ኦርቶዶክሶችን ማጥቃቱን ተከትሎ ቤ/ክርስቲያን ከገቡ የዶዶላ ነዋሪዎች 2 እርጉዞች በድንኳን ወለዱ
ከረቡዕ ዕለት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በምዕራብ አርሲ፤ ዶዶላ ከተማ በተፈጠረ ግጭት ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የተላኩ ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ የ8 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ከነዋሪዎች ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን አድርሶናል።
አራት ቀናት በዘለቀዉና እስካሁን ባልበረደው ግጭትና ግድያ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በከተማዋ በሚገኙ ቤተክርስቲያናት ተጠልለው እንደሚገኙ እንዲሁምጨቅላ ሕፃናት፣ እናቶች፣ አረጋዊያን እና ሕሙማን ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን የዶዶላ ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ልሳናት ቀሲስ እየበሩ ዓለሙ ይፋ አድርገዋል::
ዲያቆን ደለለኝ ማሞ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በሚገኙበት ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁለት እናቶች ያለ ምንም የህክምና እርዳታ መውለዳቸውን መስክረዋል። “ጭንቀት ውስጥ ነን ያለነው” ያሉት ነዋሪዎች በዶዶላ ከተማ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙት መካከል የሦስት ቀን አራስ እንደምትገኝም ተናግረዋል።
ረቡዕ ዕለት ወጣቶች ከፊት ለፊታቸው የነበሩ ቤቶችን ሲያቃጥሉ አይተው እግሬ አውጭኝ ብለው የሸሹና ሕይወታቸውንም ለማቆየት ቤተክርስቲያኗ ውስጥ እንደተጠለሉየገለጸችው ነዋሪ ደግሞ “ወደኛ ድንጋይ ሲወረውሩ፤ በጓሮ በኩል አጥር ቀደን ወጣን፤ ምንም ሳንይዝ እያለቀስን ነው የወጣነው፤ በሰው ግቢ በኩል እየተረማመድን ወደ ቤተክርስቲያኗ መጣን” ስትል የግጭቱን አስከፊ ገጽታ አስታውሳለች።
የነበረው ሁኔታ በጣም አስፈሪ ነበር የምትለው አራሷ የዶዶላ ነዋሪ የተገላገለችው ቤተክርስቲያኗ ውስጥ እንደሆነ”በልምድ የሚያዋልዱ ሰዎች ረድተውኝ በሰላም ተገላግያለሁ፤ ጡቴ ወተት እምቢ ብሎ ወተት እየለመንኩ የሚጠባው አጥቶ፤ ውሃ በጡጦ እያጠባሁ ነው ያለሁት” ስትል መጥፎውን አጋጣሚ ተርካለች።
ከሐዋሳ እናቷ ጋር ለመታረስ ብትመጣም በነበረው ብጥብጥ እናቷን ጨምሮ የሰባት ወር ህፃን የያዘች የአክስቷ ልጅ፤ በአጠቃላይ ሦስት ህፃናትና አራት አዋቂዎች ሆነው እንዳመለጡ ከሞት እንዳመለጡ ጠቁማለች።
በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ እንደሆነ የምትናገረው ያስታወቀችው እናት እስካሁን ምግብ እንዳልቀመሰችና ሻይ ብቻ እየጠጣች መተኛቷን ዛሬ ተናግራለች። ወደቤትም ሄደውም ሆነ ውጭ ወጥተው ለመብላት ለደህንነታቸው ስለሰጉ ችግር ላይ መሆናቸውን አስረድታለች።
ረቡዕና ሐሙስ ዕለት የተቃውሞ ሠልፍ በተካሄደባቸው የኦሮሚያ፣ ሐረርና ድሬዳዋ ከተሞች በክልሎችና በአስተዳደሩ ጥያቄ መሰረት የመከላከያ ሠራዊት መሰማራቱንና ሁኔታዎች እንደተረጋጉ ቢገለፅም አራሷ ግን ይህን መግለጫ በማጣጣል”ተረጋግቷል የሚባለው መንቀሳቀስ ሲቻል ነው። ያሉት ወታደሮችም ቤተ ክርስቲያኗን በመጠበቅ ላይ ናቸው” በማለት ከተረጋጋ ነገር ይልቅ አሳሳቢ ችግር መኖሩን አመላክታለች።
