትና ትርምሱ እራስ ያማል። አንዳንዶች ከለሊቱ 4፡00 AM ጀምረው ሰልፍ ይዘዋል። ሌሎች ደግሞ ከ5፡00 ጀምረው ሰልፍ ይዘው የሚገቡበትን ሰአት በጉጉት ይጠባበቃሉ።

ሰልፈኛው አካባቢውን በሰንደቅ አላማ እና በአላባ አሸብርቆታል። ወንዱም ሴቱም የዶ/ር አብይ ምስል ያለበትን ከናቴራ አድርጎ፤ ክብሩን ለዛሬው ዋጥ አድርጎ… ስለዶ/ር አብይ አህመድ ፍቅር ሲል በዚያ ሃይለኛ ጸሃይ፤ በዋሺንግተን ዲሲ ጎዳናዎች ላይ ሰልፍ ይዞ ቆሟል። አንዳንዱ እዛው በቆመበት ማንቀላፋት ጀምሯል፤ አንዳንዱ ደግሞ ቀልድ ቢጤ ለማውራት ይሞክራል።

“ይሄ ሰልፍ ጨርቆስ ያለውን የዶ/ር ቢቸግርን የልምድ አዋላጅ ክሊኒክ አስታወኝ…”

“እንዴት?” ሌላው ይጠይቃል።

“የልምድ ማዋለጃው እንደተከፈተ ሰሞን ወረፋ በዝቶ ነበር። እርጉዝ ሴቶች እየሄዱ ይሰለፋሉ። ከዚያም የመግቢያ ከፍለው ይገቡና፤ ለቀነ ቀጠሮው ወረቀትም ከፍለው ይወጣሉ። ‘ቀጠሮ የሚሰጣቸው ግን ለመቼ ነው?’ ለሚቀጥለው አመት!! በመሃል ልጁ ይወለዳል እኮ!” ይልና በራሱ ቀልድ ከት ከት ከት ብሎ  ይስቃል። “ጨርቆስን ልጁ እኮ ተወልዶ፤ አዋላጇ ራሷ ለክርስትና ትጠራለች።” ተሰላፊው በሰልፉ ምክንያት ከመበሳጨቱ የተነሳ ሊስቅም ሊሳቀቅም አልቻለም። ቀልድና እና ምሬቱ ግን ተቀላቅሎ ቀጥሏል።

አንዳንዱ ደግሞ ቁጣውን በግጥም መልክ አቅርብ የተባለ ይመስል“ስማ እንጂ እዛ ጋር! ወይ ተደመር ወይ ተመርመር!” ብሎ ይቆጣል።

በመሃል የሰልፉ ብዛት እና የጸሃዩ እየጠነከረ መሄድ ምርር ያስደረጋት አንዲት ልጅ፤ “ኧረ ይቅር። ለቴዲ አፍሮ ኮንሰርትም እንዲህ አልተሰለፍኩ።” ብላ አቋርጣ ልትሄድ ስትል፤ አንድ ሴትዮ ቀበል አድርገው፤ “ቻይው ልጄ! እኔ በጃንሆይ ግዜ ዘይት ጠፍቶ ተልፌያለሁ፣ በደርግ ግዜ ዳቦ ለመግዛት ሰልፍ ይዣለሁ፤ እንደዚህ አይነት የሚያማርር ሰልፍ ግን አይቼ አላውቅም። ቢሆንም ግን አብይ ይሄን ሁሉ መንገድ አቋርጦ መጥቶ ሳይማረር እኛ መማረር አይገባንምና ቻይው።” ብለው እሷንም ሌላውንም ሰልፈኛ እያጽናኑና  እያዝናኑ አቆይተውታል።

የሚገርመው ነገር… ጠዋት በዚያ በኩል ለስራ የሄደ ሰው፤ ስራውን ጨርሶ በዚያው በኩል ሲመለስ፤ የተሰለፈ ህዝብ አይቶ…

“ምንስነው ይሄ ነገር?” ብሎ ይጠይቃል።

“ጠቅላይ ሚንስትራችንን ለመቀበል የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ…” መልሱን አልጨረሰም፤ የፈረንጁ ጥያቄ ቀጠለ።

