ተስፋችን በእግዜር ነው! || ጌታቸው አበራ

ተስፋችን በእግዜር ነው! || ጌታቸው አበራ

       በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት በዓለማችን ለተፈጠረው 
                 ታላቅ ቀውስ ማስታወሻ

ዐይን በማትገባ በደቂቅ ህዋስ ጠንቅ፣
እየተጠለፈ አንድ-ባንድ ሲወድቅ፣
አእላፍ…ተከተተ በየጎጆው ዋሻ፣
ላስከፊው ጦርነት ምሽግ መዳረሻ፤
ዓለም ተናወጠች ፍጡር ተረበሸ፣
በዋለበት አድሮ እየነጋ መሸ።

..በጥበቡ መጥቆ ከምድር የዘለለ፣
ጨረቃ ላይ አርፎ ፈጣሪ የመሰለ፣
በብርሃን ፍጥነት ሮኬት አስፈትልኮ..፣
ሮቦት፣ ካሜራውን ወደ ማርስ ልኮ፣
የህይወት ምንጭን ፍንጭ በድካም ያሰሰ፣
የእውቀት ጥማቱን በህዋ ያራሰ…፣
አንዲት መናኛ “ጨርቅ” የፊት መሸፈኛ፣
አንዲት “ቬንቲሌተር” ንጹህ ትንፋሽ ማግኛ፣
ለዜጎቹ ማድረስ ተስኖት ሲዋትት፣
ይኸን የዓለም ምስጢር እንግዲህ ምን ይሉት?!

ተስፋችን በእግዜር ነው በማያመነታ፣
ሰማይና ምድርን በፈጠረ ጌታ!
ከራማ መንበር ላይ ቁልቁል በሚያስተውል፣
የዓለማት ገዢ ረቂቅ፣ ምጡቅ፣ ኃያል!

መጋቢት 2012 ዓ/ም
(አፕሪል 2020)

LEAVE A REPLY