“ያለነው በመከራ፣ በስቃይ ነው፤ ከፍተኛ ብርድ አለው፤ አራስ ሆነን ውጭ እያደርን ነው፤ የታመሙ ህፃናት አሉ፤ አንዲት የአምስት አመት ልጅ ቶንሲል ታማ ስታለቅስ ነበር ፣ ግን ምን ማድረግ ትችላለች” ስትል መንግሥት እንዲደርስላቸው ተማፅናለች። በተመሳሳይ ዲያቆን ደለለኝም በኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው እንዳሉና ከሁለት መቶ በላይ አባወራዎችም ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን ይዘው በመቃብር ቤቶች እንዲሁም ድንኳን ውስጥ እንደሚገኙ ተናግሯል።
የሦስት ቀጠና ማህበረሰብ፤ ቀጠና 4፣ 5 እና 7 በዚችው ቤተክርስቲያን ተጠልለዋል:: ሌሎች ደግሞ በቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ይገኛሉ ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው ዕለት ከተማዋ መጠነኛ መረጋጋት እንደታየና ከቤተክርስቲያኗ በቅርብ ርቀት የሚገኙ ሰዎች ከቃጠሎ የተረፈ ንብረትም በመሰብሰብ ጀምረዋል የሚሉት የዜና ምንጮች በቤተክርስቲያኗ ዙሪያ አንድ ፓትሮል፣ አስራ ሁለት የሚሆኑ የመከላከያ አባላት ብቻ በአካባቢው እንዳሉ አረጋግጠውልናል::
ተጠልለው የሚገኙት ምዕመናንም በምግብና ውሃ እጥረት እየተሰቃዩ ይገኛሉ:: “አንዳንድ ግለሰቦች ከውጭ ምግብ እያመጡ በሚረዱት ነው እየተዳደርን ያለነው። በጣም የተቸገርነው ደግሞ ውሃ መቅዳት ባለመቻሉ ነው።” ሲሉ ሁኔታውን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ የሚመጣው የውሃ መስመር በመቋረጡ፣ እንዲሁም ወንዝ ሄደው እንዳይቀዱ ለደህንነታቸው በመስጋታቸው በውሃ ጥም እየተሰቃዮ እንደሚገኙና ቤተክርስቲያኗን ለቀው ቢወጡ አካባቢውን የሚጠብቀው ኃይል ለደህንነታቸው ዋስትና ስላልሰጣቸው አሁንም ስጋት እንዳደረባቸው፣በጭንቀትም ላይ እንደሚገኙ ሕዝብና መንግሥት ይድረሱልን ባሉት መልዕክታቸው ላይ አስገንዝበዋል።
የጃዋር ደጋፊዎች ነን ያሉት መንጋዎች ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ነው በከተማዋ እየፈጸሙ ያሉት የሚናገሩት ዲያቆን ደለለኝ በእነዚህ የተደራጁ አካላት ስምንት ቤት መቃጠሉን፣ የተዘረፈና የወደመ ንብረት በስፋት መኖሩን ጠቁመው ረቡዕ ዕለት በቤተክርስቲያኗ አባቶች ላይ ከባድ ድብደባ መፈጸሙንም አጋልጠዋል።
እስካሁን በአደጋው የሞቱ ስድስት ሰዎች እንደተቀበሩና በዛሬው ዕለትም ከሃዋሳ የመጣች አንዲት ሴት ዛሬ መቀበሯን በፍጥነት ያደረሱን የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች፤ በሞትና በሕይወት ስላለው ሰው አሁን ላይ ርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻልል እና ሦስት ሰዎች በሞትና በህይወት መካከል እንደሚገኙ አስታውቀውናል::
ከረቡዕ ዕለት አንስቶ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ህፃናት ፣ ሴቶች፣ አረጋዊያን ተጠልለው እንደሚገኙ ገልፀው፤ የተጎዳ ሰው ለመጠየቅ ትናንት ወደ ሆስፒታል በማምራት ላይ የነበረች አንዲት ሴት ድብደባ ተፈፀሞባት ሕይወቷ በማለፉ ዛሬ የቀብር ሥነ ሥርዓቷ መፈጸሙን አረጋግጠናል።
በርካታ ሰዎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት ተፈጽሟል ያሉ ምንጮቻችን የ8 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ቤቶች መቃጠላቸውን ፣ ንብረቶች መውደማቸውን አመላክተው ፤ ዛሬ ጠዋት ላይ መንገድ ተከፍቷል በሚል ከተለያየ ቦታ ለለቅሶና ለሌላ ጉዳይ የመጡ ሰዎች ላይም የማዋከብና የማሰር ድርጊት እየተፈፀመ መሆኑ ደግሞ መንጋውንና የከተማዋን የጸጥታ ኃይል ሚና ለመለየት አስቸጋሪ ከማድረጉ ባሻገር መንግሥት ጉዳዮን ያወቀዋል ወይ? የሚል ጥያቄን አጭሯል።
“በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው የተፈፀመው፤ ሰው መረጋጋት አልቻለም። እናቶችና ሕፃናት እየተራቡ ናቸው፤ ውሃ ወጥቶ መቅዳት አልቻልንም። ወደ ፈጣሪ ከመጮህ ውጭ ሌላ የምናደርገው ነገር የለም” የሚሉት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉት ነዋሪዎች በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይናገራሉ::
ግጭቱም ከብሔር ጋር የተገናኘ ቢሆንም መልኩን ቀይሮ ወደ ወደ እምነት እንደዞረ እና በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ያለው፣ በአብዛኛው የኦርቶዶክስ አማኞች መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል::
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዮ ከተሞች 67 ሰዎች እስካሁን ሞተዋል ሲል አመነ
የጃዋር መሐመድን የድረሱልኝ ጥሪ ተከትሎ ከሰሞኑ በተከሰቱ ግጭቶች የሟቾች ቁጥር ስልሳ ሰባት መድረሱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አስታውቋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ግጭቶቹ በተከሰቱባቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች መሐል በተለይም በድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞች ስልሳ ሁለት ንፁሃን ዜጎች፣ እንዲሁም አምስት የፖሊስ አባላት መገደላቸውን የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራ ይፋ አድርገዋል። አስራ ሦስቱ በጥይት የተገደሉ ሲሆን ፣ ቀሪዎቹ 54 ሰዎች ደግሞ በድንጋይ ተደብድበው መገደላቸውን ከሓላፊው ዘገባ መረዳት ተችሏል።
ግድያውን አስመልክቶ የተለየ ዘገባ ያቀረበው ኒዮርክ ታይምስ በበኩሉ አስራ ሦስቱ ሰዎች የሞቱት በፀጥታ ኃይሎች ጥቃት እንደሆነና የሌሎቹ የግድያ መንስዔ ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭት መሆኑን ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል:: 213 ሰዎች በተጨማሪነት መቁሰላቸውንም ዘግቧል።
ከግማሽ በላይ ለሆነው የግድያ መንስዔ ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭት መሆኑን የየአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት፣ የሆስፒታል ምንጮች እና ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን ፤ ቢቢሲ ከተለያዩ አካባቢዎች ባለሥልጣናት፣ ከሆስፒታል ምንጮችና ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ የሟቾች ቁጥር 44 መድረሱን ትናንት ምሽት ዘግቦ ነበር።
ይሁንና ትናንት ከሰዓት በኋላና ማምሻውን እንዲሁም እስከ ቅዳሜ ማለዳ ድረስ በደረሱ ተጨማሪ አደጋዎችና ቀደም ሲል በሆስፒታል ገብተው ሕክምና ሲጠቀሙ የነበሩትን ጨምሮ የሟቾቹ ቁጥር 67 መድረሱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል::
በኮፈሌ ክርስቲያን የሆኑ የአንድ ቤተሰብ አባላት በመንጋዎች ተገደሉ
በኮፈሌ ሃይማኖታዊ እና ብሔር ተኮር ጥቃትን የተላበሰው የጃዋር ደጋፊዎች የቀሰቀሱት ግጭት ተባብሶ እንደቀጠለ ነው የተሰማው:: በምዕራብ አርሲ ዞን ኮፈሌ ከተማ ነዋሪ የነበሩ 2 ዘመዶቹ እና አንድ በዘመዶቹ ቤት ያደገ ወጣት እንደተገደሉበት ለቢቢሲ ተናግሯል::
አቶ ታምራት ጸጋዬ የአብነት አክሊሉ አጎት (የእናቱ ወንድም) ሲሆኑ፤ ረቡዕ ዕለት በተፈጠረው ግርግር አቶ ታምራት ጸጋዬ፣ ልጃቸው አቶ ሄኖክ ታምራት ጸጋዬ እና በአቶ ታምራት ቤት ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ ወጣት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መገደላቸውን አብነት አክሊሉ ገልጿል።
“ተሰብስበው ወደ አጎቴ ቤት መጡ። ከዚያ በመጀመሪያ አጎቴን (አቶ ታምራት ጸጋዬ) ገደሉት። ከዚያ በተመሳሳይ ሁኔታ ልጁን ገደሉት። ከዚያ ቤት ውስጥ ያደገ ሱቅ ውስጥ ይሰራ የነበረ ልጅ ገደሉ” ሲሉም ሀዘን በተሞላበት ተናግረዋል::አብነት የሟች አስክሬን ላይም አስነዋሪ ድርጊት መፈጸሙን ጠቁሟል::
የአቶ ታምራት ልጅ፤ ሄኖክ ታምራት ጸጋዬ በቅርቡ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ በምጣኔ ሃብት ዘረፍ የተመረቀ ሲሆን ፤ አቶ ታምራት በኮፈሌ ከተማ ወፍጮ ቤት፣ ሆቴል እና መኪኖች እንዳሏቸው ተሰምቷል። የቤተሰብ አባላቱን ከተገደሉ በኋላ የአቶ ታምራት መኖሪያ ቤት እና መኪናም ተቃጥሏል።
የአቶ ታምራት እና የልጃቸው ትውልድ እና ዕድገት እዛው ኮፈሌ መሆኑን የሚናገረው አብነት “ተወልደው ባደጉበት ኮፈሌ እንኳ መቅበር አልቻልንም። በስንት መከራ ዛሬ በናዝሬት ከተማ 10 ሰዓት ላይ ቀብራቸው ተፈጽሟል” በማለት የገጠማቸውን ችግር ያስረዳል።
16 ሰዎች የሞቱባት የአዳማ ግጭት ከጎዳና ወደ ሆስፒታል ተሸጋገረ
“ቄሮ” ነን ባዮቹ የጃዋር አሕመድ ተላላኪዎችን ድባቅ መትቶ ወደ መጡበት ጋራ እና መንደር በመሸኘት ግንባር ቀደሙን ሚና የተጫወተው የአዳማ ሕዝብ በተለያዮ ግጭቶች አስከፊ አደጋዎችን ከሰሞኑ ሲያስተናግድ ከርሟል:: ከረቡዕ እስከ ዛሬ (ዓርብ) ድረስ ወደ አዳማ ሆስፒታል ህይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው የመጣ ሰዎች እና የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቶ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር በጠቅላላው 16 መሆኑን ያስረዳሉ።
