ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያን እየመራ የሚገኘው የብልፅግና ፓርቲ፣ የትግራይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ነብዩ ስሁል ሚካኤል ዛሬ በትግራይ እየተካሄደ ያለው ምርጫ ሕጋዊ አይደለም አሉ።
“ህወሓት እያካሄደ ያለው ምርጫ ሳይሆን፣ እንዲሁ የዲሞክራሲ ልምምድ እያደረገ እንደሆነ ነው እኛ የምናየው፤ የምንገመግመው። ምክንያቱም አንድን እንቅስቃሴ ምርጫ ለማለት መስፈርቶች አሉ። ምርጫው ደግሞ እነዚያን መስፈርቶች አያማሏም” ያሉት ወጣቱ የትግራይ የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሓላፊ፣ እየሆነ ያለው አካሄድ በሕግ አግባብም ትክክል አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
“ከመሠረታዊ ነገር ስንጀምር ምርጫው ሕጋዊ አይደለም። ሕጋዊ ያልሆነው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ስለማይፈቅደው ነው። ሁለተኛ ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ አለ። በተደጋጋሚ ነው ይሄንን ውሳኔ ያሳለፈው። ከቀናት በፊትም አጽድቆታል። ስለዚህ አንድ ምርጫ፤ ምርጫ እንዲባል የመጀመሪያው መስፈርቱ ሕጋዊ መሆኑ ነው። ስለዚህ ሕጋዊ ስላልሆነ ምርጫ ብለንም መጥራት የለብንም” በማለት የዛሬው የትግራይ ክልል ምርጫ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው አረጋግጠዋል።
“በሌላ በኩል ምርጫ የይስሙላ ምርጫ ነው። ህወሓት አጀንዳ ስላጣ እያደረገው ያለው ቀቢጸ ተስፋዊ ሂደት ነው። ይሄ ደግሞ ምንም ዋጋ የለውም። አብዛኛዎቹን መስፈርቶች አላሟላም፣ የሕዝባችንም ፍላጎት አይደለም፣ እውነተኛ የምርጫ ሂደትን የተከተለና ተአማኒ አይደለም። ስለዚህ በዚህ መልኩ ስናየው ምርጫ ብለን መጥራት አንችልም።” በማለት ለቢቢሲ ጉዳዮን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ነቢዮ ስሁል፤ ይህን እያደረገ ባለው ህወሓት ውስጥ በተፅዕኖ ያሉና ብልፅግናን መቀላቀል የሚፈልጉ በርካታ አባላት መኖራቸውን ተጨባጭ መረጃ አለን ሲሉም ተናግረዋል።
“የትግራይ ሕዝብም ሕግ አክብሮ፣ ሐሳቦች በትክክል ተንሸራሽረው፣ እውነተኛ ምርጫ ተካሂዶ፣ በሕዝብ የተመረጠ ፓርቲ መንግሥት ሆኖ እንዲመራው ነው የሚፈልገው፤ ለዚህም ነው የታገለው”በማለት የትግራይ ሕዝብና ህወሓት ፈጽሞ አንድ እንዳልሆኑ ያመላከቱት አቶ ነቢዮ፤ “ሀቁን ከትግራይ ሕዝብ ታሪክም አንጻር ስናየው የትግራይ ፍላጎት ይሄ ነው እንጂ በጨረባ ምርጫ፣ የውሸት ምርጫ አድርጎ መንግሥት መሰየም አይፈልግም። ስለዚህ የመነጠል ስሜት አይሰማንም” ሲሉ ብልፅግና በትግራይ ሕዝብ ተቀባይነት እንዳለው ገልጸዋል።