ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ||| በሙክታር ኡስማን

ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ||| በሙክታር ኡስማን

ውድ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንኳን ለሀገርዎ አበቃዎ። በተፈጠረውና በወደቀብን መዓት ምን እንደሚሉን በጉጉት ስጠብቅ ነበር። ማምሻውን መግለጫዎትን አነበብኩ። የዘውትር ማፅናኛ ቃል ከመሆን ያለፈ ሀባ ጠብ የሚል ነገር አጣሁበትና ይህን ደብዳቤ ልፅፍሎት ተነሳሳሁ።

“አረሙን እየነቀልን፣ ስንዴውን እንንከባከባለን” ከእርስዎ መግለጫ ያተኮርኩባት አገላለፅ ነች። እንዲህ አይነት ባዶ ማፅናኛ ቃላት ናቸው እኛን እያደነዘዙ ወደ ቄራ የሚወስዱን ስልዎት ለቃልዎት ክብር መንፈጌ ሳይሆን ውስጣችን ያለውን ምሬት የሚያሽል ህመማችንን የሚመጥን ባለመሆኑ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆይ፣

እርሶ በሩሲያ እያሉ ከ67 በላይ ሰው ሞቶአል፣ የቆሰሉት ቤቱ ይቁጠረው፣ ቤተእምነቶች ወድመዋል፣ ቀሳውስት ተገድለዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ በተለይ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን በድህንነት ስጋት በሀገራችን ውስጥ ከቤታችን ሳንወጣ ተሳቀን፣ ነፍስግቢ ነፍስ ውጪ ላይ ነበርን፣ በመንፈስ ድቀትና ተስፋ መቁረጥ አብዛኞቻችን ሞተናል!

ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆይ፣

እርሶ ወደ ውጪ እግሮን ባነሱ ቁጥር አደጋ፣ ስቃይና መከራ ይመጣብናል። ተቋማትን አላጠናከሩም፣ በርስዎ ምትክ ማንን እንደተኩ አናውቅም፣ ሀገሪቱ መፈንጫ ትሆናለች። ለዚሁም ነው በዚህ ሁለት ቀናት “አብይ ሆይ ካሁን በሗላ ወደ ውጪ ሲወጡ፣ እባክዎ ይዘውን ይውጡ” እየተባለ ያለው።
ህግ አይከበርም፣ ጥፋተኛ አይቀጣም፣ የገደለ አይታሰርም፣ የአሰራር ክፍተት ያሳየ የመንግስትዎ ሀላፊዎች የሚያስጠይቃቸው አሰራር የለም። ሁሉ ነገር ተድበስብሶ ያልፋል። እርሶም አርሙን እየነቀልን፣ ስንዴውን እንንከባከባለን በሚል የተደበሰበሰ አባባል ያልፉታል። እኛ ይህ አይነት ጅምላ አገላለፅ ሰልችቶናል።

ማነው አረም? ይለይና በህግ ይጠየቅ። በህግ ጥላ ስር ይሁን። እንትና አረም ሆኖብኛል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኔ ሁን ይበሉን። እኛ ለእርሶና ለመንግስቶ እንዲሁም ለሀገራችን እንቆማለን።

ጠቅላያችን የተፈጠረውን ይህን መዓት ከስሩ አጣርቶ ምክንያትን ከውጤት አሰናስኖ ለርስዎም ሆነ ለፓርላማ የሚያቀርብ ኮሜቴ ሾመው ለምን ለኢትዮጵያ ህዝብ አያሳውቁም?

ለምን ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአስቾካይ አጣርቶ ለህዝ እንዲያሳውቅ ማሳሰቢያ አይሰጡም። እነዚህ መንገዶችና አመራር የሚሄድባቸው ሌሎች ቆራጥ እርምጃዎች እንዴት ከመግለጫዎ ይጎድላል?

ውድ ጠቅላያችን ሆይ፣

በዚህ ሁለት ቀናት ለተፈጠረው ችግር ምንም የማያሻማ ያልተድበሰበሰ ሀቅ አለ። ከፀጥታ ክፍሎች፣ ከፌዴራል ፖሊስ ለጃዋር መንግስት የመደበውን ጥበቃ ጃዋር ሳያውቅ ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ለመቀየር አመራር የሰጠ አካል አለ። ይህ አመራር ማነው? ይህ አመራር ከሗላው ምን ተልዕኮ ይዟል? ትዕዛዙን አስፈፃሚዎች የእዝ ሰንሰለት ምን ይመስላል? ይህ በሆነ በሰዓታት ውስጥ እንዴት ይህ ሁሉ ሰው ተንቀሳቀሰ? የኦሮሚያ ክልል ፖሊስና ልዩ ሀይል እንዴት ህዝቡን መታደግ አቃተው? ጃዋር የሚባለው ሚናው ያልተለየ ከርስዎ ስልጣን በላይ በመሆን ለህይወቱ ስለሰጋ ይህንን ሁሉ መከራ በሀገሪቱ ላይ ማውረዱ እንዴት ነው የሚታየው? ሌሎች አማራጮች እያሉ ወጣቶች አስቆጥቶ ወደ አደባባይ ማስወጣቱ በህግ አያስጠይቀውም። እሱ አደጋ ተደቀነብኝ ባለ ቁጥር ሚስኪኑ የሀገር ልጅ፣ ከከፖለቲካ የራቀው ቄስ እንዴት ይገደላል? እንዴት ቁርዓን ተቃጥሎ ሜዳ ላይ ይበተናል? የሀገር መከላከያ፣ የሌሎች ሀገሮችን ሰላም የሚያስከብር መከላከያችን እንዴት ተወርዋሪና ፈጣን እርምጃ ሳይወስድ ዜጎች ባደባባይ ተገድለው፣ ሬሳቸው በገመድ ሜዳ ለሜዳ ሲጎተት ዝም ብሎ በመመልከት ከሁለት ቀን በሃላ መግለጫ ይሰጣል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፣

በሌሎች ሀገሮች እንዲህ ያለ አመፅ ሲነሳ የፀጥታ ሀይሎች ከህዝብ ወገን ይቆማሉ። አድማ በታኝ ያሰማራሉ፣ በጭስ፣ በውሃ፣ በፕላስቲክ ጥይት፣ ከፍሲልም በጠምመንጃ እራሳቸውንም ህዝብንም ይከላከላሉ። በዚህም ምክንያት እነሱም ይጎዳሉ፣ ይሞታሉ። ህዝብም ዘላለም ያስታውሳቸዋል። በዚህ ሁለት ቀን ይህ ሊታይ ቀርቶ ሽታውም አልነበረም። ተቋም አጥተናል፣ ወታደርና ፖሊስ አጥተናል። ጠባቂ አጥተናል። ጠቅላይ ሚኔስትር፣ አረም ነቃይ የለንም፣ እንደስንዴ የሚንከባከበን መንግስት የለንም! አባት እንደሌለው ልጅ የማንም መጫወቻ ሆነናል። በዚህም ሆድ ብሶናል። በሀገራችን ተስፋ ልንቆርጥ፣ በእርሶም ተስፋ ልንቆርጥ ጫፍ ላይ ነን።

ጠቅላይችን ችግሮች አይፈጠሩ፣ ምንም ኮሽ አይበል አላልንም ነገር ግን ምንም አርምጃ ሲወሰድ ባለማየታችን ስጋት ገብቶናል። ወደ ብልፅግና እንጓዝ ይሉናል፣ ግንኮ ከብልፅግናው በፊት ለህልውናችን ተኩረት ሊሰጠው ይገባል። እንዴት በተከበረች ሀገር ዜጎቹን የሚጠብቅ ከአጥቂ የሚያስጥል ፖሊስ፥ የሚገዛን ህግ ይጥፋ? እንዴት ጠባቂ ወታደር እንጣ? እንዴት አለውልህ ባይ እንጣ?