“ታዲያ ይሄ ሁሉ ግርግር እና ትርምስ ምን ያስፈልጋል?” ሌላ ጥያቄ።

“ትርምስና ግርግር የተፈጠረው በልምድ ማነስ ነው። ብዙ ልምድ ያለን የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ እንጂ የድጋፍ ሰልፍ አድርገን አናውቅም።” ፈረንጁ እየገባው መጣና ጭንቅላቱን መነቅነቅ ጀመረ። “እናም የተቃውሞ ሰልፍ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ልምድ አለን። ጠዋት የጀመርነውን ሰልፍ አሁን ጨርሰን እቤታችን እንመለስ ነበር።” የሚል መልስ አገኘ።

“That make sense!” ብሎ መንገዱን ቀጠለ።

 የሆኖ ሆኖ የሰልፉ ብዛት… ለሊቱን አልፎ፣ ቀኑን አጋምሶ አምስት ሰአት፣ ስድስት ሰአት… ሰባት እና ስምንት ሰአታትን አስቆጠረ። ህዝቡ በዶ/ር አብይ ፍቅር እና በሚያናድደው ሰልፍ መሃል ሆኖ፤ እያጉረመረመና እየተበሳጨ፤ የዋሺንግተን ዲሲ አዘጋጆችን እየረገመ… ብዙ ቆየ። ብዙ መቆየቱ ደግሞ ከብርቱ የበጋ ጸሃይ እና መናደድ ጋር ስለሆነ፤ የህዝቡን መጉላላት “ብዙ” የሚለው ቃል ብቻውን አይገልጸውም። በዚያ ላይ ይሄን ሁሉ ተሰልፎ… “አዳራሹ ሞልቷል” ተብሎ ሊመለስ እንደሚችል እያወቀ የተሰለፈ ህዝብ አለ።

በሌላ አቅጣጫ ደግሞ እኛ አለን። ጋዜጠኞች ከ9፡00 AM በፊት በስፍራው ተገኝተናል። የህዝቡን ሰልፍ አልፈን ወደ ዋናው በር ስናመራ፤ ጋዜጠኞችም ካሜራና የሚዲያ ትጥቃቸውን ይዘው ሰልፍ ላይ ናቸው። የኢሳት፣ የኦ.ኤም.ኤን፣ የአባይ፣ የሁሉም ሚዲያ ሰዎች ላባቸውን እየጠረጉ በዋናው በር ላይ በሰልፍ ተኮልኩለዋል። የህዝቡን ሁኔታበ ፎቶ እና በቪዲዮ ለማንሳት በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች፤ እነሱ ራሳቸው በህዝቡ ፎቶ ሲነሱ ዋሉ። ታዋቂ የሚባሉ ጋዜጠኞቻችን በዚህ አይነት ተሰልፈው ሲጉላሉ ማየት ያሳዝናል። “ምንድነው ነገሩ?” ስንል፤ ግማሹ “Secret Service Police እስኪመጣ ነው” ተባልን። በኋላ ላይ እንደተረዳነው ግን ለካስ ይሄ ሁሉ መጉላላት ዋተር ጌት ተኝተው እንቅልፋቸውን ያልጨረሱ የመንግስት ጋዜጠኞች ሳይገቡ ሌላው እንዳይገባ ነው – ታግተን የቆየነው። ሁኔታው እያናደደ የሚያስቅ ስለሆነ ከሁለት ሰአታት በላይ ነገሩን በትዕግስት ከመጠባበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረም።  ደግሞም ከዚህም የባሰ ሰልፍ በወዲያ በኩል አለና… እሱን በማሰብ ጭምር፤ በዝምታ ዝም ብለን ተሰለፍን።

“ለዚህ ሁሉ ትርምስ ምክንያት የሆነው አዘጋጅ ኮሚቴው ነው” በሚል ብዙዎቹ ኮሚቴውን በሃሜት ይቦጭቁታል። ከዚህ ሁሉ ትርምስ ጀርባ ግን አምባሳደሩም ሆነ ኮሚቴው የጎላ ሚና እንዳልነበራቸው የተረዳነው ቆይተን ነው። ከዚህ ሁሉ ጀርባ… ነገሩን የበላይ ሆኖ የሚያሽከረክረው Event organizer ሆኖ እንዲሰራ የተመደበው የሄኖክ ተስፋዬ ቡድን ነው። የዋሺንግተን ዲሲ የፓርኪንክ ንጉስ ተብሎ የሚንቆላጰሰው ሄኖክ፤ የመቶ ሺህ ብር ኮንትራት ከኢምባሲው ጋር ከጨረሰ በኋላ ስራውን በሚገባ መስራት አለመስራቱ፤ ገንዘቡ በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉ ሊገመገም ይገባል።

