“ነይ ሀገር እንሣል” || መላኩ አላምረው

“ነይ ሀገር እንሣል” || መላኩ አላምረው

ሀገር ልሥል ሳስብ፣ ሴት ትታየኛለች፤
ውበቷም ቁመቷም፣ አንችን የመሰለች።
.
ሀገር ልሥል ሳስብ…
ያደግሁበት ከፍታ፣ ግሽ ይመጣብኛል፤
ከግሽ ተራራ ስር፣ ግዮን ይታየኛል፤
የግዮን ምንጭ ጠበል፣ ሰይጣንን ያርቃል፤
ሰይጣን የራቀው ልብ፣ ከአምላክ ይታረቃል፤
አምላኩን ሚፈራ፣ ሕዝቡን ያከብራል፤
ሕዝቡን የሚወድ፣ ሀገሩን ያፈቅራል፤
ሥዕሏን በሕሊናው፣ አትሞ ያኖራል።
.
ነይ ሀገር እንሣል…
ካንች ጋራ ስሆን… ይታየኛል ባ’ይኔ፤
ተሰባብሮ ሲወድቅ፣ የመሰይጠን ወኔ፤
በመሰይጠን ፋንታ፣ መልአካዊ ፀባይ፤
ከልቤ ሲመነጭ፣ ከዓይኖችሽ ሲታይ፤
በድምጼ ሲወጣ፣ በአንደበትሽ ሲዜም፤
ገፍትሮ ሲጥለው… የጥላቻን አዚም፤
ይታየኛል በቃ….
ዘር ቆጣሪ በቀል፣ አርባ ክንድ ሲርቀን፤
መልአካዊ ፀባይ፣ በፍቅር “ሲያደቀን” !!!
ሰላም ፍቅር ሰፍኖ፣ ጥል በቀል ሲያበቃ፤
ሁሉን የሚረታው………….. ፍቅር ነዋ በቃ !!!
.
ከግሽ ስር ጠብቂኝ…
ከግሽ ተራራ ስር፣ ትልልቅ ዛፍ አለ፤
ሀገርን… ሀገርን… ሀገርን… ያከለ።
.
ከአንደኛው ዛፍ በላይ፣ ሰንደቅ ዓላማዋ፣ ከፍ ብላ ተሰቅላ፤
በቃል ኪዳን ታስራ፣ ሰማያዊ ምሥጢር፣ በቀለሞቿ አዝላ።
ከዓላማው ጫፍ ላይ፣ ነጭ እርግብ ተቀምጣ፤
ክንፎቿን ዘርግታ…
ስትጸልይ ‘ምትታይ፣ ሰላምና ፍቅርን ከላይ እንዲመጣ።
.
(ደስ አይልም ውዴ…
ባ’ገር ፍቅር ስሜት ይህንን መመልከቱ?
አሳዛኙ ነገር…
ሰንደቅ አፍቃሪዎች፣
ይኸው በእርሷ ሰበብ፣ ወህኒ ሰነበቱ 🙁
ይሁና ግድ የለም…
ምሥጢር ስላዘለ የሰንደቋ ቀለም፤
ለማንም አሳሪ፣ የሚረዳ አይደለም።
ሀገር መራሁ የሚል፣ ባ’ገር ዓርማ ሰበብ፣ ዜጎቹን ማሰሩ፤
ይዘገያል እንጅ… በታሪክ ሲገረፍ፣ አይቀርም ማፈሩ።)
.
.
እይ ከተራራው ታች…
ዛፎቹን ተመልከች…
ሀገር ይመስላሉ፤ ሀገር ያክላሉ፤
ብዙ ቅርንጫፎች፣ ከጎን ያበቅላሉ፤
በየቅርንጫፉ… ቅጠልና አበባ፣ ፍሬም ያወጣሉ፤
ፈጽሞ አይታዩም… አንደኛው ቅርንጫፍ ከሌላው ሲጣሉ።
.
