የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም

ቅዱስ ሲኖዶስና መጅሊሱ በሃይማኖት ግጭቶች ዙሪያ በዝግ እየመከሩ ነው

ቅዱስ ሲኖዶስና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና መጅሊስ በሰላምና በጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክር መጀመራቸው ታወቀ ፡፡

ከጥቅምት12 እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ በሀገሪቱ ሰላምና በህዝቦች አብሮ መኖር ፣ በምዕመናን ህይወትና በእምነት ተቋማት ላይ እየደረሰ ስላለው ጥፋት ውይይት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

በዚህ መሠረት በዛሬው ዕለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፣ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስ ፣የቋሚ ሲኖዶስ አባላት እንዲሁም የጠቅላይ ምክር ቤቱ ከፍተኛ መሪዎችበተገኙበት የመጀመርያው የጋራ ምክክር መካሄድ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል::

የኢትዮጵያ ነገ የቤተ ክህነት ምንጮች እንደገለጹልን ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዮ የኦሮሚያ ክልሎች በድሬደዋና በሐረር ከተሞች ክርስቲያኖችን ታርጌት ያደረገ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸሙ፣ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውና ካህናት መደብደባቸውና መገደላቸው እየተባባሰ መሄዱ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ያለመረጋጋት ተከትሎ አክራሪ ብሔርተኞችና ፖለቲከኞች አጋጣሚውን ወደ ሃይማኖታዊ ግጭት እየወሰዱት መሆኑ የሃገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የከፋ ችግር ላይ እንዳይጥላት በማሰብ የሃይማኖት አባቶቹ በችግሮቹና መፍትኄዎቹ ላይ በዝግ እየመከሩ መሆናቸውን ታማኝ ምንጮቻችን ነግረውናል::

የደቡብ ክልል መንግሥት ሲዳማን በዞንነት ለማቆየት ምንም ጥረት አለማድረጉን ኢሰማኮ አጋለጠ

የሲዳማ ክልል የሕዝበ ውሳኔ የምርጫ ቅስቀሳ፤ የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት እንዲቋቋም በሚጠይቀው የሻፌታ ቡድን ከፍተኛ የበላይነት የተሞላ ነበር ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ትናንት የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን አስመልክቶ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ብሎ ባወጣው መግለጫ፤ የሻፌታ ቡድን በሰላማዊ ሠልፍ፣ በስብሰባዎች፣ በጎዳናዎች፣ ቤት ለቤት በመዘዋወር፣ በመንገዶች እና በአደባባዮች ልዩ ልዩ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶችን በመስቀል ሰፊ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጉን ይፋ አድርጓል::

የሲዳማ ዞን የደቡብ ክልላዊ መንግሥት አካል ሆኖ እንዲቀጥል የቀረበው የጎጆ ቡድን ግን፤ የምርጫ መረጃው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በቴሌቭዥንና ሬዲዮ በተመደበለት ሰዓቶች ከመደመጡ በስተቀር፤ የምርጫ ቅስቀሳ አልነበረውም በማለት ሲዳማ በደቡብ ክልል ውስጥ እንድትቀጥል ጉዳዮ የሚመለከተው የክልሉ መንግሥት እንቅስቃሴ አለማድረጉንም አጋልጧል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የክትትል ቡድን አባላት በጎበኙት አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ የተወሰኑ የወጣት ቡድኖች ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፉ ሰዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መስተዋላቸውንም ገልጿል።

“ለአማራጩ የጎጆ ቡድን የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ የተከለከለ ነገር ባይኖርም፣ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ለኢሰመኮ ታዛቢዎች እንደገለጹት፤ በሲዳማ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ አማራጩን ሐሳብ በይፋ ለመቀስቀስ ስጋት እና ፍራቻ ነበር” በማለት የደቡብ ክልል መንግሥት ሲዳማ በዞንነት እንድትቆይ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አለማድረጉን በመግለፅ ሥልጣን ላይ ያለውን የክልሉን መንግሥት ለተመዘገበው ውጤት ተጠያቂ አድርጓል።

2.3 ሚሊየን መራጮች በተመዘገቡበት የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በመራጮች ምዝገባ ወቅት፤ የኢሰማኮ የክትትል ቡድን ለመራጭነት ዕድሜያቸው ያልደረሰ የሚመስሉ ነገር ግን ለአካለ መጠን የደረሱ መሆኑን የሚያመለክት መታወቂያ ካርድ ያላቸው የተወሰኑ መራጮች መመልከቱንም ኮሚሽኑ አጋልጧል።

 አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጨናነቀ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ሰላማዊ ምርጫን ለማደራጀት እና ለማስፈጸም የተቀናጀ ጥረት ማድረጉን ጠቅሶ፤ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አነስተኛ የሥነ ሥርዓት ችግሮች መታየታቸውንም በግልፅ አስቀምጧል።

ኢሰመኮ በዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተመራ 20 አባላት ያሉት የሰብዓዊ መብት ክትትል ቡድን ማሰማራቱ ተገልጾ፤ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ. ም. በተካሄደው ምርጫ ላይ የተከሰተ ይህ ነው የሚባል ችግር እንደሌለ ገልጾ የክትትል ቡድኑ በምርጫው ቀን በአምስት የከተማ አስተዳደሮች እና 15 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ከ100 በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መመልከቱንም አስታውቋል። የኮሚሽኑ የምርጫ ክትትል ቡድን በቅድመ ምርጫው ወቅትም ተጨማሪ የምርጫ ጣቢያዎችን መመልከቱን ጠቁሞ፤ የኢሰመኮ የክትትል ቡድን በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከ2000 የሚበልጡ መራጮች መመዝገባቸውን ማስተዋሉን ጠቅሶ፤ ይህም ለምርጫ ጣቢያዎች ሥራ አፈጻጻም አስቸጋሪ እንደነበርም አስታውቋል። እንደ የድምፅ መስጫ ሳጥን፣ የምርጫ ወረቀቶች እና ቀለም ያሉ የምርጫ ቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት ያስተዋለባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውንም አልሸሸገም።

በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መግባት፣ ድምጽ በሚስጥራዊነት ለመስጠት በበቂ ሁኔታ የተከለለ ሚስጢራዊ ቦታ አለመኖር፣ የድምፅ አሰጣጥን በሚመለከት ለመራጮች ተገቢውን መመሪያ ወይም መረጃ አለመስጠት፣ የምርጫ ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያው ውጭ መሆን፣ የተወሰኑ የምርጫ አስፈፃሚዎች የፌደራሉን የሥራ ቋንቋ [አማርኛ] የማይናገሩ እንደነበሩ በመጥቀስም ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አለመቻላቸውን መታዘቡንም በመግለጫው ኢሰመጉ አመላክቷል።

ኮሚሽኑ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ብቻ በመመርኮዝ ስለ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እና አንዳንድ ቁልፍ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶችን የሚገልጽ መሆኑን በመጥቀስ፤ አጠቃላይ የምርጫው ግምገማ አለመሆኑንም  ኅብረተሰቡ ልብ ሊል እንደሚገባ ባወጣው መግለጫ ላይ አስገንዝቧል።

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በዛሬው ዕለት ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና የሺዋስ አሰፋ ከጀርመን ፓርላማ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዮ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎና ተቀባይነት ባላቸው በሳል ፖለቲከኞች የተዋቀረው ኢዜማ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር በሰለጠነ መንገድ ለማስፋት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል::

ሀገሪቱ ካለችበት የብሔርተኝነት ፖለቲካ ልክፍትና ከደፈረሰው ሠላም አኳያ  ቀጣዮ ሃገራዊ ምርጫ መካሄድ የለበትም ብሎ የሚያምነው ኢዜማ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መካሄዱ ቁርጥ ከሆነ መሳተፉ አይቀሬ በመሆኑ ከወዲሁ በተለያዮ የሃገሪቱ ክልሎች ተዘዋውሮ ከኅብረተሰቡ ጋር የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ ይገኛል::

ዛሬ ደግሞ የኢዜማ ዋነኛ መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና በአደረጃጀት የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋከጀርመን ፓርላማ ምክትል ፕሬዚዳንትና ከልዑካቸው ጋር ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም ቀጣዩ ምርጫን አስመልክቶ ገለጻ ከማድረግ ባሻገር ሰፊ ውይይትና አካሂደዋል::

በቀጣዮ ሃገራዊ ምርጫ አዲስ አበባን ጨምሮ የኢትዮጵያ አንድነት በቀዳሚነት በሚቀነቀንባቸው የተለያዮ ከተሞች አሸናፊ ሊሆን ይችላል ተብሎ በብዙዎች ቅድመ ግምት የተሰጠው ኢዜማ  እረፍት የለም በሚል መንፈስማደራጀት፣ ማሰልጠን እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት(ውይይት) በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከአንድ ቤተሰብ ስድስት ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን አጡ