ለምሳሌ የአዳራሹ ዝግጅት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ተጠናቋል። በንጋታው ከህዝቡ የሚጠበቀው ተሰልፎ እየተፈተሸ መግባት ብቻ ነበር። ህዝቡ ውጪ ቆሞ ጸሃይ እየቆላው፤ ቀኑ ከተጋመሰ በኋላ አዳራሹ በሴክሬት ሰርቪስ ፖሊስ መፈተሽ አለበት ተብሎ፤ ማለዳ ላይ ሊሰራ የሚገባው ስራ ረፋዱ ላይ ተጀምሮ፤ ህዝቡ ከሰባት ሰአታት በላይ ውጪ እንዲንገላታ ምክንያት ሆነ። ሌላው ቀርቶ 40 ሺህ የሚይዘው አዳራሽ በብረት ተከልሎ ለ25 ሺህ ሰው ብቻ እንዲሆን ሲደረግ Event ኦርጋናይዘሩ ሄኖክ ተስፋዬ፤ ሲሆን ፖሊስን ማሳመንና 40 ሺህ ህዝብ እንዲስተናገድ ማድረግ፤ ይህ ካልሆነም ደግሞ አንድ ቀን ቀደም ብሎም ቢሆን በመገናኛ ብዙሃን ይህንኑ ጉዳይ ለህዝቡ ማሳወቅ ያስፈልግ ነበር።

ሄኖክ እና ቤተሰቡ ከአየር ማረፊያው ጀምሮ አቀባበል አድርገዋል። እናትየው እቴቴ (ትዋልተንጉስ) ምርጥ የተባለ ምግቧን ለንጉሳችን አቅርባለች። አባትየው በምሽቱ የራት ግብዣ ላይ ተገኝተዋል። ያዲሳባው አበልጅ ከዝግጅቱ ጀርባ ሆኖ ከነ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር ጎንበስ ቀና ሲል ነበር። ‘ይሄ ሁሉ ለምን ሆነ?’ ብለን ሙግት መግጠም አንፈልግም፤ ቢሆንም አይቆጭምና። ፈረንጆች የልባቸውን ነገር በትህትና መግለጽ ሲፈልጉ፤ “Don’t get me wrong…” ብለው ይጀምራሉ። እናም ሄኖክ ማለት ገና በ16 አመቱ አሜሪካ መጥቶ፤ እራሱን አስተምሮ፤ ቤተሰቡንና ወገኑን በመርዳት፤ የሰራቸው መልካም ነገሮች አሉት። ወዳጃችን ሄኖክ ከዱከም ጀርባ ከያዛት ትንሽዬ ፓርኪንግ ስራ ተነስቶ፤ ቦታውን ገዝቶ፣ አሮጌ መኪኖች እየሸጠ ስኬታማ የሆነ ሰው ነው። ለዋሺንግተን ዲሲ ከንቲባ ያለውን ፍቅር ለማሳየት፤ ትላልቅ የሚባሉ የልደት በአል ግብዣዎችን እያደረገ፤ በስጦታ መያዝ ያለበትን እየያዘ… በድካሙም በገንዘቡም U street፣ ናሽናል እና Dulles Airport የሚገኙ መኪና ማቆሚያዎችን ጨረታ እያሸነፈ፤ እጅ መንሻን መሰረት ባደረገ ህጋዊ አሰራር ሃብታም የሆነ ኢትዮጵያዊ ነው። እናም “Don’t get me wrong…”! ጨረታ ማሸነፍ ደግሞ ከድሮም ይሆነዋል… በዘመነ ህወሃት በአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ ጨረታውን አሸንፈው ወስደዋል።

እንግዲህ የውጪውን ሰልፍ ታልፎ እንደምንም ወደ ውስጥ ሲገባ ሌላ የሚያናድድ ነገር ያጋጥማል። ህዝቡ እንደባህር አሸዋ በአንድ ወገን ተገድቦ ቆሟል። በህዝቡ እና በመድረኩ መካከል ከስምንት መቶ ጫማ ርቀት በላይ ርቀት አለ። ያንን ሁሉ ሰልፍ አልፎ የገባው ህዝብ በብረት እና በሴኩሪቲ ታጥሮ፤ የመድረኩን ዝግጅት በስክሪን ከማየት ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳይኖረው ተደርጓል። በዚያ ላይ የVIP መቀመጫ በብዛት እያለ፤ አዳራሹም ገና ሳይሞላ፤ የውጭው በር ተዘጋ። ምንም ሰው እንዳይገባ ተደረገ፤ ብዙ ሰዎችም ቀኝ ኋላ ዞረው ዝግጅቱን ከቤታቸው ወይም ከስልካቸው ስክሪን ላይ ማየት ጀመሩ።

