አዳሜ || በማሕሙድ እንድሪስ

አዳሜ || በማሕሙድ እንድሪስ

ልትሰሚኝ አልቻልሽምና በፍቅር አምላክ ስማፀንሽ
ተረትቼ አቅም አጥቼ
ከግሮችሽ ስር ተደፍቼ ….. እያነባሁ ስለምንሽ
ሳግ አፍኖኝ ትንፋሽ አጥሮኝ
የቀረችኝ አንድ እወነቴን ላንቺ ብቻ መንገር አምሮኝ
እንደምንም የሞት ሞቴን ” እባክሽን ስሚኝ ” ስልሽ
ከመጤፍም ሳትቆጥሪኝ ተራምደሽኝ በመሄድሽ
የሆንኩትን እንድትሆኝ አልመኝም አንቺን ሁኜ
እንደ ጭካኔሽ ጨክኜ
አልልሽም የኔን ይስጥሽ ።
አልልሽም አቅም ይንሳሽ
ተስፈ ቆርጠሽ ህልምሽ መክኖ በኩዮችሽ ተበለጭ
አልልሽም ልክ እንደኔ ከሰውነት ተራ ውጪ …
አልልሽም !
አልልሽም !
አልልሽም …………… የኔን ይስጥሽ ።
ሁሌም ደስታሽ ሙሉ ይሁን
የሚያሳዝን የሚያስከፋ
የሚያስተክዝ የሚያስለቅስ … ክፉ ነገር አያግኝሽ ።
ይህም ሆኖ
ያደረግሽኝ እንዲገባሽ — ግልፅ ሆኖ እንዲታይሽ
እውነትሽን እውነት ብሎ
የሚያዳምጥሽ እጭና — የሰሚ ያለህ ያሰኝሽ! !!

LEAVE A REPLY