በቅርቡ በመቀሌ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ማድረጋቸው የታወቀው ዳውድ ኢብሳ ከሊቀመንበርነት ታገዱ

በቅርቡ በመቀሌ ከህወሓት ጋር ግንኙነት ማድረጋቸው የታወቀው ዳውድ ኢብሳ ከሊቀመንበርነት ታገዱ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ ድርጅቱን ለ21 ዓመት የመሩትን አቶ ዳውድ ኢብሳን ከሊቀመንበርነት ማንሳቱን አስታወቀ።

“ኦቦ ዳዉድ ኢብሳ በሊቀመንበርነት በቆዩባቸው 21 ዓመታት የድርጅቱን ገንዘብና ሀብት ብቻቸውን ሲያዙበት ኖረዋል፤ በድርጅቱ ውስጥ አድልዎ በመፍጠር የአካባቢያቸውን ሰዎችና ዘመዶች ቁልፍ የሥራ መደቦች ላይ በመመደብ ጥቅማቸውን አስጠብቀዋል” ሲልም የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ሊቀመንበሩን ያገደበትን ምክንያት አብራርቷል።
 “በዚህ መሰል ኣካሄድ ከድርጅቱ ህገ ደንብና አሠራር ውጭ የራሳቸውን አምባገነንነት በድርጅቱ ላይ አነግሰዋል”  ያለው የሥራ አስፈጻሚው መግለጫ፤  “አቶ ዳዉድ ኢብሳ 21 ዓመት በሊቀ መንበርነት በቆዩበት ጊዜ ድርጅቱ ፈራርሶ ከነበረበት ወረደ እንጂ እድገት አላሳየም። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ዳውድ በአመራር ዘመናቸው የኦነግ ዋና አመራርና መዋቅሩ እንዲፈርስ ማድረጋቸውን፣ የጋራ አመራር የሚለው በሀሳብ እንጂ በተግባር ሊታይ አልቻለም” ብሏል።
አሁን ላይ ኦነግ ዉስጥ የተማሩና ልምድ የቀሰሙ አባላት ቁጥር አነስተኛ ነው ያለው ግንባሩ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው አቶ ዳዉድ ናቸው ሲል ወቅሷቸዋል።
 ብዙ አመታት ባስቆጠረው የኦሮሞ ነጻነት ትግል ውስጥ ኦነግ ከተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ትግል ጋር የትግል አጋርነትና ወዳጅነት ለመፍጠር ጥረቶችእንዳደረገ የጠቆመው የግንባሩ መግለጫ፤ ይህም የትግል አጋርነትና ወዳጅነት በእኩልነት፣ በመከባበርና በዲሞክራስያዊ መርህ ላይ መሆንን መሰረት ያደረገ መሆኑን አመላክቷል።
ለታክቲክ ወይም ለግዜያዊ ጥቅም ተብሎ የሚደረግ ትብብር ዘለቄታዊ ጥቅም አያስገኝም ያለው መግለጫ፤ በተለይም ህወሓት በኦሮሞ ህዝብና በኦሮሞ ታጋዮች ላይ ላደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ይቅርታ ጠይቆ በኦሮሞ ህዝብ ቅቡልነት አስኪያገኝ ድረስ፣ ኦነግ ከዚህ ድርጅት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑ ይታወቅልኝ ብሏል።
ሆኖም አቶ ዳዉድ ኢብሳ ከአመራሩ ዕውቅና ውጪ የፋይናንስ ሠራተኛቸውን በቅርቡ መቀሌ በተካሄደው የህወሃት ስብሰባ ላይ አንዲሳተፍና ግንኙነት እንዲያደርግ መላኩ የግንባሩን ፖሊሲ የጣሰ ህገ ወጥ ድርጊት ሆኖ አግኝተነዋል ያለው ሥራ አስፈጻሚው ፤ ኦነግ በኦሮሞና በትግራይ ህዝብ መካከል ያለው ወንድማዊና ዘላቂ ግንኙነት አንዲጠናከር እንደሚሠራም ይፋ አድርጓል።

LEAVE A REPLY