የመድረክ አስተዋዋቂዎቹ ኑኑ ሊበን ዋቆ እና ዳንኤል ክብረት ናቸው። ኑኑ ዋቆ እራሷን በራሷ Spokes person አድርጋ ነው የሾመችው። የዛሬ ሁለት አመት ገደማ… ለንደን ላይ በተደረገው የኦሮሞ ኮንፈረንስ፤ አባቷ “ለኦሮሞ የማትሆን ኢትዮጵያ ትበታተን” በማለቱ ከፍተኛ ተቃውሞ የደረሰበት ሰው ነው። ልጅቱ ኑኑ EBS TV ላይ ኑኑ ሾው የሚል ዝግጅት ነበራት። ከኦሮምኛና እንግሊዘኛ በቀር አማርኛ ለማውራት ባለመፈለጓ ቀይ ካርድ ያገኘች ናት። መድረኩ ላይ ከዲያቆን ዳንኤል ጋር በመሆን በ’ንግሊዘኛ ዝግጅቱን እያስተዋወቀች ናት። ዲያቆን ዳንኤል ደግሞ ተናዶ የገባውን ህዝብ የባሰ ለማናደድ በሚመስል መልኩ… “ቁጭ በሉ!” የሚል ትዕዛዝ ቢጤ መልዕክት ያስተላልፋል፤ እሷም ወደ ፈረንጅ አፍ ትተረጉምለታለች።

ይሄ ስብሰባ የተደረገው ሳንዲያጎ ዌይም ዴንቨር ላይ ወይም ሌላ ከተማ ቢሆን ኖሮ፤ ህዝቡ በተባለው መሰርት ቁጭ ቁጭ ብሎ ለማዳመጥ ይዘጋጅ ነበር። እግዜር ያሳያቹ…ዋሺንግተን ዲሲ ላይ፤ ተናዶ የገባን ህዝብ፤ የታማኝ በየነ መድረክ እና ማይክ የተነጠቀን ህዝብ… “ቁጭ በል” ሲባል ሊፈጥር የሚችለው ንዴት አስባችሁታል? አማርኛ መናገር የሚጎፈንናት ኑኑ ዋቆ ጭምር፤ በቦሌ ልጆች ቅላጼ… ከአንዴም ሁለት ግዜ፤ “ኧረ በናታቹህ ቁጭ ቁጭ በሉ!” ስትል የሳቀም የተናደደም ብዙ ሰው ነበር። ህዝቡ በተደጋጋሚ “ታማኝ ታማኝ!” እያለ ይጮሃል። የመድረክ አዘጋጆቹ “ታማኝ! ታማኝ!” የሚለውን የህዝብ ድምጽ እንደዋዛ ሊያልፉት ሞክረው ነበር። ለማናደድ የተቀጠሩት የመድረክ ሰዎች ጭራሹን በዚህ ቁጣ መሃል አምባሳደር ካሳን ወደ መድረኩ እንዲወጣ አስደርገው፤ የባሰ አስጮኹበት። በመጨረሻ ዶ/ር አብይ አህመድ ታማኝ በየነን ወደ መድረክ ጠርቶ የግንቡን ማፍረሻ ገሶ ሲያቀብለው ደስ ያለንን ያህል፤ ለራሱ አምባሳደር አለመቆሙ “ለምን?” እንድል ብቻ ሳይሆን፤ ፖለቲካ አስቀያሚ ጨዋታ መሆኑን አስታውሶናል።

