የውበት ጀርባው || በእውቀቱ ስዩም

የውበት ጀርባው || በእውቀቱ ስዩም

ላንተ የሚታይህ፤ የሚያምር ፈገግታ
ያበባ ጉትቻ
ላንተ እሚታይህ ውብ ገፅታ ብቻ

ጥርሷን ጉራማይሌ፤ የተነቀሰች ቀን
ያየቺው መከራ፤ ያየቺው ሰቀቀን
የጆሮዋን ጫፉን ፤ በሾህ ስትበሳ
የበላችው ፍዳ ፤ ያየቺው አበሳ
የዋጠችው ህመም፤ ከሬት የመረረ
የቀመሰው ማነው፤ከሷ በስተቀረ?

ከያንዳንዱ ታላቅ ፤ ውበት በስተጀርባ
ሲንዠቀዠቅ ኑሯል ፤ ብዙ ደምና እንባ

ይሄም ታላቅ ዜማ
ይሄም ታላቅ ስእል
ይሄም ታላቅ ተረት
ይሄም ታላቅ ድርሰት
ከፊትህ አልቆመም፤ እንደመና ወርዶ
ስቃይ ያቃልላል፤ ከስቃይ ተወልዶ ፤

ምንጭ ፤አዳምኤል

LEAVE A REPLY