በኢትዮጵያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጥላል ተባለ

በኢትዮጵያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጥላል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና ሰሞኑን በኢትዮጵያ እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግሥታት ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊጥል እንደሚችል የምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት የልህቀት ማዕከል አስታወቀ።

ማዕከሉ እንደገለጸው ከሆነ በተለይም በመካከለኛው እና ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ሊጥል ይችላል ተብሎ ተገምቷል።
በእነዚህ ሀገራት የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋዎችን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ የልህቀት ማዕከሉ አስጠንቅቋል፡፡
የዝናብ ትንበያው ከዛሬ ጀምሮ በሚቀጠሉት ሠባት ቀናት ውስጥ የሚጠበቅ ሲሆን በምዕራብ እና መካከለኛው ኢትዮጵያ ጥቂት ቦታዎች ከ 200 ሚሊ ሜትር በላይ ከባድ ዝናብ ይጠበቃል ነው ተብሏል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በጎረቤት ሀገራት ደቡብ-ምዕራብ ሱዳን፣ከሰሜን-ምዕራብ እስከ ደቡብ-ምዕራብ ደቡብ ሱዳን፣በምዕራብ እና፣ሰሜን-ምስራቅ ሶማሊያ እንዲሁም በሰሜን-ምዕራብ ዩጋንዳ እና ምዕራብ ኬንያ ከ 50 እስከ 200 ሚሊ ሜትር የሆነ መካከለኛ ዝናብ እንደሚኖር ነው የተነገረው።
በሰሜን፣ በምስራቅ እና በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ሱዳን፣ በሰሜን ምዕራብ ኤርትራ፣ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ደቡብ ሱዳን፣ በሰሜን እና በደቡብ ሶማሊያ፣ በጅቡቲ የባህር ዳርቻዎች፣ በማዕከላዊ እና በምስራቅ ዩጋንዳ አንዳንድ አካባቢዎች ከ 50 ሚሊ ሜትር በታች የሆነ ቀላል ዝናብ ይኖራል ተብሏል፡፡
እንደ የምስራቅ አፍሪካ የአየር ንብረት የልህቀት ማዕከል ትንበያ ከሆነ አብዛኞቹ፣ የደቡብ ምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች፤ የታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ ፣ ደቡባዊ ኡጋንዳ ፣ ከምስራቅ እስከ ሰሜን ምዕራብ ኬንያ፣ደቡብ ምስራቅ ደቡብ ሱዳን ፣ ማዕከላዊ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ እና የኤርትራ ባህር ዳርቻዎች ደረቃማ የአየር ሁኔታ ሊያመዝን ይችላል።
በሌላ በኩል በማዕከሉ የሙቀት ትንበያ መሰረት በሰሜን-ምስራቅ ኢትዮጵያ አንዳንድ ክፍሎች ፤ ሰሜን ሱዳን፣ የኤርትራ ባህር ዳርቻዎች፣ በጅቡቲ እና የሶማሊያ ሰሜን ምዕራብ ጠረፍ ክፍሎች ከ 32 ℃ በላይ የሆነ ከፍተኛ ዕለታዊ አማካይ የሙቀት መጠን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የደቡብ-ምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች ከ 20 እስከ 32 የሆነ መካከለኛ የሙቀት መጠን ሲጠበቅ፤ አብዛኞቹ ደቡባዊ እና ሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች ገድሞ ከ20 በታች የሆነ የሙቀት መጠን ይኖራቸዋል ነው የተባለው፡፡

LEAVE A REPLY