የማይባክን ህልም በራያ ሰማይ ስር!!!!!

የማይባክን ህልም በራያ ሰማይ ስር!!!!!

ወይለት አለቀሰ ፣ከፋው መንደፈራ፣

መንጀሎም አፈረ በክፉ ሰው ስራ፣
ጎሊና ሆድ ባሰው፣
ተላወሰ ሆዱ ፣ሆርማት ፍቅር ፈራ፣
በአይኑ ጉድ አየበት፣
ወንድሙ ሲያረክሰው የወንድሙን ስራ።

ተረግሞ ነው እንጅ፣
ፈርዶበት ነው እንጅ፣
እጄን በእጄ ብሎ ጆሮው ጉድ የሰማ፣
ለሰው ዋስ ነበረ፣
መንጀሎና አራዱም ዳዩ ካላኮርማ።

ወረምኛ ገብርኤል፣
የጃውሳው ቀየ፣
ደጉ ተፈራ ቤት ጤፍ ውሃ ምርጊቱ፣
እንኳን ለወንድሙ፣
ሽመል አያነሳም ለላሙ ለከብቱ።

የወንድም ቀበኞች፣
ከመሃሉ ገብተው፣
ዙረውበት እንጅ፣
እንደ አንበሶ ዶሮ ፣ ባይተዋር ውሎበት፣
ራያ ራዩማ፣
በወንድሙ ገላ፣አይስብም ጨክኖ ፣የጥይት ቀለበት።

እነ አንገቶ ሞላ፣
ከመሃል መንገድ ላይ ቢቀርም ጉዟቸው፣
እንደ አልፎ ሂያጅ ጅረት፣
ሽው እልም አይሆንም አይጠፋም ስማቸው፣
ተገልጦ አየዋለሁ፣
ሃገሬን የሚለው፣
ወገኔን የሚለው፣ የዘመን ህልማቸው።

ጃኖ መንግስቱ ዘካላኮርማ

LEAVE A REPLY