ረጂሙ መስታውት ፊት ቆሜ ዘናጭ ሱፌን ለበስኩ:: ክራቫት ማሰሩ ላይ ግን አልተሳካልኝም:: የክራቫቴ ራስ ባንድ ጎን ተድቦልቡሎ የቡዳ መዳኒት መስሏል::
…
ቁርሴን በልቼ በዳግማዊ ምኒልክ ሀውልት ስር የማስቀምጠውን አበባ ለመግዛት ወጣሁ:: ገና አፋልቱ ላይ ልደርስ ስል አንዱ ብቅ አለና:-
“በውቄ አድናቂህ ነኝ!”
“በጣም አመሰግናለሁ” አልሁኝ ፈገግታየን በርግጄ::
“የመጨረሻውን መፅሀፍህን ስንት ኮፒ አሳተምህ?”
“አስር ሺ”
“የማትፈልገው አስር ብር ይኖርሃል?”
ፈገግታየ ድራሹ ጠፋ::
” አትፍረድብኝ መሮኝ ነው!! አንገፍግፎኝ ነው” አለኝ ፈላጩ ራሱን እያከከ::
“ኑሮ ይህን ያህል ካንገፈገፈህ ለምን አንድ ሊትር ናፍጣ ገዝተህ ራስህን አታቃጥልም?”
” አንድ ሊትር ናፍጣ ስንት ነው?”
” አምሳ ብር?”
አምሳ ብር ካለኝ !! ለምን ራሴን አቃጥልለሁ? ”
“አንድ ዙርባ አልቅምም?”
አሳቀኝ ስለተመፅዋችነቱ ሳይሆን ስለኮሜድያንነቱ አስር ብር ሸለምኩት::
” አመሰግናለሁ!! ኢትዮጵያ ሲያልፍላት ውለታህን እከፍላለሁ!!” አለኝ ፈገግ ብሎ::
” ኢትዮጵያ ያልፍላታል ብለህ ታስባለህ?”
” ታድያስ መንግስት ደብቆት ነው እንጂ በምሥራቅ ኢትዮጵያ : ለቀጣይ ሁለት መቶ አመት የሚቆይ ጋዝ ተገኝቷል”
” ምን አይነት ጋዝ?”
” አስለቃሽ ጋዝ”
በድጋሜ ስላሳቀኝ ሃያ ብር ጨመርኩለት::
…አበባ መሸጫው እስክደርስ : አባቴ ስለ አድዋ የነገረኝን ያልተሰማ ታሪክ ላጫውታችሁ::
🏹🏹🏹🏹🏹🏹🏹
ባጤ ምኒልክ ዘመን ፈጠነ ሞገሴ የተባለ ዝነኛ ሽፍታ ማንኩሳ ውስጥ ይኖር ነበር:: ያድዋ ብሄራዊ ውትድርና አዋጅ ሲታወጅ ፈጠነ ሞገሴ ዱር ውስጥ ስለነበር ያዋጁ ቃል የደረሰው በጣም ዘግይቶ ነው:: ታድያ: ያዋጁን ቃል እንደሰማ ባጭር ይታጠቅና ወደ ጦርሜዳ ብቻውን ይገሰግሳል:: ፈጠነ ሞገሴ ቀንና ሌት ተጉዞ አሸንጌ ላይ ሲደርስ ያጤ ምኒልክ ሰራዊት ውጊያውን በድል አጠናቆ ሲመለስ አገኘው::ፈጠነ የንጉሱ ሰራዊት እየፎከረ እየሸለለ ተሰልፎ ሲያልፍ ሲያይ በቅናት ሊያብድ ደረሰ:: ወደ አገሩ ሲመለስ ለሚስቱ ምን ሊያወራት ነው? ምን ግዳይ ሊያቀርብላት ነው?! መጀመሪያ የመጣለት ሀሳብ ” ዘመቻው ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት ስላላሳተፈ ጦርነቱ እንዲደገም ግርማዊነትዎን እማፀናለሁ” የሚል ደብዳቤ ለምኒልክ መፃፍ ነበር:: ይህ እንደማያዋጣ ገባው::
ሌላ ዘዴ ለማውጠንጠን ከጎዳናው ተዘንጥሎ ባቅራብያው ወደሚገኘው ዱር ገባ:: ይህ በእንዲህ እያለ : ከሰራዊቱ ተገንጥሎ ወደ ሁዋላ የቀረ አንድ የመንዝ ዘማች የማረከውን የጥልያን በበቅሎ ላይ አስቀምጦ እየነዳ ሲመጣ ተመለከተው:: ይቺን ይወዳል ፈጠነ ሞገሴ!! ፈጠነ ሞገሴ ጠብ አማረው:: ግን የጠብ ምክንያት በቀላሉ ስላልመጣለት ተናደደ:: ወድያው ግን አንድ ሰበብ ብልጭ አለለት:: የመንዙን አርበኛ መንገድ ዘግቶ ” ጌታው!! ፈረንጁን ምርኮኛ በቅሎ ላይ አስቀምጠህ አንተ በእግርህ መሄድህ ምን አስበህ ነው? የጥቁር ዘር ከታች የነጭ ዘር ከላይ ነው ለማለት ፈልገህ ነውን? የድሉን ፍሬ ለማራከስ ፈልገህ ነውን?” ብሎ ነገር ፈለገው:: አንዳንድ ሲባባሉ ቆዩና መፋለም ጀመሩ:: ፈጠነ ሞገሴ ባረፈ ጉልበት ለተፋለመ ወደረኛው ሊቋቋመው አልቻለም:: በዚህ ፍልሚያ የመንዙ ወታደር ለመጀመርያ ጊዜ ሲማረክ : ጣልያኑ ለሁለተኛ ጊዜ ተማረከ”…