ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ለ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መቀረቡ ተሰማ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገበታ ለሃገር ፕሮጀክትን አስመልክቶ ከፋይናንስ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለፕሮጀክቱ 30 ሚሊዮን ብር ለመስጠት በቦርዱ አማካኝነት መወሰኑን ይፋ አድርጓል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የሆኑ ሌሎች አካላትም ፕሮጀክቱን በፋይናንስ በሚደግፉበት ሁኔታና የፕሮጀክቱ የፋይናንስ አጠቃቀምና ግልጽነት ዙሪያ ሀሳብና ጥያቄ ማቅረባቸውም ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ፕሮጀክቱ በግልጽ የፋይናንስ ሥርዓት የሚመራ መሆኑን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቶቹ ሃገርን ከማሳደግ አኳያ ያላቸው ሚና ወሳኝ እንደሆነና ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው አብራርተዋል።
በውይይቱ ላይ የባንኩ ገዢ የፋይናንስ ዘርፉም ለፕሮጀክቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ባንኩ ለተቋማቱ የድጋፍ ጥያቄ ደብዳቤ እንደሚልክና ሁሉም በቦርዳቸው ተወያይተው እስከ መስከረም 2013 መጨረሻ እንዲያሳውቁ አሳስበዋል።
በመንግሥት በኩል ከፋይናንስ ተቋማት የሚደረገውን ድጋፍ የሚያስተባበር ኮሚቴ መቋቋሙንና በሚቀጥለው ሣምንት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር እንደሚወያይ የገለፁት ይናገር ደሴ፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ቢያንስ ሦስት ቢሊዮን ብር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።