የ #ኢትዮቴሌኮም ከፊል ድርሻ ሽያጭ ሂደት ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚዘገይ ተገለጸ

የ #ኢትዮቴሌኮም ከፊል ድርሻ ሽያጭ ሂደት ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚዘገይ ተገለጸ

መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ድርሻ ለመሸጥ (privatization) የወሰነውን ውሳኔ ለመተግበር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሳውቀዋል። ትላንት ጷግሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የቴሌኮም ዘርፍ ሪፎርምን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በተደረገው ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሴክተሩን ለሌሎች ሁለት ተወዳዳሪዎች የሥራ ፈቃድ (License) በመስጠት ለውድድር ክፍት ለማድረግ የተወሰነው ውሳኔ በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ተግባራዊ እንዲሆን ዝግጅቱ ተጠናቋል። ከ100 ዓመት በላይ በኢትዮጵያዊያን የተገነባውን ኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ የተወሰነው ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ተጨማሪ ጊዜ እንደሚወስድ እና ሂደቱን የበለጠ ለሕዝብ ግልፅ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በምን ያህል ጊዜ እንደሚገፋ ግን ግልፅ አላደረጉም። የቴሌኮም ዘርፍ ሪፎርምን በተመለከተ «ምንም ዓይነት የፖሊሲ ግፊት የለም፤ ቢኖርም የሚቀበል መንግሥት አይደለም ያለው።» ሲሉ ውሳኔው የሚመሩት መንግሥት እንደሆነ አስረድተዋል።

የ #ኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ድርሻን ግልፅነት በጎደለው ሂደት ለውጪ ባለኃብቶች ለመሸጥ የሚደረገው ጥድፊያ እንዲቆም ማሳሰቡ ይታወሳል። ሐምሌ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ኢዜማ ይፋ ባደረገው ምጥን ፖሊሲ ላይ የቴሌኮም ሴክተር ከተራ መረጃ ማስተላለፊያነት ባለፈ ሀገራዊ ደህንነትን ማረጋገጫ እና የሌሎች ዘርፎች የወደፊት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ስትራቴጂክ ዘርፍ በመሆኑ ዘርፉን በሚመለከት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ምክክር እንደሚፈልግ ተገልፆ ነበር። ዘርፉ የፈጠራ እና የምርምር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የሌሎች ዘርፎች ዕድገት ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት እና ኢትዮጵያዊያን ባለኃብቶች በዘርፉ ውስጥ ያላቸውን የወሳኝነት ሚና የሚቀንስ ተግባር መፈፀም አደገኛ ውጤት እንዳለው በኢዜማ ምጥን ፖሊሲ ውስጥ በስፋት ተብራርቷል።

ገዢው ፓርቲ አሁን ባለንበት የሽግግር ወቅት ሀገራዊ አንድነትን መጠበቅ፣ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ እና ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ የሚያስችሉንን መንግሥታዊ ተቋማትን የማጠናከር ሥራ ከመሥራት አልፎ ሕዝባዊ ይሁንታ ያለገኝባቸውን በቀጣይ ወዳደሮ የሚያሸንፈው መንግትሥ እና በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁነቶች ላይ ከፍተኛ ውጤት ያላቸውን የፖሊሲ አማራጮች ትግበራ ውስጥ መግባት እንደሌለበት ምጥን ፖሊሲው ላይ የተብራራ ሲሆን ተመሳሳይ የፖሊሲ ጉዳዮችን ላይ ያሉትን አማራጮች ማኅበረሰቡ በሚገባ ተረድቶ የተሻለ የሚለውን በነፃ ምርጫው ሲያሳውቅ ብቻ መተግበር እንዳለባቸው ተጠቅሶ ነበር።

መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለውጭ ባለኃብቶች ለመሸጥ የተከተለው ሂደት ግልፅነት የሌለው እና የተጣደፈ መሆኑ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የዓለም ባንክ ከዚህ ቀደም ሌሎች ሀገሮች ላይ ጫና በማሳደር ከተደረጉ ሪፎርሞች ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና ዓለም ባንክ እየተገፉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያደረጉ ሀገራት ከእነዚህ ተቋማት ጥገኝነት መላቀቅ አቅቷቸው ሀገራዊ ሉዓላዊነታቸው አደጋ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በምጥን ፖሊሲው ላይ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ውይይት ያደረገ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያየ መንገድ ባሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት መረዳት እንደተቻለው መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ድርሻ ሽያጭን በተመለከተ ለሕዝብ በቂ መረጃ እንዳላቀረበ ነው። በተጨማሪም በዳሰሳው ውስጥ ከተሳተፉ ዜጎች አብላጫዎቹ ገዢው ፓርቲ በምርጫ ይሁኝታ ሳያገኝ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን የመወሰን ሥልጣን የለውም ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

ትልንት በተደረገው ውይይት ምጥን ፖሊሲውን ያዘጋጁት ሁለት ባለሙያዎች እና ሁለት የኢዜማ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተገኝተው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሀገራችን የሚደረጉ ሪፎርሞችን እየተከታተለ ጉድለቶች እንዲታረሙ የማስገንዘብ ሥራ እና በጥናት ላይ የተደገፉ የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረብ እንደሚቀጥል ታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም 40% ድርሻ ለውጭ (ድንበር ተሻጋሪ) ኩባንያዎች መቅረቡ የሚደቅናቸው ሀገራዊ አደጋዎች እና የሽያጭ ሂደቱ ችግሮች ላይ በኢዜማ የተዘጋጀውን ምጥን ፖሊሲ ለማግኘት ይህንን መስፈንጠሪያ ይጫኑ

https://drive.google.com/file/d/1MRjHK8LaiOUXLAaXCUZS8avbfnQNBMGS/view?usp=sharing

LEAVE A REPLY