ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑ፣ በፌደራል መንግሥቱና በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው እና 27 ዓመታት ሀገሪቱን በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ የዘወራት ቡድን አካል የሆኑ ግለሰቦች ዛሬ በትግራይ ክልል ምርጫ ላይ እየተወዳደሩ ናቸው።
አይነኬ ይመስሉ የነበሩትና በለውጡ ማለዳ ከግፍና ዝርፊያቸው ጋር ሸሽተው መቀለ የከተሙት ዋና ዋና የህወሓት አባላት በፌደራል መንግሥቱ እወቅና በተነፈገው ምርጫ ላይ በተለያዮ የምርጫ ጣቢያዎች አማካይነት ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ለውድድር መቅረባቸው ታይቷል።
በለውጡ ማግስት አንዴ መቀሌ፣ ሌላ ጊዜ አዲስ አበባ በመርገጥ ወጥ የሆነ አቋም ለማሳየት የተቸገሩት፣ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንትና የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ በአድዋ ከተማ ፓርቲያቸውን ወክለው እየተወዳደሩ ናቸው።
የማፍያው ቡድን መሪ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የትውልድ ከተማ በሆነችው አድዋ ከተማ ውስጥ ባሉ ሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የቀድሞዋ የንግድ ሚኒስትር ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ) ፣ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና በርካታ አሳሪ ሕጎችን አርቃቂ የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ እየተወዳደሩ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያሳያል።