በእምነታቸው ምክንያት እሰከ 16 ዓመታት የታሠሩ 20 ኤርትራውያን ከእስር ተፈቱ

በእምነታቸው ምክንያት እሰከ 16 ዓመታት የታሠሩ 20 ኤርትራውያን ከእስር ተፈቱ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኤርትራ መንግሥት በእምነታቸው ምክንያት ለዓመታት አስሯቸው የነበሩ ከ20 በላይ ግለሰቦችን መልቀቁ ተሰማ።

ታሳሪዎቹ አብዛኞቹ ከወንጌላውያን እና ጴንጤቆስጣል ቤተ እምነቶች እንደነበሩ የጠቆሙት የቢቢሲ የዜና ምንጮች፤ ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል የተወሰኑት ከአስመራ ውጪ ታስረው መቆየታቸውን አስረድተዋል።
ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገውና በኤርትራ ስላለ የእምነት ነጻነት የሚከራከረው ሃኒባል ዳንኤል፤ ከእስር ከተለቀቁት ግለሰቦች መካከል ለ16 ዓመታት ታስረው የቆዩ እንደሚገኙም ይፋ አድርጓል።
የተለያዮ ምንጮች ጉዳዮን አስመልክቶ ይህን ቢሉም የኤርትራ መንግሥት በይፋ ስለ እስረኞቹ መለቀቅ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ግለሰቦቹ ከእስር የወጡት የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ሲሆን፤ ለዋስትና ማስያዣነት የተጠየቀው የቤት ባለቤትነት ወይንም የንግድ ፈቃድ መሆኑንም ከመረጃ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል።
በኤርትራ የእምነት ነጻነት እንዲኖር የሚሠሩ አካላት በበኩላቸው በኤርትራ ሦስት የይሖዋ እምነት ምስክር አባላት ከ25 ዓመት በላይ በእስር ላይ እንዳሉ በመግለፅ እየተከራከሩ ይገኛሉ።
በኤርትራ መንግሥት እውቅና ያላቸው የኦርቶዶክስ ክርስትና፣ ካቶሊክ፣ ሉትራን እና እስልምና ሃይማኖቶች ብቻ ሲሆኑ፣ እኤአ ከ2002 ጀምሮ ከእነዚህ ሃይማኖቶች ውጪ ያሉ በአጠቃላይ እምነታቸውን በይፋ ለማካሄድ ህጋዊ እውቅና መነፈጋቸው ይታወቃል።
ከዚህ በተጨማሪ የኤርትራ መንግሥት በ1994 ላይ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስትያናትን ሙሉ በሙሉ በመዝጋቱ፣ በዚህም የተነሳ ለአምልኮ ስርዓት ወይንም የተለያዩ ማህበራዊ ህይወቶቻቸውን ተሰባስቦ ማከናወን መከልከላቸውን የዓለም ዐቀፍ ሃይማኖቶች ነጻነት ላይ የሚሠራው የአሜሪካው ተቋም፣ USCIRF አስታውቋል።

LEAVE A REPLY