ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰላማዊ ትግልን ብቸኛ አማራጩ አድርጎ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የድርጅቱ ሊቀ-መንበር የነበሩትን የአቶ ዳውድ ኢብሣ ከሥራ መታገድ እና በቀጣይ ሰላማዊ ትግል መምረጡን አስመልክቶም ድርጅቱ ሰፋ ያለ መግለጫ ዛሬ ሰጥቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው፤ ድርጅቱ የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ አካላት እና ከህወሃት ጋር ግንኙኘት አለው የሚለውን እና ሌሎች የሚነሱት ሀሳቦችን ለማጥራት፣ እንዲሁም በድርጅቱ ቀጣይ ሂደት ላይ ለመወያየት ነበር ብሏል።
ይሁን እንጂ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ለማድረግ ወደ ድርጅቱ ግቢ በሚገባበት ወቅት በአቶ ዳውድ ኢብሳ አዛዥነት፣ ኮሚቴው ወደ ግቢ እንዳይገቡ መደረጋቸውን እና እንግልት እንደገጠማቸው ኮሚቴው ገልጿል።
ኦነግን ሲመሩ የነበሩት ኦቦ ዳውድ ኢብሳ እገዳ ቢደረግባቸውም፣ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጋር ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የዶክመንት እና ንብረት የመሰብሰብ ሥራ ውስጥ መግባታቸውን የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዲባ ይፋ አድርገዋል።
በቀጣይም የኦሮሞ ነጻት ግንባር (ኦነግ) ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ትግል እንደሚያደርግ ለመግለፅ እንወዳለን ያለው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ ከሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ ውጪ እገዳ የተደረገበት የድርጅቱ አመራር ወይም አባል ባለመኖሩ በዚህ ምክንያት ከድርጅቱ የሸሹ አካላት እንዲመለሱ ሲሉ ጥሪ አቅርቧል።