ሁሉም በየህሊናው የሚሰጠውን ፍርድ ለየራሱ በመተው ከዝግጅቱ ጥቂት ቀናት በፊት የሆነውን እናውጋቹህ። እንደድፎ ዳቦ ከላይም ከታችም እሳት ሲነድበት የነበረው አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን የኢምባሲ ሹፌርም ሆነ አጃቢ ሳይዝ፤ ታማኝ በየነን በአካል ለማነጋገር እቤቱ ድረስ ይሄዳል፤ ሄዶም ከታማኝ ጋር ተነጋግሮ ሰላም ያወርዳል። ነገር ግን ከዚያ መልስ… ባልታወቀ ምክንያት፤ ታማኝ በየነ ወደ መድረክ እንዳይወጣ ተደረገ። ከጀርባ ሆነው ትዕዛዝ የሰጡትን ሰዎች ባናውቅም ሁኔታው አንድ ነገር አስታወሰን። የዛሬ 12 አመት በቨርጂንያ ኮመንዌልዝ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ለምረቃቸው ፓርቲ ለማዘጋጀት ስብሰባ ተቀምጠዋል። የመድረክ ዝግጅታቸው እንዲደምቅ “ታማኝ በየነ” የክብር እንግዳቸው ሆኖ እንዲመጣ ሃሳብ አቅርበውለት እሺ ካላቸው በኋላ፤ ጉዳዩን ወደ ተማሪዎቹ አመራሮች አምጥተው  ሊያስወስኑ ሲሉ፤ አንደኛው የተማሪዎች አመራር – ቢንያም ተስፋዬ “በጭራሽ አይሆንም!” ሲል ተከራከረ። ታማኝም ለተማሪዎቹ ምርቃት ሳይሄድ ቀረ። ያ ታማኝ በየነ እንዳይገኝ የተቃወመው ተማሪ ቢንያም ተስፋዬ – የሄኖክ ተስፋዬ ትንሽ ወንድምና አሁን Event Organizer ተብለው ተፍ ተፍ ሲሉ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንደኛው ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ አምባሳደሩ ታማኝ በየነ ቤት ድረስ ሄዶ ከተስማማ በኋላ፤ ተመልሶ መጥቶ ውሳኔውን እንዲሰርዝ ያስደረጉት እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉ፤ ከመላ-ምት ያለፈ መረጃ ስለማይኖረን፤ ወጋችንን በዚህ ቁም ነገር እንቋጭ።

እንግዲህ እነ እገሌ እና እነ እገሌ ትዝብት ወረሱ እንጂ ታማኝ በየነ በህዝብ ጩኸት ወደ መድረኩ ወጥቷል። ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ቢሆን በስደት ላይ ያለውን ሲኖዶስ እና ፓትርያርክ እንዲያ አውርዶና አዋርዶ ሲያሳቅላቸው ይቆይ እንጂ፤ የሃይማኖት አባቶቻችን አገር ቤት ገብተዋል። ኑኑ ሊበን ዋቆ “አማርኛ መናገር አልፈልግም” ትበል እንጂ፤ ሳትወድ በግድ ገብታበታለች። እንኳንስ እሷ… ኦቦ ሊበን ዋቆም አገር ቤት ገብተው  ተደምረዋል። እነኃይሌ ገብረስላሴ፣ ሳሙኤል ሰንሻይን፣ ሄኖክ ተስፋዬ እና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች በጠቅላይ ሚንስትሩ ዙሪያ ተደጋግመው እየታዩ ነው። እነዚህ ሰዎች ኢህአዴግ ውስጥ ከተደመሩ ቆይተዋል። እኛ የምንፈልገው ግን ወደ ህዝቡ የሚደመርን በመሆኑ፤ ህዝባዊነታቸውን በመደመር ብቻ ሳይሆን በመቀየር ጭምር ማረጋገጥ አለባቸው። ያለበለዚያ ነገሩ ሁሉ በአሮጌ አቁማዳ፤ አዲስ ወይን ጠጅ መያዝ ወይም ውሃ መውቀጥ ነው የሚሆን። ቢሆንም ግን (መደምደሚያችንን በእርቅ ለመጨረስ ያህል) ሰዎቹን ይቅር እንላቸው ዘንድ… እነዳንኤል ክብረት ህዝቡን ይቅርታ ይበሉልን፤ ባለሃብቶቹ እነሄኖክ ደግሞ ከወጪ ቀሪ የደረሰብንን ኪሳራ ይክፈሉልን። ከዚያ ፋይላችንን እንዘጋለን።

ነገሩን ስናጠቃልለው… የአባቶቻችን እና የናቶቻችን ጸሎት ኢትዮጵያና ልጆቿን እየጠበቃት እዚህ ደርሰናል። ከዚህ በላይ ባለብዙ ራዕይ የሆንን ኢትዮጵያውያን ራሳችንን በነጻነት ያቆየነውን ያህል፤ ለሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ነጻነት የቆምነውን ያህል፤ ዛሬም ከኢትዮጵያ አልፈን ለአፍሪቃ የምንተርፍ ዜጎች እንድንሆን፤ የጥላቻንና የሌብነትን ግንብ ለማፍረስ ያብቃን። አሜን!

LEAVE A REPLY