ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሁለት ጊዜ የኦስካር አሸናፊው አሜሪካዊው ተዋናይ ቶም ሃንክስና ባለቤቱ ሪታ ዊልሰን በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ በአውስትራሊያ ህክምና ሲከታተሉ ከነበረበት ሆስፒታል መውጣታቸው ታወቀ።
ዝነኞቹ ጥንዶች በአውስትራሊያዋ ጎልድ ኮስት የተገኙት የኤልቪስ ፕሪስሊ ሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ፊልም ለመስራት ነበር። የ63 ዓመቱ ስመ ጥር የፊልም ባለሙያቶም ሃንክስ ባለፈው ሐሙስ እሱም ባለቤቱም በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያሳወቀው በሥራ ላይ ካለበት አውስትራሊያ ነው።
ቶም ሃንክስና ባለቤቱ በሆስፒታል አስፈላጊው እርዳታ ተደርጎላቸው ቢወጡም ፤ አሁንም እዚያው አውስትራሊያ ክዊንስላንድ ውስጥ በተከራዩት ቤት ራሳቸውን ለይተው እንደሚቀመጡ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ከኦስካር ተሸላሚው ቶም ሃንክስ ብቻ በተጨማሪእንግሊዛዊው ተዋናይ ኢድሪስ ኤልባም በቫይረሱ መያዙን በትናንትናው እለት በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሯል። ኢድሪስ ኤልባ እንዳለው ምንም ዓይነት የህመም ስሜት ባይኖርበትም አግኝቶት የነበረ ሰው በቫይረሱ ስለተያዘ እንደተመረመረና በውጤቱም እሱም ኮሮናቫይረስ እንደያዘው መታወቁን ይፋ አድርጓል።
“ጥሩ ነኝ እስካሁን ምንም ምልክት የለኝም አትደናገጡ” ሲልም ኢድሪስ በትዊተር አድናቂዎቹን አረጋግቷል። “ምንም እንኳ የሰው ዘር የተከፋፈለ ዓለም ላይ የሚኖር ቢሆንም በእንዲህ ያለው ጊዜ ግን አንዱ ለሌላው አጋርነቱን ማሳየት አለበት” ያለው ኢድሪስ ካለፈው አርብ ጀምሮ ራሱን ለይቶ መቆየቱንም አረጋግጧል።