ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትብብር ለመሥራት የሠባት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ስምምነት መፈራረማቸው ተሰማ።
ስምምነቱ በተከናወነበት ወቅት የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት በተለያዩ መስኮች ላይ በጋራ በመሥራት ላይ እንደሚገኙና ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና ዋነኛ አጋር መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በነበሩት ጊዜያት በአጋርነት በተከናወኑ ተግባራትም በተለይ በሶሺዮ ኢኮኖሚ እድገት ረገድ የተገኘው ውጤት እንዳለ ሆኖ፣ የሃገሪቱ ፈጣን እድገት ከሚጠይቀው ፍላጎት አንፃር ይህን አጋርነት በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ማጠንከር ያስፈልጋል ነው የተባለው።
በድህነት ቅነሳ፣ በሥራ ፈጠራ፣ አምራች ዘርፉን በማጎልበት፣ በአቅም ግንባታ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈን እና በአካባቢ ጥበቃ ረገድ አጋርነትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም እነዚህን ወሳኝ ተግባራት ስኬታማ በሆነ መልኩ ለመፈፀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
አሁን የተፈጸመው የጋራ ስምምነትም የሠባት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ያስገነዘቡት ሚኒስትሩ፣ የስምምነቱ ትግበራ ትሩፋትም ኢትዮጵያ በቀጣይ ዐሥር ዓመታት ውስጥ ቅድሚያ ለሰጠቻቸው የልማት ሥራዎች ውጤታማነት ግዙፍ ሚና እንደሚያበረክት ነው የተገለጸው።
ስምምነቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስተግበር መንግሥት ቁርጠኛ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ውጤታማ የሆነ ክትትል እና ቁጥጥር፣ እንዲሁም ግምገማዎችን በመተግበር ብሎም ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ በኢትዮጵያ ዶክተር ካትሪን ሶዚ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ በተለይ ለአጀንዳ 2030 የዘላቂ ልማት ስኬት ህዝብ፣ ሰላም፣ ብልፅግና እና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።