ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ ታከለ ኡማ፤ ከህገ ወጥ መሬት ወረራውና የኮንዶሚኒየም እደላው ጋር በተያያዘ ለሠሩት ሥራ ምንም የሚጸጸቱበት ነገር እንደሌለ ዳግመኛ አረጋገጡ።
በአዲስ አበባ አስተዳደር በነበራቸው የሁለት ዓመት የሥልጣን ቆይታ አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት ታከለ ኡማ ሰሞኑን ክፉኛ እያስተቻቸው ያለው ሥራቸውን በእጅጉ እንደሚኮሩበትና ትክክል እንደሆኑም ጭምር ገልጸዋል።
ሁለት ዓመት ከቆዮበት የአዲስ አበባ ከንቲባነት ቦታቸው በመነሳትዎ ቅሬታ ተሰምትዎታል ይባላል በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ አወዛጋቢው የቀድሞ ከንቲባ፤” ብዙ ሊባል ይችላል። እውነታው ግን የተለየ ነው።
ከአዲስ አበባ ኃላፊነቴ እንደምነሳና ወደ ሌላ ተልዕኮ እንደምሄድ ከሁለት ወራት በፊት አውቅ ነበር። ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ኃላፊነት የመጣሁበትን ወይም ኃላፊነት የተረከብኩበትን ሁለተኛ ዓመት ከሌሎች ባልደረቦች ጋር በዘከርንበት ዕለት ሥራ ለማስረከብ ዝግጁ ነበርኩ።
ነገር ግን በፓርቲያችን በኩል ዝግጅቱን ስላልጨረሱ ነው እስከ ነሐሴ አጋማሽ በኃላፊነት ላይ የቆየሁት። ከኃላፊነት በመነሳቴ አልተከፋሁም፣ እንዲያውም ደስተኛ ነኝ ብል ይቀለኛል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“እኔ የለውጡ የታሪክ ጉዞ አካል ነኝ። ከምክትል ከንቲባነት ኃላፊነት የተነሳሁት በራሴ ፍላጎት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መልቀቂያ አቅርቤ ነው። እውነታው ይህ ነው።” ያሉት ታከለ ኡማ፤ አንድ ኃላፊ እስከሚነሳ መጠበቅ የለበትም የሚል እምነት ያለኝ ሰው ነኝ፤ ይህንን እምነቴንም በተግባር ፈጽሜያለሁ ሲሉም የእርሳቸውን ከሥልጣን የመነሳት ምስጢር ሸፋፍነው ለማለፍ ሞክረዋል።
ታማኝ ምንጮቻችን ታከለ ኡማ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ጠቁመው፤ ይህ የሆነው ግን ኢዜማ የመሬት ወረራውን እና የኮንዶሚኒየም ህገ ወጥ እደላውን አስመልክቶ ያደረገው ጥናትና ተጨባጭ ወጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዮ ሹማምንቶች ዘንድ አስቀድሞ በመድረሱ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።