ረቡዕ ዕለት ወደ ከተማዋ ሆስፒታል ከሄዱት መካከል ሁለቱ የአፍሪካ ዱቄት ፋብሪካ ዘበኛ ጥይት ተኩሶ የገደላቸው ሰዎች ይገኙበታል። የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሓላፊ ራውዳ ሁሴን የዱቄት ፋብሪካው ጥበቃ ጥይት ተኩሶ ሁለት ሰዎችን መግደሉን እና በዚህ የተበሳጩ ሰልፈኞ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ 15 መኪኖች ማቃጠላቸውን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ሆስፒታሉ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ተጎጂዎችን ያስተናገደው ትናንት አርብ ዕለት እንደሆነ የሚናገሩት ምንጮች “ትናንት ጉዳት ደርሶባቸው የመጡት ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ይሆናል” ያሉ ሲሆን ፤ የጉዳቱ መጠን ከከባድ እስከ ቀላል የሚባል እንደሆነ እና “በዱላ የተደበደቡ፣ በስለት ጭንቅላታቸው ላይ የተወጉ፣ በጥይት የተመቱ ሰዎችም አሉበት” አሉበት ሲሉ አረጋግጠዋል::በትናንትው ዕለት ብቻ ሕይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው የመጣ እና በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 12 እንደሆነም የከተማዋን ነዋሪዎች በማነጋገር መረጃ የሰበሰበው የኢትዮጵያ ነገ ዘጋቢ አድርሶናል።
ዘግየት ብሎ በደረሰን መረጃ መሠረት ረቡዕ ዕለት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ክፍል (አይሲዩ) ውስጥ የነበረ አንድ የ21 ዓመት ወጣት ዛሬ ጠዋት ህይወቱ አልፏል።
በዚህ ወቅትም በሆስፒታሉ በአደጋኛ የጤና ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ያሉ በመሆናቸው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ግምት መኖሩ ታውቋል:: አይኑ የጠፋ፣ አጥንቱ የተሰበረ በርካታ ሰውም እንዳለ ከሰበሰብነው የጉዳተኞች ዝርዝር ውስጥ አግኝተናል።
በከተማው ውስጥ ያለው ግጭት ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ዘልቆ ገብቷል ተብሏል:: ወንድሙ የሞተበት አንድ ወጣቶችአስክሬን ክፍል አቅራቢያ አምርሮ እያለቀሰ ፤ የተደራጁ ሰዎች የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲያለቅ የነበረውን ልጅ ላይ ጉዳት እንዳደረሱበት የኢትዮጵያ ነገ የዜና ምንጮች ይናገራሉ::
ሆስፒታል ውስጥ ጉዳት ተደርሶበት የተደበደበው ወጣት የቀዶ ህክምና ከተደረገለት በኋላ ፣ የጤናው ሁኔታ መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ የሆስፒታሉ ባልደረቦች ከታካሚ ብዛት እያጋጠማቸው ካለው የሥራ ጫና በተጨማሪ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት እንዳለም ሰምተናል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ (ቪኦኤ) የአፋን ኦሮሞ ክፍል ሪፖርተር የሆነው ጋዜጠኛ ሙክታር ጀማል በአዳማ ከተማ ‘ጀማል መጋዘን’ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በመንገድ ላይ ቃለ-መጠይቅ እያደረገ ሳለ ድብደባ እና ዘረፋ ተፈጽሞበት፤ ጭንቅላቱ እና ወገቡ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ጋዜጠኛ ሙክታር ሆስፒታል ተኝቶ የህክምና አገልግሎት እየተደረገለት ነው። ሙክታር ቃለ-መጠይቅ እያደረገ ሳለ የተደራጁ ወጣቶች መጥተው ድብደባ እንደፈጸሙበት ፣ ቦርሳውን ሲበረብሩ የቪኦኤ መታወቂያ ካርድ ካዩ በኋላ ትተውት እንደሄዱ ተናግሯል::