ኢትዮጵያውያንን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀጠፈ የሚገኘው የመኪና አደጋ አሁንም እየተባባሰበት ይገኛል:: ዛሬ ይፋ በሆነው መረጃ በደቡብ ክልል ከንባታ ጠምባሮ ዞን ፣ ሀደሮ ጡንጦ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የስድስት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ለማወቅ ተችሏል።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ማቲዎስ አደጎ እንደገለጹት ከሆነ አደጋው የደረሰው ትናንት ማለዳ 12 ሰዓት አካባቢ በሀደሮ ጡንጦ ወረዳ በተለምዶ ሌሾ ማዞሪያ ነው። ኤፍ ኤስ አር የጭነት ተሽከርካሪ ከዶዮገና ወደ አረካ በመጓዝ ላይ እያለ ነፍሰ ጡር ይዞ ወደ ጤና ጣቢያ በመጓዝ ላይ ከነበረ ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ጋር በመጋጨቱ አሳዛኙ አደጋ ደርሷል።

ብዙዎችን ባሳዘነውና እንባ ባራጨው አደጋ ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት እንደሆኑ እና፤ አስክሬናቸውን ቤተሰብ መረከቡንም ኮማንደሩ ገልጸዋል። ከሟቾቹ በተጨማሪ አንድ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባት የቤተሰቡ አባል በዱቦ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት መሆኑንም ተናግረዋል።

አሽከርካሪው ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝም  የጠቆሙት ኮማንደር ማቲዎስ የአደጋው መንስኤ ለጊዜው ባይታወቅም ሲጥል የነበረው ዝናብ ጋር ተያይዞ በመጋረድ ምክንያት የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠው፤ አሁን ላይ ወቅቱ ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን በመቆጣጣር ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ምክር ለግሰዋል::

የተባበሩት መንግሥታት ለማዕከላዊ አፍሪካ የሚያደርገውን ዕርዳታ አቆመ

የተባበሩት መንግሥታት፤ በማዕከላዊ አፍሪካ ተወክሎ የነበረ ግለሰብ ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ተፈርዶበት የነበረ መሆኑን በመጋለጡ የተነሳ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ማቋረጡ ተሰማ።

የተባበሩት መንግሥታት ከ’ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ’ ጋር በመሆን፤ በ’ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ’ (ማዕከላዊ አፍሪካ) የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይሰጥ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት የተራድኦ ክፍል እንዳለው፤ የቀድሞው የ’ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ’ ወኪል የሆነው የቤልጄየም ቄስ ሉክ ዴልፋት፤ ህጻናት ይበዘብዝ እንደነበር ክሶችእየቀረቡበት ነው።

አሁን ግለሰቡ ከሥልጣኑ መነሳቱ ቢገለጽም የማዕከላዊ አፍሪካ አመራሮች እንዲሁም የቤልጂየም እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ጉዳዩን እየመረመሩም ይገኛሉ። በማዕከላዊ አፍሪካ መዲና የሚገኙ አቃቤ ሕግ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት፤ ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ቄሱ ላይ ክስ ተመስርቶበታል።

የተባበሩት መንግሥታት የተራድኦ ክፍል (ኦሲኤችኤ)፤ ወሲባዊ ጥቃትና ብዝበዛ አንታገስም ካለ በኋላ ተቋሙ የምርመራው ውጤት ይፋ እስኪደረግ እገዳው አይነሳም ሲል አቋሙን አስታውቋል።

ቄስ ሉክ ዴልፋት፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2012 ላይ በወሲባዊ ትንኮሳ ተከስሰው ተፈርዶባቸው እንደነበር አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ለ10 ዓመት ያህል ከህጻናት እና ከታዳጊዎች ጋር ከሚያገናኘው ሥራም ታግዶ ነበር።ሆኖም ግን በ2013 ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ተልኮ፤ 2015 ላይ በ ‘ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ’ ተቀጥሯል። ‘ዲግኒቲ ፋውንዴሽን’ እንዳለው፤ ቄሱ የተመደበው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥቃትን ለመከላከል ባቋቋመችው ቦታ ላይ ነው።

በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው ካጋ ባንዶሮ ለሁለት ዓመት የሠራው ቄስ በቀጣይ የ ‘ካቶሊክ ቻሪቲ ካሪትስ’ ዋና ጸሐፊ ሊሆን መቻሉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

LEAVE A REPLY