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፣

እርስዎ አረመኔ እንደልሆኑ እናውቃለን፣ እርስዎ ኢትዮጵያና ህዝቧን እንደሚወዱ እናውቃለን። እርስዎ ታሪክ የሚንከባከቡ፣ ሌሎችን ከፍ በማድረግ ከፍ ማለት እንደሚቻል የገባዎት ምንም የበታችነት መንፈስ የማያሰቃዮት መሪ እንደሆኑ እናውቃለን። ለሀገርዎ እየለመኑ እንደሚያመጡ፣ እዳ እንደሚያሰርዙ፣ በርግጥም የተናገሩትን ሰርተው እንዳሳዩን እናውቃለን።

ግን ጠቅላይ ሚኒስቴር በዚህ መንገድ ብቻ አይመዘኑም። በርስዎ አስተዳደር ስር ህግ ረክሳለች፣ ዱርዬ ነግሷል፣ ግለሰቦች የተቋም ሚናን ይዟል፣ የፀጥታ ሀይሎች ከወጣቶች ጋር በአንድነት ሆነው መንገድ ሲዘጉ አይተን አፍረናል፣ በመንጋ ሰው ሲገድሉ፣ ዘቅዝቀው ሰቅለው ሲያቃጥሉ፣ በድንጋይና በዱላ ሰው ጨፍጭፈው ሲገድሉ፣ ገድለው ሜዳ በገመድ ሲጎትቱ ታዝበናል። ይህ በኢትዮጰያ ታሪክ ከዚህ ቀደም ያልሆነ እና የማይታሰበው ነገር፣ ዛሬ የሆነው፣ እና እየሆነ ያለው በእርስዎ አስተዳደር ስር ነው።

ጠቅላችን፣ ትህትናዎ ላይ ተሹፏል። ይቅርታባይነትዎ ላይ ተቀልዷል። ማሃሪነትዎ ላይ ሰዎች ተሳልቀዋል። ዝቅ ብለው ለሀገርዎ ከጭቃ ጋር ታግለው ችግኝ መትከልዎ፣ በየሀገራቱ እየሄዱ ማስታረቁ፣ ሰው ሁሉ ሳይታሰር በነፃነት እንዲናገር፣ እንዲንቀሳቀስ መፍቀድዎ፣ ጋዜጠኛና ፖለቲከኛ ያለእስር እንደፈለገው እንዲፅፍ፣ እንዲሰባሰብ እና እንዲደራጅ በመፍቀድዎ እንደቂል ታይተዋል።

በንደዚህ ያሉ መንገዶች ብቻ ሀገር ሊመሩ አይችሉም። ሰይፍም ማንሳት አለቦት። ህግ መከበር አለበት። ይህ እርምጃዎ እክል ከገጠመው እርዳታ ከዜጎች ይጠይቁ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪ ያቅርቡ። የ ኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር ወዳድ፣ ቆራጥና ጀግና መሪን አቤት ማለት ያባቶቹ ነው! የኢትዮጰያ ህዝብ በውድ ሀገሩ አይደራደርም! እርስዎ አሁን በያዙት መንገድ ሀገራችንን እንዳናጣ ስጋት አለን። እየተጠቃ ያለው ሰው ሲመረው እንስሳ ይሆናል። ገዳዩን ይገላል፣ ገሎ መሄድ ብቻ አይበቃም፣ መገደልም ይኖራል። ሞትን ቀስ በቀስ እየለመድን መሆኑ ያስፈራናል። ስለዚህ ክፉ ጊዜ እንደሚመጣ ይኸው ምልክት አይተናል። ከባዱ ጊዜ ሳይመጣ ነቃ ብለው በህግ ሰይፍ ስር ሀገሪቷን ኮምጨጭ ብለው ይምሩ!
እልዎታለሁ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

አክባሪዎ
ሙክታር ኡስማን አደም
ከጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ
የህግ መመህር
ጂግጂጋ

LEAVE A REPLY