ፈጣሪ ጠቢብ ነው…
ማስተዋል ላደለው፣ በተፈጥሮ ምሥጢር፣ ፍቅር ያስተምራል፤
የሰው ልጅ ብኩን ነው…
ይህን ሳያስተውል፣ ሲብከነከን ውሎ፣ እንደቃዠ ያድራል።
ያንች’ና’ኔ ልብ ግን…
ከሰፊ መዝናኛ፣ ፍቅር እያወጋ፣ ጥበብ ይቀምራል፤
ከዛፍ ከቅጠሉ…
ከአበባ ከፍሬው፣ በሰንደቁ ቀለም፣ ሀገርን ይሥላል።
.
(((ሀገር የሚሥል ሰው፣ ቀለም አይቀይጥም፣
ምን ቀለም ቢቀየጥ፣ ከሰንቅ አይበልጥም።)))
.
እንዲያውም እንዲያውም…
ልብ ሀገርን ሲሥል፣ የወገኑ እምባ ነው፣ የብሩሽ ቀለሙ፤
የከፋው ሕዝብ እምባ…
ሦስት ቀለም ይሠራል… አረንጓዴ – ቢጫ – ቀይ ነው በስሙ።
እንባው ሽቅብ ሲተን…
የቀለማቱ ዓይነት፣ በእግዜር እጅ ተስለው፣ ሰማይ ያስውባሉ፤
ይህን የሚያዩ ዓይኖች… በራሳቸው እምባ ፍቅር ይከንፋሉ፤
የሰማዩን ምሥል፣ በሽመና ሰፍተው፣ ዓርማ ይሠራሉ፤
የሰፉትን ዓርማ፣ በክብር ይሰቅላሉ፣ በፍቅር ይለብሳሉ፤
.
ሀገር የሚሳለው፣ በሰማይ ጠፈር ነው፣ ምድር ላይ አይደለም፤
ከበላይ ያልሆነ፣ እንኳንና ሀገር፣ ምድር ብሎ የለም።
.
አንዳንዶች….
ሀገርን ሲሥሉ….. እጅግ ያስቃሉ…
በቋንቋ በቀለም…. እየከላለሉ…
የሕዝብን ማጎሪያ፣ ካርታ ነው ይሉናል፤
ወረቀት ላይ ከፍለው፣ ባ’ካል ያባሉናል።
.
ሰው በነፃ ነፍሱ፣ እግሩ ወደመራው፣ ይኑር እንጅ ሄዶ፤
ምን ይሉታል ክልል?
ምን ይሉታል ካርታ? ሰውን ባጥር ማኖር፣ ማሰር አስገድዶ?
.
ተያቸው ዓለሜ…
ሀገር መሣል ውሉ፣ ያልገባቸው ሁሉ፤
ብዙ ተሳስተው፣ ብዙ ያስወራሉ፤
በንዴት ሚያወራን፣ አሳደው ያስራሉ፤
ሰው ባሰሩ ቁጥር፣ ሀገር ይገድላሉ።
.
.
ነይ ሀገር እንሣል…
ከፍታው ጠፈርን፣ በሚነካ አድባር፣ ከፍ ብሎ ከሰማይ፤
የግዮንን ጠበል፣ አምጦ በሚወልድ፣ በግሽ ተራራ ላይ፤
ሀገር ከመሰሉ፣ ከትልልቅ ዛፎች፣ አንዱን ተከልለን፤
የሀገርን ዓርማ፣ ጠፈር ላይ አትመን፣ በልብ ላይ ተክለን፤
ከገነት ሚሰማን፣ የግዮን ወፍ ዜማ፣ በፍቅር ዘምረን፤
ፍቅር የሚያጠፋን፣ አበጣባጭ ጋኔን፣ በጠበሉ አባረን።
.
ነይ ሀገር እንሣል !!!

LEAVE A REPLY