በኮሮና ቫይረስ ከተጠረጠሩት 113 ሰዎች መካከል 74ቱ ነፃ መሆናቸው ታወቀ

በኮሮና ቫይረስ ከተጠረጠሩት 113 ሰዎች መካከል 74ቱ ነፃ መሆናቸው ታወቀ

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ||

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ በሽታ (ኮቪድ -19) ስርጭትን አስመልክቶ በሰጠው መረጃ:-

• በዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሠረት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2012 ይህ መረጃ እሰከ ተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 174 ሺህ 881 ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም 77 ሺህ 781 ጤንነታቸው ተመልሷል።
6 ሺህ 526 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል።

• በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ያሏቸው መሆኑን 158) ሀገራት ሪፖርት አድርገዋል።

በሀገርአቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለ የዝግጅት ሁኔታ:-
• በሁሉም ወደ ሀገር መግቢያ ጣቢያዎች እየተደረገ የሚገኘው ምርመራ የተጠናከረ ሲሆን 600 ሺህ 080 ሰዎች በሙቀት መለያ (ኢቦላ እና ኮቪድ-19 በማጣመር) አልፈዋል፡፡

• በሙቀት መለያ ካለፉት ውስጥ 8 ሺህ 985 በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ አገራት የመጡ ናቸው፡፡

•በሽታው ሪፖርት ከተደረገባቸው አገራት የመጡ ተጓዞችን በተጨማሪ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ማረጋገጥ ከተቻለው 5 ግለሰቦች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸውን 992 ባሉበት ቦታ ለ14 ቀናት የሚደረግ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ።
1285 የሚሆኑ ሰዎች ለ14 ቀን የጤና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው ጤንነታቸው በመረጋገጡ የጤና ክትትላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

የበሽታውን ተመሳሳይ ምልክቶች በማሳየታቸው እንዲሁም ከመጀመሪያው ታማሚ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት 113 ሰዎች በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ማእከል እንዲቆዩ ከተደረጉት መካከል የላብራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ 74ቱ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
አምስቱ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ታማሚዎች ሲሆኑ፣ በለይቶ ማቆያ የሕክምና መስጫ ማእከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
34 ሰዎች ደግሞ በለይቶ ማቆያ ሆነው የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
• አምስቱ የኮሮኖ ቫይረስ ታማሚዎች በአሁኑ ሰዓት በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት ሕብረተሰብ የሚሳተፍባቸው ቦታዎችን እንደ ትምህርት ቤቶች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና ስብሰባዎችን ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት እና ለመቆጣጠር በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ሕብረተሰቡ በተለይም የበሽታውን ምልክት ያሳዩ ወይም ተጠርጣሪዎች ተብለው በለይቶ ማቆያ አካባቢ የሚሆኑ ግለሰቦች ምንም እንኳን ውጤታቸው ነፃ መሆናቸው ቢረጋገጥም፣ የማግለል ባህርይዎች እንዳይከሰቱ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እና ስለ ኮሮኖ ቫይረስ ወረርሽኝ ምንነት፣ መከላከያ መንገዶች በጥልቀት ሊረዳው የሚገባ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡

ሕብረተሰቡ ከዚህ በፊት ማንኛውንም በሽታ ለመከላከል ሲጠቀምባቸው የነበረውን የበሽታ መከላከያ መንገዶች ችላ ሳይል እና ሳይደናገጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

● ሳል ወይም ትኩሳት ካለው ግለሰብ ቢያንስ ሁለት የአዋቂ እርምጃ ርቀት ያህል መራቅ
● እጅዎን በአግባቡ ሳይታጠቡ አይንና አፍንጫዎን አይንኩ፣
● ከሰዎችጋር አይጨባበጡ፣
● እጅን በንጹሕ ውኃ እና ሳሙና አዘውትረው ይታጠቡ፣
● ሰዎች ወደ በሚበዙባቸው ቦታዎች በተለይም የሕመም ስሜት ካለዎት አይሂዱ፣
● በሚያነጥሱበት እና በሚያስሉበት ጊዜ አፍ እና አፍንጫዎን በሶፍት ወይም ክርንዎን አጥፈው በመጠቀም ወደ ሌሎች እንዳያስተላልፉ ይጠንቀቁ፣ የተጠቀሙበትን ሶፍት እና ተመሳሳይ ነገሮች በቆሻሻ ክዳን ባላቸው ማጠራቀሚያ ያስወግዱ፣
● በሥራ ቦታ፣ በትራንስፖርት እና መኖሪያ ወይም የመኝታ ክፍል መስኮት በመክፈት በቂ አየር እንዲኖር ያድርጉ፣
● መረጃዎችን ከአስተማማኝ ምንጮች ብቻ በመቀበል፣ የተሳሳቱ መረጃዎች የሚያስከትሉትን መደናገር እና ፍርሃት ይከላከሉ!

በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሀገራት የሚመጡ ሰዎች ወይም ንክኪ ያላቸው ማንኛውም ግለሰብ ራሱን ለ14 ቀን በመለየት በበሽታው አለመያዛቸውን ሲያረጋግጡ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መክሯል።

ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 011-8-27-67-96 መደወል ወይም በኢ-ሜይል አድራሻ ephieoc@gmail.com በመጠቀም መረጃ ማግኘት ይቻላል ብሏል፡፡

LEAVE A REPLY