/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 21 አባላት ያሉት የፕራይቬታይዜሽን ምክር ቤት ማቋቋማቸው ተገለጸ። ጠ/ሚኒስትሩ ባቋቋሙት ም/ቤት ውስጥም የሚዲያና በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ ታዋቂ ፖለቲከኞች ያካተተ መሆኑም ታውቋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ፣ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ዘላለም መለሰ፣ ዶ/ር አለማየኹ ስዩም፣ አቶ በቀለ ገለታ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ አበበ አዕምሮ ስላሴ፣ ወ/ሮ ሳራ አበራ፣ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፣ ዶ/ር ጸጋዬ በርሔ፣ አቶ ተገኘወርቅ ጌቱ፣ ዶ/ር አይናለም መገርሳ፣ አቶ ካሳ ከበደ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አቶ ሌንጮ ባቲ፣ ዶ/ር አብርሐም ተከስተ፣ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ አቶ ተክለወልድ አጥናፉና አምባሳደር ግርማ ብሩ የም/ቤቱ አባላት ሆነው መመረጣቸውን የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ሃላፊ ፍፁም አረጋ በትውተር ገፃቸው አስታውቀዋል።
አቶ ፍጹም አረጋ እንደገለጹት ምክር ቤቱ ግዙፍ የመንግሰት ድርጅቶች በከፊል ወደግል የሚዘዋወሩበት ሂደት ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነት ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣መብራት ሀይልና ኢትዮ_ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ከሚዞሩት ግዙፍ የመንግስት ደርጅቶች ግንባር ቀደሞቹ መሆናቸውን ከወራት በፊት ጠ/ሚኒስትር አብይ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።