በክረምቱ ጎርፍ በኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መጎዳታቸውን መንግሥት አስታወቀ

በክረምቱ ጎርፍ በኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መጎዳታቸውን መንግሥት አስታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች መጎዳታቸውን መንግሥት አስታወቀ።

የሰላም ሚኒስትሯ ሞፈርያት ካሚል እና የውሃ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ፤ ለጋዜጠኞች  በሰጡት መግለጫ የዘንድሮ ክረምት ዝናብ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በቤቶችና መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
ወ/ሮ ሞፈርያት ካሚል በሦስት ክልሎች እና 23 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ገልፀው፣ 580 ሺኅ ዜጎች መጎዳታቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 217 ሺኅ የሚሆኑት ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አስረድተዋል።
እንደ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ገለጻ ከሆነ፤ ሰሞኑን የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከአዋሽ ወንዝ መነሻ እስከ መድረሻው ፣ በኦሞ ወንዝ፣ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ በሚገኙ እንደ ባቱ (ዝዋይ) እና መቂ ባሉ ከተሞች፣ በአባይ ተፋሰስ አካባቢ እና ጣና ሐይቅን ጀምሮ እስከ ሱዳን ፣ እንደዚሁም በባሮ ወንዝ መሆኑን ታውቋል።
ሰሞኑን በአንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በመቶ አመታት ውስጥ አንዴ የሚከሰት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ስለሺ፤ በአዋሽ ወንዝ የተከሰተው ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መሆኑን አብራርተዋል።
ዘንድሮ ከባድ ዝናብ መተንበዩንና  ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ እንደምሳሌም በኦሮሚያና በአፋር ክልል ውስጥ 134 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውሃ መውረጃ መስመር ጥገና እንደተደረገም ተናግረዋል።
“ዘንድሮ አደጋው በደረሰበት ስፍራ በሄሊኮፕተር በመታገዝ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ሳይደርስ የተሳካ ሥራ መሥራት ተችሏል፤ ጎርፉ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በተወሰኑ ከብቶች ላይ አደጋ ደርሷል፤ የተወሰኑ ቤቶችም በጎርፍ ተውጠዋል” ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፤  በቀጣይም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለዜጎች ያደርጋል ብለዋል።

LEAVE A REPLY