/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ(አብዲ ኢሌ) ባይረጋገጥም በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሉ እየተገለጸ ነው። በክልሉ ጅጅጋን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች አለመረጋጋት መስፈኑም ታውቋል።
ቤተክርስቲያናት፣ ባንኮች፣ የንግድ ድርጅቶች፣የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ሀይሎች(የክልሉ) እየተቃጠሉና እየተዘረፉ መሆኑ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።ጎሳን(ብሔር) መሰረት ያደረገ ጥቃትም እየተፈጸመ ነው ተብሏል።
ከጅጅጋ ከተማ በተጨማሪ ወርደር፣ ጎዴ፣ ደጋሃቡር፣ ቀብሪደሃርና በሌሎች በርካታ የክልሉ ከተሞች በልዩ ሀይል ፖሊስ በታገዝ መልኩ ባንኮችን እየዘረፉ ነው። ቤተክርስቲያናትም እየተቃጠሉ ነው።
በዚህም የበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋቱም እየተነገረ ነው። አሁንም በክልሉ የተረጋጋ ነገር የለም። አብዲ ኢሌም ከሰዓት በሗላ በክልሉ ቴሌቪዥን ቀርበው ህዝቡ እንዲረጋጋ እንዲሁም ዘረፋ እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።
የመከላከያ ሰራዊት አባለት የከተማውን ቁልፍ ቦታዎች ከመቆጣጠር ባሻገር በከተማው ውስጥ የተፈጠረውን ስርዓት አልበኝነት ለማስቆም ጥረት አለማድረጋቸው የጅጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
(በክልሉ እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ የመንግስትም ሆነ የመንግስት ሚዲያዎች ገብተው መዘገብ ባለመቻላቸው ግለሰቦች ከሚሰጡት መረጃ በስተቀር እርግጠኛ ሆኖ መናገር አልተቻለም።)