በአሁኑ ሠዓት ወሎ ላይ እየሆነ/እየተደረገ ስላለው ነገር የሚሰማኝን ሀዘንና ቁጭት በዝምታ ካልሆነ በስተቀር በምን ቋንቋ ልገልፀው እችላለሁ? ይኸ ሁሉ የሆነው “ኧረ እባካችሁ ተው …” እያልን እየተማፀንን ነው፡፡ ወሎ የፍቅር አገር ነው፡፡ ወሎ የመቻቻል ተምሳሌት ነው፡፡ ወሎ ሙስሊም – ክርስቲያኑ ልዩነቱ ጎልቶ ሳይታይ አብሮ የሚኖርበት የዱኣና የፀሎት አገር ነው፡፡ ወሎ የአማራው፣ የኦሮሞው፣ የአፋሩ፣ የአርጎባው፣ የአገው፣ የራያው፣ የትግሬው … ወዘተ መግቢያና መናኸሪያ ነው፡፡ ወሎ የህብረብሔራዊነትና የአብሮነት መገለጫ ነው፡፡ ይህን ደጋግመን ተናግረናል፡፡ ግን የሚሰማን አልተገኘም፡፡
አሁን ላይ በከሚሴ፣ አጣዬ፣ ኤፌሶን፣ ማጀቴ … ወዘተ (በአካባቢው ተደራጅቶ በሚንቀሳቀስ ሽብርተኛ ቡድን) በወገኖቻችን ላይ እየተፈፀመ ያለው አስፈሪ ድርጊት በእንጭጩ ሊገታ ይገባል፡፡ መንግሥት የድርጊቱን ፈፃሚዎች በቁጥጥር ሥር ማዋልና ለፍርድ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት የህዝቡን ሰላም የመጠበቅ፣ ህግና ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት የዘነጋው ይመስላል፡፡ ይህን ማድረግ ግዴታው ሲሆን፣ ካልቻለ ደግሞ ለህዝቡ ግልፅ ማድረግ አለበት፡፡ ህዝቡ ያለበትን ሁኔታ በግልፅና በትክክል ማወቅ አለበት፡፡
አሁን እየሆነ/እየተደረገ ያለው ነገር በተለይ የወሎን ህዝብ የሚያሳዝን መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የወሎ ህዝብ ያልበላውን የሚያክኩት ሌሎች ባለረጃጅም እጆች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ወሎ ላይ ጦርነትና እልቂትን የሚደግሱት ለወሎ ህዝብ አስበው፣ ወሎን ከችጋር፣ ከስደትና ከመንከራተት ለመታደግ አይደለም፡፡ ዝሆኖቹ በወሎና አካባቢው ላይ ሲፋለሙ ሣሩ እንደሚጎዳ አጥተውት አይደለም፡፡ ምናልባትም ዓላማቸው ወሎን በጦርነት በመደቆስና አቅመ-ቢስ በማድረግ አካባቢውን በቀላሉ ለመቆጣጠርና እንዳሻቸው ለመፏለል ሊሆን ይችላል፡፡ ግንኮ ወሎን ለወሎዬዎች ቢተውት ለሁሉም በሩ ክፍት ነው፡፡ ወሎ ለምን ይደቆሳል? እንዳውም የለማና የበለፀገ ወሎ የሁሉም አለኝታ ሊሆን እንደሚችል ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ይኸ ለሁሉም አካባቢዎች የሚሠራ ነው፡፡ እንደሀገር የሚያስፈልገን የተናጠልና በአጠቃላይ ልማትና ብልፅግና ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እርስ በርስ መተሳሰብና መናበብ ያስፈልጋል፡፡ ጠባብ ብሔርተኝነት ለዚህ ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ጠባብ ብሔርተኝነት በባህሪው ቀናተኛ ነው፡፡ እናም ተገቢ ላልሆነ ፉክክርና ግጭት መንስኤ ነው፡፡ አሁን በሀገራችን ለተፈጠረው የእርስ በርስ ፍጥጫ ዋነኛ መንስኤው የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ከፊታችን የምንዋጋው ነገር ቢኖር ጠባብ ብሔርተኝነት ነው፡፡ የምንዋጋው ግን መሣሪያ አንስተን አይደለም፡፡ የምንዋጋው አስተሳሰቡን በተሻለና ተራማጅ በሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ ጠባብ ብሔርተኝነትን የምንዋጋው ማንንም ለመጉዳት አይደለም፡፡ ይልቁንም በውጤቱ ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡
አንድ ነገር ግን ይሰመርበት!
ሌላው ሁሉ በብሔር ተደራጅቶ ሥጋት እየፈጠረ ባለበት ሁኔታ አንዱን ወገን ነጥሎ ለማውገዝ መሞከር በምንም ዓይነት መመዘኛ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌላው በብሔር ተደራጅቶ መብትህን ሲረግጥ፣ ጥቅምህን ሲጋፋ፣ ህልውናህን ሲገዳደር የሚኖርህ ብቸኛ አማራጭ አንተም እሱ በቀየሰው መንገድ ተደራጅተህ መከላከል ነው፡፡ በብሔር መደራጀት መወገዝና፣ እንዳስፈላጊነቱ በህግም መታገድ አለበት፡፡ አለበለዚያ ግን ሁሉም በሂደት ተስፋው እየተሟጠጠ በየብሔሩ ተደራጅቶ አሸናፊና ተሸናፊ ወደሌለበት የማያልቅ ጦርነት ውስጥ መገባቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በፌዴራልና በክልል ደረጃ በሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ከሁላችንም በላይ ታሪካዊ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ በተለይ በአሁኑ ሠዓት ሩዋንዳን በመጎብኘት ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ያላቸውን የመንግሥት ሥልጣንና (ተሸርሽሮ ያላለቀውን) የህዝብ ድጋፍ በመጠቀም በዘር ፖለቲካ ላይ የማያወላውል አቋም መያዝና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ አጋጣሚ በኦሮሚያ ልዩ ዞንና አካባቢው፣ በጦረኞችና ነፍሰ-በላ ቡድኖች ህይወታቸውን ስላጡ ወገኖቼ ሳስብ የሚሰማኝ ልባዊ ሀዘን ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ መግለፅ የምችልበት ቃላት የሉኝም፡፡
ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ!!!